ሳዑዲ በቁጥጥር ስር ያዋለቻቸውን ባለሀብቶች እና ልዑላን በገንዘብ ልትፈታ ነው

BBN NEWS

ሳዑዲ አረቢያ በቁጥጥር ስር ያዋለቻቸውን የልዑላን ቤተሰቦች እና ባለሀብቶች በይቅርታ እና በገንዘብ ቅጣት ልትፈታ መሆኑ ተገለጸ.. የሳዑዲ አረቢያ ፖሊስ በወጣቱ የሳዑዲ አልጋ ወራሽ ልኡል መሀመድ ቢን ሰልማን ትዕዛዝ ልዑላን እና ባለሀብቶችን ሰብስቦ ማሰሩ ይታወቃል.. የሳዑዲ መንግስት ከታሳሪዎቹ ጋር ድርድር ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በመጨረሻም ድርድሩ መቋጫ ማግኘቱ ተሰምቷል.. በድርድሩ መሰረትም በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች፣ በቅርቡ በገንዘብ ቅጣት እና በይቅርታ እንደሚፈቱ ታውቋል.. ቢቢሲ የሳዑዲ አረቢያን ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በጸረ ሙስና ዘመቻ የታሰሩት ሰዎች፣ በይቅርታ እና ገንዘብ በመክፈል ከእስር መፈታት እንደሚፈልጉ ለሀገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል.. የሳዑዲ መንግስትም ለጉዳዩ ይሁንታ መስጠቱን የገለጸው ዘገባው፣ በተደረሰው ስምምነት መሰረትም መንግስት በቅርቡ እስረኞቹን እንደሚፈታ ዘገባው ያክላል.. ከእስር የሚፈቱት ሰዎች በቀረበው የድርድር ሀሳብ የሚስማሙ ብቻ መሆናቸውም ታውቋል.. በቀረበው የድርድር ሀሳብ ላይ ያልተስማሙ ታሳሪዎች መኖራቸውም የተገለጸ ሲሆን፣ እኒዚህ ታሳሪዎች ምንም ዓይነት ሙስና ውስጥ እንዳልተዘፈቁ የተከራከሩ ናቸው ተብሏል.. በዚህም ምክንያት በቀጣይ ህጋዊ ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚችልም ተጠቁሟል.. ከኢትዮጵያዊ እናት የሚወለዱትን ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ጨምሮ 11 ልዑላን፣ አራት ሚኒስትሮች እና የቀድሞ ሚኒስትሮች እንዲሁም ሌሎች በርካታ ባለሀብቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል.. ከታሳሪዎቹ መካከል አንዱ የነበሩት ልዑል ማቲን ቢን አብዱላህ ባለፈው ሳምንት በገንዘብ መደራደራቸውን ተከትሎ፣ ከአንድ ቢሊዬን የአሜሪካ ዶላር በላይ ከከፈሉ በኋላ ከእስር ተፈትተዋል.. ሼህ አላሙዲን በገንዘብ እና በይቅርታ ለመውጣት ከተደራደሩ ባለሀብቶች መካከል እንደሚገኙበት ምንጮች ይጠቁማሉ::

 

ሳዑዲ በቁጥጥር ስር ያዋለቻቸውን ባለሀብቶች እና ልዑላን በገንዘብ ልትፈታ ነው