የሶማሊው ክልል መሪ አቶ አብዲ ሙሃመድ ከቀብሪበያህ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዲያስፖራ ቤተሰብ አባላትን አሰረ።

የሶማሊው ክልል መሪ አቶ አብዲ ሙሃመድ ከቀብሪበያህ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዲያስፖራ ቤተሰብ አባላትን አሰረ።

(ኢሳት ዜና ማጋቢት 04 ቀን 2010 ዓ/ም) እርምጃው የተወሰደው በውጭ ያሉ የዲያስፖራ አባላት በቅርቡ በሚካሄደው የሶህዴፓ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ለማስገደድና ለፕሬዚዳንቱ ድጋፋቸውን እንዲያሳዩ ለማስገደድ ነው። ከታሰሩት መካከል የ90 ዓመት አዛውንት ሳይቀር ይገኙበታል። በርካታ ወላጆች መታሰራቸውን ተከትሎ፣ ህጻናት ቀንና ሌሊት በጸሃይና በብርድ እንዲቀጡ እየተደረገ ነው።
ምንጮች እንደገለጹት በውጭ አገር የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ፕሬዚዳንቱ የሚፈጽመውን በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ጭፍጨፋና ስቃይ በፌስቡክ እያጋለጡ መምጣታቸውን ተከትሎ፣ ፕሬዚዳንቱ በአገር ቤት የሚኖሩ ወላጆቻቸውንና ዘመዶቻቸውን ሰብስቦ በማሰርና የዲያስፖራ አባላቱ ዘመዶቻቸውን ለማስፈፋት ሲሉ ይቅርታ እንዲጠይቁና ለአቶ አብዲ ድጋፋቸውን በአደባባይ እንዲገልጹ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው።
አቶ አብዲ ሚኒሶታ ውስጥ ሚኒሶታ ውስጥ በከፈተው ጽ/ቤት፣ ማንኛውም ዘመዱ የታሰረበት ዲያስፖራ ወደ ጽ/ቤቱ በመሄድ ለአቶ አብዲ የይቅርታ ደብዳቤ በመጻፍና ድጋፉን በመግለጽ እንዲሁም 2000 ሺ ዶላር በመክፈል የታሰሩ ዘመዶቹን ማስፈታት እንደሚችል እያስገደደና ገንዘብ እየዘረፈ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ።

ልጆቻቸው ውጭ አገር ካሉት ወላጆች በተጨማሪ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ የተማሩና ኢትዮጵያዊነትን ያቀነቅናሉ የተባሉት ሁሉ እየተያዙ ነው። “በክልሉ የሚፈጸመው በደልና ግፍ ይብቃ!” በሚል የክልሉ ተወላጆች የጀመሩን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ አቶ አብዲ ከፍተኛ በጀት መድቦ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንም ምንጮች ተናግረዋል። በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ጥቂት የተማሩና ለኢትዮጵያ አንድነት በመዋደቅ የሚታወቁት የአቶ አብዱላሂ ቤተሰብ አባል የሆኑት ዶ/ር ሃሰን አብዱላሂ በአቶ አብዲ ትዕዛዝ እንዲታሰሩ ከተደረገ በሁዋላ በእርሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው ነው።
ዶ/ር ሃሰን ላለፉት 9 ዓመታት በክልሉ ውስጥ ምንም አይነት ስራ እንዳይሰሩ ታግደው ከቆዩ በሁዋላ በቅርቡ በፕሬዚዳንቱ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የታሰሩ ሲሆን፣ የእርሳቸውና የዘመዶቻቸው ንብረት የሆኑ 2 ማደያዎችና መኖሪያ ቤቶች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲወረስባቸው ተደርጓል። ሆቴላቸውም አገልግሎት እንዳይሰጥ ታግዶ ተዘግቷል። ሰሞኑን ደግሞ በአቶ አብዲ የታዘዙ 4 የልዩ ሃይል አባላት ወደ ዶ/ር ሃሰን ባለቤት ቤት በመሄድ አስገድደው እንደሚደፍሯት እየዛቱ እያሰቃዩዋት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። የዶ/ር ሃሰን ባለቤት ጫናውን መቋቋም እንደተሳናት እና በእየቀኑ እያለቀሰች እንደምትገኝ ታውቋል።

አቶ አብዲ በፌስቡክ ትችት የሚጽፉ የዲያስፖራ አባላትንና እርሳቸውን ይቃወማሉ ብለው ያሰሩዋቸውን ቤተሰቦች ካሰሩ በሁዋላ ሴቶች ተገደው እንዲደፈሩ በማስደረግና ቪዲዮ በማስቀረጽ፣ በዲያስፖራ አባላትና በእስረኞች ላይ የስነ ልቦና ጫና እየፈጠሩና መረጃው እንዳይወጣ ከፈለጋችሁ ይቅርታ ጠይቁ፣ ገንዘብም ክፈሉ እንደሚባሉ ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
አንዳንድ የዲያስፖራ አባላትም ሳይወዱ በግድ የተጠየቁትና ገንዘብ መክፈላቸውንና ይቅርታ መጠየቃቸውን የገለጹት ምንጮች፣ ብዙዎቹ ግን “አናደርገውም” እያሉ ነው። በቅርቡ የሚደረገው ስብሰባ ዋና አላማ በውጭ የሚኖሩ የሶማሊ ክልል ተወላጆች ከህወሃት ጎን ቆመዋል ለማሰኘት የታለመ ነው፡፡
አቶ አብዲ የክልሉን ፖሊስ በማፈራረስ እርሳቸው የሚመሩት ልዩ ሃይል ክልሉን እንዲቆጣጠረው አድርገዋል። ይህን አሰራር አጥብቀው የተቃወሙት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ብ/ጄኔራል መሃመድ በአቶ አብዲ ትዕዛዝ ታስረው ከፍተኛ ስቃይ እየተፈጸመባቸው ሲሆን፣ እርሳቸው እንዲፈቱ የእርሳቸው የቅርብ ዘመዶች ይቅርታ እንዲጠይቁ ቢለመኑም፣ ቤተሰቦቹ ግን “ ግደሉት እንጅ ይቅርታ አንጠይቀም” ማለታቸው ታውቋል።
“የሶማሊ ነፍጠኞች ናቸው” ተብለው አገራቸውን በመውደዳቸው ብቻ የሚሰቃዩት የጂድዋቅ ጎሳ አባላትን ለመቅጣት አቶ አብዲ ውሃ እስከማቋረጥ ደርሰው እንደነበር ምንጮች አክለው ገልጸዋል።

አቶ አብዲ በዘመዶቻቸው ላይ የሚፈጽመውን ግፍ በተመለከተ የሶማሊ ክልል ተወላጆች እስከ ጠ/ሚኒስትሩ ድረስ ደብዳቤ ቢጽፉም ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም። የዶ/ር ሃሰን ቤተሰቦችም በተመሳሳይ ሁኔታ ደብዳቤዎችን ጽፈው ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ቢያሳውቁም ምንም መልስ ሊያገኙ አልቻሉም። የፌደራል ባለስልጣናት በአቶ አብዲ ላይ ምንም ስልጣን እንዲሌላቸው እየገለጹ ሲሆን፣ እርሳቸው በከፍተኛ ገንዘብ የያዙዋቸው የህወሃት ጄኔራሎች ከጀርባ ድጋፍ እየሰጡዋቸው ፕሬዚዳንቱ የፈለጉትን እያደረጉ ነው ሲሉ ለጠየቁዋቸው ሰዎች መናገራቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
አቶ አብዲን ትዕዛዝ እየተቀበሉ የማሰርና የማሰቃየቱን ስራ የሚሰሩት ብ/ጄኔራል አብዱልራህማን ላ ባ ጎሌ መሆናቸውንም ምንጮች ተናግረዋል፡፤

The post የሶማሊው ክልል መሪ አቶ አብዲ ሙሃመድ ከቀብሪበያህ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዲያስፖራ ቤተሰብ አባላትን አሰረ። appeared first on ESAT Amharic.

የሶማሊው ክልል መሪ አቶ አብዲ ሙሃመድ ከቀብሪበያህ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዲያስፖራ ቤተሰብ አባላትን አሰረ።