አገርን ከውድቀት የታደጉ መሪዎቻችንን አሁንም እንርዳቸው! (ሰርፀ ደስታ)

ያገሬ ልጆች(ኢጆሌ ቢያ) እንዴት ናችሁ? ከልባችሁ ሆናችሁ ለአገራችሁ የተጨነቃችሁ፣ የጸለያችሁ የየበኩላችሁን ያበረከታችሁ ሁሉ አሁን እግዚአብሔርን እያመሰገናችሁ ቀጣዩን ሂደት በትኩረት እንድትቀጥሉ እጠይቃለሁ፡፡ አሁን ያለንበት የተስፋ ጎሕ ከ7-8 ወር በፊት ፍጹም የማይታሰብ ድቅድቅ ጨለማ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ከ3000 ዓመት በላይ የኖረች አገር ትጠፋ ይሆን ሕዝባችንስ እርስ በእርሱ ይተላለቃል ብለን እጅግ የተጨነቅን ብዙዎች ነን፡፡ ሴረኞች ይህ እንዲሆን ያላቸውን ሁሉ ሞክረዋል፡፡ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት በገዛ አገራችን መዋቅር ሰርተው 27 ሲያሴሩ እኛ ተኝተን ነበር፡፡ በመጨረሻም ወደእልቂት እንድንገባ በቻሉት ሁሉ ሞከሩ፡፡ ሴራቸው ሁሉ ግን ተገልብጦ ለእኛ መፈቃቀርና አንድነት ለአገራችንም ወደሰላም መንገድ በር ከፋች ሆነ፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ነው፡፡ ሰው በአሰበውማ ከሆን ምኑን የእግዚአብሔር ሥራ ተገለጠ፡፡ ለማ መገርሳ ሰሞኑን አልነበረም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ማለት የጀመረው፡፡ ገና ወደ ኦሮሚያ ፕሬዘዳንትነት ሲመጣ ነበር ስለ አገር አንድነትና ኢትዮጵያዊነት እቅጩን የተናገረው፡፡ በወያኔና ኦነጋውያን ጥምር ሴራ የተከፋፈለንና በተለይም ደግሞ ከአገር ባለቤትነቱ አውጥተው በገዛ አገሩ ስደተኛ ለሆነው ብዙ የኦሮሞ ሕዝብ የለማ ፍልስፍና ሁሉንም ቆም ብሎ ራሱን እንዲያይ አድርጓል፡፡ ለማ ከመጀመሪያውም በዚህ መልኩ ቢመጣም ፈተናዎች ግን እጅግ እየከፉ ሄደው ነበር፡፡ እርግጥ የአንድነቱ ደወል የመጀመሪያው ደዋይ የጎንደር ሕዝብ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ የወያኔንም ሴራ ይፋ ያደረገው ይሄው ደወል ነበር፡፡ ይገርማል ሕዝብ እንዴት አንድ ይሆናል ብሎ ለሕዝቦች መበታተንና መተላለቅ የሚሰራ የመንግስትነት ጭምብል አጥልቆ 27 ዓመት አገርንና ሕዝብን አንድ በአደረጉ አባቶች ቤተመንግስት ኖረ፡፡ የጎንደሩን ጥሪ የተቀበለው የኦሮሞ ሕዝብ ቀጠለ፡፡ ሆኖም ይህን ግንኙነት መልሶ ለማቋረጥ ወያኔ ከአጋሮቿ ጋር ብዙ ሞከረች፡፡ ሁላችንም የሆነውን ሁሉ በትኩረት እናስታውስ፡፡ እነለማ ባይመጡ ወያኔና አጋሮቿ ሊሳካላቸው ይችል ነበር፡፡

የለማን ቡድን ለዚህ ጥንካሬው ያበቃው የሕዝብ ግፊት ነው ማለት የለማንና ቡድኑን ጥረትና ውለታም መዘንጋት እንዳይሆን፡፡ ለማ የሕዝቡ ችግርና ሰቆቃ ስለገፋው ሳይሆን ሞትም ከአለ ከሕዝቤ ጋር እንዲል እልህ ውስጥ ያስገባው ነው ሆኖ እኔ ያገኘሁት፡፡ ሁኔታዎችንም በትኩረት እከታተል ነበር፡፡ ለማና ቡድኑ ባይኖሩ የሶማሌና ኦሮምያ አዋሳኝ ግጭት ወደ ለየለት እርስበእርስ መተላለቅ ይቀየር ነበር፡፡ ለማና ቡድኑ ባይሆኑ የቡኖ በደሌው ሴራ ራሱ በአገር አቀፍ ደረጃ የሆነን እርስ በእርስ መተላለቅ በፈጠረ፡፡ እነለማ እጅግ ብዙ መከራዎችን ነበር የተጋፈጡት፡፡ ሕግ የማያውቅ ወንበዴ ቡድን መንግስት ሆኖ በአለባት አገር የሆነው ሁሉ ሆነ፡፡ ትዕግስትና ብስለት ወሳኝ ሚና ነበራቸው፡፡ ይሄን ነበር ለማና ቡድኑ የተጋፈጡት፡፡ እዚህ ላይ ለማና ቡድኑ ስል እነገዱንም እዚሁ ላይ ልደምራቸው፡፡ መደመርን አደል ጠ/ሚኒስቴራችን በአጽኖት እንድንተገብር የነገሩን? አዎ ላለፉት በርካታ ወራት በበአዴንና ኦህዴድ የተለዩ መሪዎች ምክነያት ነው አገራችን ዛሬ ላለንበት ተስፋ የደረሰቸው፡፡ እንደወንበዴዎቹ ሴራ ከሶሪያና ሊቢያም የከፋ አደጋ ውስጥ በገባን፡፡ እነዚህን የኦሕዴድና በአዴን መሪዎች በዚህ ሰዓት እግዚአብሔር ያስነሳውም ከ3000ዓመት በላይ ስሙን ስትጠራ የኖረችን አገር አስቦ እንደሆነ አስተዋልኩ፡፡ 3000 ዓመት በላይ ስል አሁንም አንዳንዶች ይሸክካቸዋል፡፡ ይህን እውነት ግን እኛ ብንዘነጋውም እግዚአብሔር ያውቀዋል፡፡ ሌሎችንም ይህን እውነት መዝግበው እንዲያቆዮ በእኛም (ዛሬ ለሚሸክከን)ምስክር እንዲሆንብን ብዙዎች ቀድመው ጽፈውታል፡፡ መጻፈቅዱስና ቁርዓን ሳይቀሩ ይህን እውነት ጽፈውታል፡፡  እስኪ ከመጻፈ ቅዱስ ጥቂት ምሳሌ ላንሳ

 • ዘፍጥ 2፡13:- የሁለተኛውም ወንዝ ሥም ጊዮን(አባይ) ነው፡፡ እሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከባል
 • መዝ 87፡4፡- ኢትዮጵያ እጆን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች
 • ኤር 13፡23፡- ኢትዮጵያዊ (አበባ)መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ሊለውጥ ይችላልን
 • አሞጽ 9፡7፡- የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን ይላል እግዚአብሔር (

ከእስራኤል በፊት ኢትዮጵያውያን የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊው የሙሴ አማት ካህን ነበር፡፡ ይህ ሰው ግን ከእስራኤል ወገን አደለም፡፡ ሌሎች ጥንታዊ ጸሀፍትም ይህን እውነት ሲመሰክሩት እናያለን፡፡ ለምሳሌ

 • ኢትዮጵያ መጀመሪያ የተመሠረተ አገር(መንግስት)
  • Stephanus Byzantinus (Greece, 6th century BC)
 • ኢትዮጵያዊያን የመጀመሪያዎቹ የሥነከዋክብት ተመራማሪዎችና የፕላኔቶች ሰያሚዎች
 • ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያዎቹ በሰማይ አምላክ የሚያመልኩ ሕዝቦች
  • Diodorus Siculus  (Greece 90-21BC)
 • ኢትዮጵያ የሥልጣኔ መሠረት ከግብጽም፣ ግሪክም በፊት John G. Jackson (1939)

የዘመናዊው ሳይንስ የመለዘር ጥናት ውጤትም ዛሬ ላይ እየመሰከረ ያለው ይሄንኑ ተጽፎም እኛ ግን በሴረኞች ሴራ ተመርተን ተረት ነው ያልነውን እውነት ነው፡፡ ምን ሆነን ይሆን ወደዚህ የመጣንው፡፡ ለግንዛቤ ያህል ይበቃችኋል፡፡ወደ ተነሳሁበት፡፡

እነለማ ዛሬ አገሪቱን በሚገርም ፍጥነት ወደ ነበረችበት እየመለሱ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስቴራችን ከተሾሙ በቀናት ውስጥ ለ27 ዓመት ስትፈርስ የነበረችን አገር ሕዝቦቿን  ወደ እውነተኛ ማንነታቸው እንዲመለሱ ይሄው ጀምረውታል፡፡ እግዚአብሔርም ይረዳዋል፡፡ ዛሬ ከወንበዴዎች ተላቃ ኢትዮጵያ በልጆቿ እጅ እየገባች ነው፡፡ ግን ገና ብዙ ይቀራል፡፡

ኤች አር 128 ጸደቀ! ጥሩ ነው፡፡ ቢዘገይም ጥሩ ነው፡፡ ለአዲሱ ጠ/ሚኒስቴራችን ጥሩ ግብዓት ነው፡፡ ወንበዴዎቹን የሚያስርና የዘረፉትን ንብረትም በየትም አገር እንዳይንቀሳቀስ የሚያደርግ ሕግ ቀጣዩ ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ አሁንም ማስተዋል የሚያስፈልጉን ጉዳዮች አሉ፡፡ ከውስጣችን ሁሉንም ነገር ያለማፈር በድፍረት ልናወጣው የሚገባ መርዝ አለ፡፡ አሁንም ወያኔና ኦነጋውያን እንዲሁም ሌሎች የ60ዎቹ ሴረኛ ቡድኖች አያርፉም፡፡ አንድ ነን መባባላችን ለወሬ አደለም፡፡ እንዲህ ያለው እንድነት ሊቀር ይገባል፡፡ በመተሻሸት የኖርንባቸው የውሸት መሞካሸቶች ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል፡፡ በትላንትናው እለት የኦነግን ባንዲራ የያዙ ግለሰቦች ከኢትዮጵያውያን ጋር ቆመው ታይተዋል፡፡ እርም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ አውጡ፡፡ ኦነግ ከወያኔ ያልተናነሰ የሕዝብና አገር ጠላት እንደሆነ አሳምረን እናውቃለን፡፡ ይህን በየትኛውም ሁኔታ እድል ልንሰጠው የምንችለው ጉዳይ አደለም፡፡ ኦነጋውያን አሁንም ኦሮሚያ የምትባል አገር እንጂ ኢትዮጵያ የምትባል አገር የለቻቸውም፡፡ ለመሆኑ የማን አገር ባንዲራ ያዝኩ ሊሉ ነው የኦነግን ባንዲራ የያዙት፡፡ ልብ በሉ ይህ የፓርቲ ባንዲራ አደለም፡፡ ሰዎች ተሰልፈው የነበሩት ስለአገር ጉዳይ እንጂ ስለፓርቲም አደለም፡፡ ኦነግ ሁሌም ኦነግ ነው!! ከወያኔ ያልተናነሰ ጨካኝ! እርግጥም ሁሌም እንደምለው ኦነግና ወያኔ በውስጥ ውል አላቸው፡፡ እንዘናጋ፡፡ ኦሮሞ የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን ግንባር ቀደም ሆናችሁ ይህን ልትዋጉ ያስፈልጋል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት መክኖ ከሌሎች ሁሉ እንደ ጠላት እንዲታይ ወያኔና ኦነግ በሕብረት ሲሰሩ ነበር፡፡ ይህ እውነት ለብዙው አሁንም አልገባውም፡፡ ያልተፈጠረ ታሪክ እያወሩለት ከእውነተኛ ታሪኩ ሕዝቡን አውጥተው ለራሳቸው ባሪያ አድርገውት ኖረዋል፡፡ ይህን አስተውሉ፡፡ ሌላው ለኦሮምኛ ተናጋሪዎች (ማንም ሊሆን ይችላል) በአማርኛ ሲያወሩ ቅዱስ የሚሆኑ በኦሮምኛ ግን ብዙ ያልተገባ ነገር የሚናገሩትን ፊት ለፊት ተጋፈጧቸው፡፡ ይህን እድል ለሴረኞች መስጠት የለብንም፡፡ በቆይታ የእነሱ ሴራ ወደሌሎች ይዛመታልና፡፡ ይህን ብዙም ባይባል አሁንም በአማርኛ ሲያወሩ ቅቤ በኦሮምኛ ግን ሌላው አይሰማውም በሚል ይመስላል ሴራቸውን የሚነዙ አሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ቀልድ የለም፡፡ ምንም ለምነን ኢትዮጵያዊ ሁን አንለውም፡፡ ኢትዮጵያ ግን የኢትዮጵያዊያን እንደሆነች ልናሳውቀው ይገባል፡፡

ዛሬ ጠ/ሚኒስቴር አብይ በኦሮምኛ ተናገረም ተብሎ እንደ ልዩ ነገር ሲወራ አይቻለሁ፡፡ እና ለአንቦ ሕዝብ በምን ያውራ? መለስ ለመቀሌዎች በምን ነበር የሚያወራው? ኦሮምኛ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን እኮ ነው እየተነገርን ያለንው፡፡ ለነገሩ ይሄን ያህል ዘመንም የቆየው ሴረኞች ለሴራቸው እንዲመቻቸው እንጂ  ኦሮምኛ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን እኮ የኃይለሥላሴ በመጨረሻ እድሜያቸው በአዘጋጁት ሕገመንግስት ጸድቆ ነበር ነው የሚባለው፡፡ እኔ አላነበብኩትም ግን ብዙዎች የሚመሰክሩት እውነት ነው፡፡ ሰነዱም ከተገኘ ማየት እንችል ይሆናል፡፡  ጉዳዩ ግን የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ሳይሆን በሕዝብ ችግር ራሱን ትልቅ አድርጎ የሚቆምረው የ60ዎቹ ትውልድ ነው ነገሮችን ሁሉ የአበላሸው፡፡ ለማንኛውም እንኳን አብይ ቀጥሎ ገዱም በኦሮምኛ ለአምቦዎች ንግግር ሊያደርግ ይችላል፡፡ እንዲህ ትንንሽ ነገሮችን ትልቅ ትኩረት እንዲሰጣቸው ለማድረግ የሚሞክሩት እነማን እንደሆኑ እናስተውል፡፡

በነገራችን ላይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተግባር አሁን የለም ግን በአስቸኳይ ጠ/ሚኒስቴራችን ፓርላማቸውን ጠርተው በአዋጅ እንደሚያሽሩት እንጠብቃለን፡፡ የወንበዴዎቹንም ብዙ ሕግ ሆነው የወጡ ሕገ ወጥ ሕጎች እንዲሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ሥልጣንም ሆነ ኃይል ከኢትዮጵያውያን እጅ እንዳይወጣ ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ተቃዋሚ የተባሉትም ይህን አስበው ይግቡበት፡፡ ተፎካካሪ ለመሆን ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነት ዋና መስፈርት ነው፡፡

አገሪቱስ አሁን ያለንበት ተስፋ ላይ ነች እግዚአብሔር ደግሞ መጨረሻውን ያሳምርልን፡፡ ለ27ዓመት የጥፋት ዘሮች የመሸጉባቸው የመንግስት መዋቅር ብቻ ሳይሆኑ የእምነት ተቋማትም ናቸው፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ግን የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ቤትክርስቲያን  የወንበዴዎች ሰለባ ሆናለች፡፡ በሙስሊሙ ማህበረሰብም ቀላል የማይባል ፈተና እንዳለ እንረዳለን ግን በዝርዝር አላውቀውም፡፡ የኢትዮጵያዊቷ ቤተክርስቲያን ግን ከሁሉም የከፋ ነው፡፡ ከእምነቱ ሥርዓት ውጭ ሁለት ሲኖዶስ፣ ፓትሪአርክ፣ ሌላም፡፡ አልፎም የእከሌ ብሔረሰብ ቤተክርስቲያን የከሌ ብሔረሰብ እሰከማለት ተደርሶ ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ መቼም ጉድ ሳይሰሙ ነውና የቤተክርስቲያኗን ገንዘብ የባንክ ሼር ሊገዙበት ነው ተብሎ ወሬው ጦፏል፡፡ እኔ እዚህ አካባቢ ያለውን ነገር ብዙም ባልል እመርጣለሁ፡፡ ከእኔ የተሻለ ሚስጢሩን የሚያውቁ ስላሉ፡፡ የተባለው እውነት ከሆነ ግን ቀኖናዊ ሳይሆን ዶግማዊ ስህተት ነው የሚሆነው፡፡ ከንግድም ወለድ የሚቀበል ባንክ ሥራ፡፡ ሲጀምር ቤተክርስቲያኗ ከየትኛውም ንግድን ብቻ መሠረት ከአደረጉ ሥራ መለየት አለባት፡፡ መሳተፍ ከአለባት ለማሕበረሰቡ እገዛ በሚየደርጉ እንደ ት/ቤት፣ ጤና ተቋማት የመሳሰሉ አገልግሎቶች ላይ ነው፡፡ ይህ ወገንን ከመጥቀም ጋር ብዙ ሚና አለውና፡፡ ብቻ ያስፈራል፡፡ እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልፈለጉት መጠን የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው የሚለው ቃል እየተፈጸመ ነው የሚመስለው፡፡ ዛሬ ገንዘብ ከተገኛ ምን አለበት በሚል ድፍረት ትልልቅ አሳዛኝ ክህደቶች እየተፈጸሙ ይመስላል፡፡

እግዚአብሔር አገራችንንና ሕዝባችንን ይጠብቅ! አሜን!

The post አገርን ከውድቀት የታደጉ መሪዎቻችንን አሁንም እንርዳቸው! (ሰርፀ ደስታ) appeared first on ሳተናው: Ethiopian News|Breaking News: Your right to know!.

አገርን ከውድቀት የታደጉ መሪዎቻችንን አሁንም እንርዳቸው! (ሰርፀ ደስታ)