የኦሮሞ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ሥልጣን ባለቤት ነው (ስህተት)

ሰርጸ ደስታ

ይሄን የምታነቡት በኦሮሚያ ክልል ሕገመንግስት ውስጥ ነው (አንቀጽ 8)፡፡ ይህ ለኦሮምያ ለያት የሚያደርገው በይፋ ኦሮሞ የሚለው ቃል ክክልሉ ሥያሜ ኦሮሚያ ከሚለው ስለሚለይ ነው፡፡ የአፋር፣ ሶማሌና ሐረሪም በተመሳሳይ ቢገለጽም የክልሉ መጠሪያና የብሔረሰቦቹ መጠሪያ አንደ በመሆኑ በክልሉ የሚኖር ሕዝብ (በሙሉ) የሚል ትርጉም ሊመስል ይችላል፡፡ የኦሮሚያ ግን በግልጽ  የኦሮሞ ሕዝብ ነው የሚለው፡፡ ይሄን ላስተዋለ ከኦሮሞ በቀር በክልሉ የሚኖር ሌላ ሕዝብ ሥልጣን የለውም የሚል አንድምታ ነው ያለው፡፡ እንደ ክልላዊ ሕገመንግስት ይሄ በጣም አግባብነት የጎደለው ሕግ ነው፡፡ እርግጥ ነው ክልሎች በተግባርም የሚከተሉት ይሄንኑ ነው፡፡ በኦሮምያ ውስጥ ብዙ ሌሎች ሕዝቦች እንዳሉ ከእነጭርሱም የማይቀበል ነው፡፡ የሌሎቹም ያው ነው፡፡ ከላይ ባልኩት ሁኔታ የኦሮሚያ በግልጽ ስለሚነበብ እንጂ፡፡ ይሄን የሚያህል ጉልህ ግድፈት ያለበት ሰነድ ሕገ መንግስት መባሉ በራሱ ምን ያህል የከፋ ሕገወጥነት ነው፡፡ ኦሮሚያም ይሁን ሌላው ክልላው መንግስት የአንድ ብሔረሰብ መንግስት እንደሆነ በሕጉ አስቀምጦ የእኔ ብሔረሰብ በየትኛውም ክልል የመኖር መብት አለው ብሎ መናገር የሚቻል አልመሰለኝም፡፡ በአጠቃላይ ክልሎች ለየብሔረሰቡ የተሸነሸኑ ስለሆነ እንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ክልል የመኖር እድሉ የሚወሰነው የክልሉ ባለቤት በሆነው ብሔረሰብ ነው ማለት ነው፡፡ ክልሎችም በእርግጥም እያደረጉ ያሉት ይሄንኑ ነው፡፡ ዛሬ ከሱማሌ ክልል ኦሮሞ የተባለ ሁሉ ይውጣ ተብሎ የተፈረደበትም በእዚሁ “ሕገ-መንግስታዊ” አግባብ እንደሆነ አስቡ፡፡ በአማራው ሕዝብ በተለያዩ ክልሎች ተመሳሳይ ፍርድ ሲፈረድበትም ለክልሎቹ ይሄ “ሕገ-መንግስታዊ” መብት ነበራቸው፡፡ ኦሮምያን ከሌሎችም ለይት የሚያደርገው ግን ከሌሎች በተለየ ብዙ “ኦሮሞ” ያልሆነ ሕዝብ የሚኖርበት ክልል መሆኑ ነው፡፡ አንዳንዶቹም በክልሉ ነበር ነዋሪ እንደሆኑ ራሱ እውቅና አይሰጣቸውም እንጂ በእርግጥም ከማንም ቀድመው በክልሉ ነዋሪ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የዜይን (ዝዋይ) ህዝብ አስተውሉ፡፡ ይህ ሁሉ ባይሆን እንኳን  ሕገመንግስቱ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ መነበቡ የማይታረቅ ስህተት ነው፡፡  ዛሬ ድረስ የክልል ባለስልጣናት የአንድ ብሔረሰብ ባለስልጣን እንጂ የክልሉ ነዋሪዎችን እንደመንግስት በእንድ አይን አይተው የሚያስተዳድሩበት የሕሊና ዝግጁነት የላቸውም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦሮሚያ ባለስልጣናት በሕዝቦችና አገር አንድነት መሪ ተዋናይ ሆነው እየታዩ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በፊት መጀመሪያ “ሕገመንግስት” የተባለውን በአዲስ መልክ ማዘጋጀት አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ ለማ የኦሮሞ ፕሬዘዳንት እንጂ የኦሮሚያ ፕሬዘዳንት አይደለም አንደ “ሕገ-መንግስቱ”. የሌሎቹም ክልሎች አንደዛው፡፡ በነገራችን ላይ የአማራ፣ የቤኒሻንጉል፣ የደቡብ፣ ጋምቤላ ይለያል፡፡ የክልሉ ሕዝቦች ነው የሚለው፡፡ ያም ሆኖ የክልሉ ሕዝቦች ተብለው የተዘረዘሩት ደግሞ ያው ወስዶ እንደ ኦሮሚያው ነው የሚያደርገው ከአማራ ክልል በቀር፡፡ ስለዚህ እነለማ በይፋ ይህን “ሕገመንግስት” መሰረዝና አስተሳሰባቸውንም የክልሉ ባለስልጣናት እንጂ የኦሮሞ ብቻ ባለስልጣን እንዳልሆኑ በግልጽ መናገር ይገባቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ ማሰብ ሲጀመር ብቻ ክልሎች ፌደራሊዝም ሊያስብላቸው ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን አሁን ያለው የዘር ፌደራል አወቃቀር መፍረስ ግድ ይላል የሕዝቦችን ሠላማዊ ኑሩ መሳካት ከታሰበ፡፡

ይሄን እንደው ለጥቆማ ነው፡፡ ሕገ መንግስት ተብዬውን ዋናውን ሳይቀር ግን በትኩረት ብታዩት በሚገርም ሁኔታ ጸረ አገርነቱንና ጸረ ሕዝብነቱን ታስተውላላችሁ፡፡ ብዙዎች በተለይም ደግሞ ምሁር ነን ባዮች ሕገመንግስቱ የተዋጣለት እንደሆነ ብዙ ጊዜ ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ አልፎ አልፎ ከምትሰማዋ አንቀጽ 39 በቀር ልዩ ሰነድ እንደሆነም ብዙዎች አድንቀዋል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ይሄ ሕገመንግስት የተዘጋጀውና የጸደቀው የተወሰኑ ቡድኖች ስለሚፈልጉት አንደሆነ እየታወቅ ከመጀመሪያው አንቀጸ ይጀምራል ክህደቱንና ውሸቱን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያጸደቁት በማለት፡፡  እባካችሁ  አንብቡት

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቢያንስ በኢትዮጵያዊነት ጽኑ እምነት ያላችሁ ሁሉ ከሆነ ዘር በተገናኘ ራስን የመፈረጅ አዙሪት ለመላቀቅ ሞክሩ፡፡ ኦሮሞ ኦሮሞ የሚል የኦሮሞን መብት ከሌላ በላይ አሳቢ መሆኑ ሳይሆን ሌሎች የፈጠሩለትን የዘር ጉሮኖ በራሱ ላይ እያጠረ ነው፡፡ በዛው ልክ በሌሎች ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታይ እየሆነ ነው፡፡ ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ በብዙዎች ዘንድ በጥሩ እንዳይታይ የሆነውም በዚህ አካሄድ ነው፡፡ ብዙም ትኩረት አድርጌ ስለኦሮሞ የምናገረው በግዝፈቱና በመልክዓምድራዊ አቀማመጡም ሌሎችን በማማከል በመሪነት ሊሰለፍ ሲገባው አንደ አንድ አናሳ ብሔረሰብ ሆኖ ስለሚታየኝ ነው፡፡ እዚህ ላይ የምናገረው በቁጭት እንጂ ብዙዎች ሌላ ትርጉም ሊሰጡት እንደሚፈልጉት አደለም፡፡ ኦሮሞ ነህ የተባለው ሕዝብ ከዚህች ኦሮሞ ከምትል ትንስ ጉሮኖ ውስጥ ራሱን ማውጣት አለበት፡፡ ይህ ምክር ለሌሎችም ይሰራል፡፡

ሁሉም በማስተዋል ይሁን! እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይታደግ! አሜን!

ሰርጸ ደስታ

 

የኦሮሞ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ሥልጣን ባለቤት ነው (ስህተት)