ሃውስ ሪዞሉሽን 128(HR 128) በተጨባጭ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ‘ምን ለውጥ ያመጣል?

ሃውስ ሪዞሉሽን 128(HR 128) የተባለው ረቂቅ ሰነድ በአሜሪካ ኮንግረስ መፅደቁን ተከትሎ፣ ውሳኔው በተጨባጭ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ‘ምን ለውጥ ያመጣል?’ የሚለው ጉዳይ ዋናው የውይይት አጀንዳ ሆኗል።

ጉዳዩ የአንዲት ሉዓላዊት አገርን እጅ መጠምዘዝ አድርገው የሚመለከቱት እንዳሉ ሁሉ ፣ማንኛውም የውስጥና የውጭ ግፊት የለውጥ መንገድን ማፋጠኑ ስለማይቀር ሊደገፍ ይገባል ብለው የሚከራከሩ በርካታ ናቸው።

በስልጣን ላይ ያለውን መንግሥት የሚቃወሙ ሆነው ነገር ግን ለውጥ ከውስጥ እንጂ ከውጭ ሊመጣ አይችልም የሚሉ ወገኖች ፣በኃያላን አገራት ተፅዕኖ የሚመጣ ዲሞክራሲ እንደሌለና ቢኖርም ውጤቱ አፍራሽ ነው ብለው ይሞግታሉ። እነዚህ ወገኖች በቅርቡ የታየው የለውጥ ተስፋ ከየትም ሳይሆን ከሕዝብ ተሳትፎ የመጣ እንደሆነ ያሰምሩበታል።

በተለይም አገሪቱ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በሾመች ማግስት ይህ ውሳኔ መምጣቱ የለውጥ በሮችን የማጥበብ ያህል አድርገው ያዩታል። ውሳኔው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለለውጥ የሚኖራቸውን ጉልበት ያሳጣቸዋል ብለው የሚሰጉም በርካቶች ናቸው።

ከዚህ በተቃራኒ የረቂቁ መፅደቅ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የገቧቸው ቃሎች ባዶ ሆነው እንዳይቀሩ የሚያደርግ፣ ለሕዝብ የገቡትን ቃል ለመተግበር እንደ ድርጊት መርሀ ግብር የሚሆን ውሳኔ ነው የሚሉም አሉ።

ውሳኔው ድምፅ ሊሰጥበት ሰዓታት ሲቀሩ፣ የኦክላሆማ ግዛት ሴናተር ጂን ኢንሆፍ ለእንደራሴዎች በላኩት መልዕክት ረቂቁ እንዳይፀደቅ በጥብቅ መማፀናቸው ረቂቱ ውደቅ ሊደረግ ይችላል የሚለውን ስጋት ከፍ አድርጎት አምሽቶ ነበር።

ሴናተሩ ለሸንጎው አባላት በላኩት መልዕክት ፣የአዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የግል ወዳጅ ስለመሆናቸው፣ ብሎም አብረው ስለ ኢትዮጵያ መፀለያቸውን ጭምር ጠቅሰው ፤ ላለፉት 20 ዓመታት ኢትዮጵያን ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ያልጎበኙበት ወቅት እንዳልነበረና በየጊዜው በዚያች አገር ለውጥና መሻሻል እንደሚመለከቱ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት የሰጡት ቃል ለመተግበር የሚያስችላቸውን ዕድል ካለ ጣልቃ ገብነት ሊታገዙ እንደሚገባ አስረድተዋል። የዚህ ረቂቅ መፅደቅ ግን አሉታዊ ውጤት ስለሚኖረው ባልደረቦቻቸውን ረቂቁን እንዳያፀድቁ ተማፅነዋቸዋል።

በአሜሪካ የኢትዯጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ገብረሕይወት በበኩላቸው ረቂቁ እንዳይፀድቅ በፃፉት ደብዳቤ ፣ረቂቁ የሁለቱን አገራት መልካም ግንኙነት እንደሚጎዳ አሳስበው ነበር። ይህን ረቂቅ አምባሳደሩ «ያልተገባና ጊዜዉን ያልጠበቀ» ሲሉም ነው የገለጡት።

አገሪቱ ወደ አዲስ ምዕራፍ በምታልፍበት ጊዜ ፣ጉልህ ማሻሻያዎችን በማድረግ ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ መስመር በመያዝ እየተጋች ባለችበት ወቅት፣ ይህን ሕግ ማፀደቅ ያልተፈለገ መዘዝና ተቃራኒ ውጤትን የሚያመጣ ሊሆን እንደሚችልም አስጠንቅቀው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ይህ ሰነድ መፅደቅ ምንም አይነት አስገዳጅ ሀይል እንደሌለውም የፖለቲካ ተንታኞች ይገልፃሉ።

የውሳኔው ይዘት፡ –

•የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ጥሪ ያቀርባል

•ግድያና ተመጣጣኝ ያልሆነ የፀጥታ ኃይሎች እርምጃን ያወግዛል፤

•በመንግስት አካላት ተፈፀመዋል የሚባሉ የመብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ ይጠይቃል፤

•ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ እንደመጣ የሚነገረው የፖለቲካ ብዝሀነትና ምህዳር እንዲሰፋ ይጠይቃል፤

•በፀረ- ሽብር ትግሉ የአሜሪካ ሸሪክ በሆነችው ኢትዯጵያ ላይ የሚሰጠው የልማት እርዳታና የፀጥታ ትብብር ድጋፍ በድጋሚ እንዲጤንም ይጠይቃል፤

•የጉዞ የገንዘብና የንብረት እቀባ በሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ ተሳትፎ አላቸው በሚባሉ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ እንዲጣልም ይወተውታል፤

•በእስር ላይ የሚገኙ የመብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ግፊት ያደርጋል።

ሃውስ ሪዞሉሽን 128(HR 128) በተጨባጭ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ‘ምን ለውጥ ያመጣል?