ትዕምርታዊ እርምጃ! (የሱፍ ያሲን )

የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ‹ኤች.አር 128› የተሰኘውን የውሳኔ ሐሳብ (resolution) ባለፈው ማክሰኞ ሚያዚያ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. አፅድቋል፡፡ ምክር ቤቱ ያፀደቀው የውሳኔ ሐሳብ ከሚያካትታቸው አንኳር ፍሬ ነገሮች መካከል፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ፤ የፀረ ሽብር ሕጉ እንዲሻር፤ የዜጎችን የመሰብሰብና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲከበር፤ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በተቃውሞ ወቅት የተገደሉ ሰዎች ጉዳይ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ፤ በቂሊንጦ በእሳት ቃጠሎና በጥይት ስለተገደሉት፣ በእሬቻ በዓል ላይ ስለሞቱትና በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ስለተፈፀመው ግድያ ምርመራ ተካሂዶ ሪፖርት እንዲደረግ፤ ሁሉም የፖለቲካና የኅሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፤ ሠላማዊ ሰዎችን የገደሉ፣ ያሰሩ፣ ያሰቃዩ (ቶርቸር የፈፀሙ) አካላት በሙሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መምሪያ እና የገንዘብ ሚኒስቴር በግድያ፣ በማሳቃየት (ቴርቸር በመፈፀም)፣ የዜጎችን ሰብአዊ ክብር በመጣስ ወንጀል የሠሩ ሰዎችንና ድርጅቶች ላይ ተገቢውን ማዕቀብ እንዲያደርጉ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለልተኛ የሆነ ምርመራ ማካሄድ እንዲችል እንዲፈቀድለት፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መምሪያ (የአሜሪካ መንግሥት) ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የፀጥታ ዕርዳታ በድጋሚ እንዲያጤን እና ክትትል እንዲያደርግ፤ የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን በመጠቀም የሚያደረገውን ትግል እንዲደግፍ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የውሳኔ ሐሳቡ መፅደቁን ተከትሎ በተቃውሞው ጎራ ትልቅ የደስታ ስሜት ሲንፀባረቅ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በገዥው ግንባር ደጋፊዎች በኩል ከፍ ያለ የሐዘንና የቁጭት ስሜት ይታያል፡፡ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጊዜ እንስጣቸው፤ የውሳኔ ሐሳቡ እንዲፀድቅ መደገፍ ለውጥን መቃወም ነው ያሉ ወገኖችም አልታጡም፡፡ ለመሆኑ የውሳኔ ሐሳቡ መፅደቅ በኢትዮጵያና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ምን አንድምታ አለው?

እኛ እና አሜሪካ
***
ሕወሓት/ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም. መንበረ ሥልጣኑን እንዲረከብ የአሜሪካ መንግሥት የተጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የዚያን ጊዜው የሕወሓት/ኢሕአዴግ ወዳጅ የዛሬ ተቃዋሚ ሄርማን ኮኸን ለአገዛዙ ምን ያህል ድጋፍ እንዳደረጉ፣ ፕሬዚዳንት ክሊንተን አቶ መለስ ዘናዊን፣ አቶ ኢሳያስ አፈውርቂን፣ ዩዌሪ ሞሴቬኒንና ፖል ካጋሚን ‹አዲሶቹ ዴሞክራቶች› በሚል የቁልምጫ ቃል እየጠሩ ምን ያህል እንደደገፏቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

አቶ መለስ በተለይ ከአሜሪካው ዴሞክራቲክ ፓርቲ እና ከፓርቲው የተወሰኑ ሰዎች ጋር ቤተሰባዊ ሊባል የሚችል ግንኙነት ፈጥረው ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ የነበሩት ዋሕደ በላይ በአንድ አጋጣሚ “መለስ ወደ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ መምሪያ ሳይሆን በቀጥታ ወደ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ደውሎ ሁሉንም ነገር ይጨርሰዋል፤” ብለው በእርግጠኝነት ስሜት እንዳጫወቱን አስታውሳለሁ፡፡ እንደ ሱዛን ራይስ፣ ጀንዳይ ፍሬዘርና ጆኒ ካርሰን ያሉ ባለሥልጣናት፣ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እንደ መለስ ዜናዊ ያለ ባለራዕይና እንደ ኢሕአዴግ ያለ ጠንካራ ድርጅት ስለሌለ አቶ መለስንና መንግሥታቸውን ማስከፋት የለብንም እያሉ ለኢትዮጵያ መንግሥት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችንና ጋዜጠኞችን ሲያዋክብ፣ ሲያስርና ሲያሳድድ እያዩ እንዳላዩ አልፈዋል፡፡ እንደ አምባሳደር ቪኪ ሃድልስተን ያሉት ደግሞ ከኢሕአዴግም በላይ ኢሕአዴግ ሆነው በኢትዮጵያዊያን ላይ ወንጀል ፈፅመዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በበኩላቸው ስለ ሰብአዊ መብት መከበርና ስለ ዴሞክራሲ ይናገራሉ ሲባል፣ ይግረማችሁ ብለው፣ ኢሕአዴግ በዜጎች ላይ ሲፈፅመው የኖረውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ወደጎን በማለት፣ አገዛዙ “በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥት” (democratically elected government) መሆኑን “ገልፀውልን” ሄደዋል፡፡ የፕሬዚዳንት ኦባማ ድርጊት እንኳን በአፈና ሲሰቃዩ ለከረሙት ኢትዮጵያዊያን ለራሳቸው ለሕወሓት/ኢሕአዴግ ሰዎችም ያልተጠበቀ ስለነበር የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ “ከጠየቅነውና ከጠበቅነው በላይ ነው ያገኘነው” እስከማለት ደርሰዋል፡፡

ኢሕአዴግ አፋኝ መሆኑን በሚገባ እያወቅነው የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊዎች (ብዙዎች ጥቁሮችና ሴቶች ናቸው) በተደጋጋሚ “ዴሞክራሲያችሁ እያደገ ነው፤ ዴሞክራሲ ሂደት ነው፤ ታገሱ፤” ሲሉን መክረማቸው ሳያንስ ፕ/ር ባራክ ኦባማ ለኢሕአዴግ “በዴሞክራሲ የተመረጠ መንግሥት” የሚል ሽልማት ሰጥተው በሕዝባችን ላይ ቀልደዋል፡፡

በዚህ ሠላም በራቀው የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ውስጥ እንደ ኢሕአዴግ ያለ የአሜሪካና አጋሮቹ ቁርጠኛ አገልጋይ ባለመገኘቱ ምክንያት ግንባሩ የኃያላኑን በተለይም የአሜሪካን አጋርነት አትርፎ ቆይቷል፡፡ እስካሁን እንደታየው ኢሕአዴግም አሜሪካውያንን አስከፍቶ አያውቅም፡፡ እነሱም የሚፈልገውን አጉድለውበት አያውቁም፡፡ ከጦር መሣሪያ እርዳታ እስከ ዲፕሎማሲ ድጋፍ ሁሉም ሲሟላለት ቆይቷል፡፡ ወደፊትም ቢሆን አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ መሥራቷን አታቆምም፡፡ ከኢሕአዴግ ውጪ አማራጭ ስለሌለ እሱን እያስታመምን እንቀጥል የሚለው አሠራር ግን ያለ ጥርጥር ተቀይሯል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት (አዲስ አበባ በሚገኘው ኢምባሲው በኩል) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደሚቃወም መግለፁ፣ በቅርቡ ሥልጣናቸውን የለቀቁት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቴለርሰንም የኢምባሲውን መግለጫ በሚያጠናከር መልኩ፣ “ለኢትዮጵያዊያን ብዙ እንጂ መጠነኛ ነጻነት በመስጠት መፍትሔ ይመጣል ብለን አናምንም” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የወቅቱ የአሜሪካ መንግሥት አቋም ኢትዮጵያዊያን ላለፉት 27 ዓመታት ሲያቀርቡት የነበረው ጥያቄ መልስ ማግኘቱን የሚገልጽ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያዊያን “ለአፋኙ ሥርዓት መጠነ-ሰፊና ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረጋችሁ መከራችንን አታክብዱት፣ ለዴሞክራሲና ለሰብአዊ መብት መከበር ያላችሁን ቁርጠኝነት በተግባር አሳዩን …” እያሉ ያለመታከት ጮኸዋል፡፡ የ‹ኤች.አር 128› መፅደቅ ያ ያልተቋረጠ ጩኸት ፍሬ ማፍራት መጀመሩን በግልጽ ያሳያል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት አቋም እየተቀየረ መምጣቱን የተገነዘቡት የሕወሓት/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በከፍተኛ የመደናገር ስሜት ውስጥ እርስ በርሱ የሚምታታ አስተያየት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

‹አለቃችን ሕዝባችን ነው›
***

የኢትዮጵያ መንግሥት የውሳኔ ሐሳቡ እንዳይፀድቅ የታወቁ ወትዋቾችን (lobbyists) ቀጥሮ ከፍተኛ ተጋድሎ እንዳደረገ ተግልጿል፡፡ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ካሳ ተክለ ብርሃንና ጓዶቻቸው የውሳኔ ሐሳቡ እንዳይፀድቅ ያለ የሌለ አቅማቸውን ቢጠቀሙም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ “አለቃችን ሕዝባችን ነው፤ ማንም በውስጥ ጉዳያችን ገብቶ እንዲህ አድርጉ እንዲያ አታድርጉ ሊለን አይችልም ወዘተ.” የሚለው አነጋገር የመጣው አሁን ነው፡፡

የውሳኔ ሐሳቡ ከፀደቀ በኋላ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “እርምጃው የሁለቱን አገሮች የረዥም ዘመን ወዳጅነት እና ኢትዮጵያ እየወሰደችው ያለውን የለውጥ እርምጃ ከግምት ያላስገባ፣ ይልቁንም አዲሱ ጠቅላይ ሚነስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለሕዝባቸው የገቡትን ቃል ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው፤” ሲል ገልጿል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፣ “ኤች. አር 128 በአሜሪካ ኮንግረስ መፅደቁ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለን አንጠብቅም፡፡ የእኛ አለቃችንና ጠያቂነታችን ሕዝባችንና ሕዝባችን ብቻ ነው፡፡ ሕዝባችንን በማደናገር፣ የውሳኔ ሐሳቡ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል በማለት የሚያራግቡ አካላት አሉ፡፡ ሆኖም ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም፤ የሁለቱ አገሮች ግንኙነትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፤” በማለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

የሕወሓት/ኢሕአዴግ ደጋፊ የሆኑ ጽንፈኛ ድረ-ገጾች በበኩላቸው እነ ዶ/ር ነገሪ ከሰጡት አስተያየትም አለፍ ብለው፣ “ኢትዮጵያ ከቻይናና ሩሲያ ጋር አጋርነቷን ማጠናከር አለባት፤ ለኢምፔሪያሊስት እጅ ጥምዘዛ አንንበረከክም፤ የዲያስፖራው አካሄድ ኢትዮጵያን ለኒዮ-ሊብራሎች ቅኝ ግዛትነት አሳልፎ የሚሰጥ አገርን የመክዳት አካሄድ ነው፤” ወዘተ. እያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት ላይ ናቸው፡፡ ማን የውጭ ኃይሎች ጉዳይ አስፈጻሚ እንደሆነ፣ ማንስ የአገሩን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ እንደሚሰጥና የሕዝቡን ክብር እንደሚያዋርድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡

ኢሕአዴጋዊያን እንደሚሉት አለቃቸው ሕዝብ መሆኑን ከምር አምነው ሕዝብን ቢያገለግሉ፣ የዜጎችን ሰብአዊ መብት ባይጥሱ፣ ባይገድሉ፣ ባያስሩ፣ በኢትዮጵያዊያን ላይ ስቃይ (ቶርቸር) ባይፈፅሙ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ ባያሽመደምዱ፣ ጋዜጠኞችንና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ባያሳድዱ ወዘተ. ከገዛ ሕዝባቸው ጋር በዚህ ደረጃ ባልተራራቁ ነበር፤ የአገራችን ገጽታም እንዲህ ባልከፋ ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን ከኢሕአዴግ አመራሮች የሚጠበቀው ቁም ነገር የራስን ቤት ማሳመር፣ ለሐቀኛ ለውጥ ራስን ማዘጋጀት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚኖርባትን አገር ለመገንባት ቆርጦ መነሳት፣ በዜጎች ላይ ስቃይ መፈፀምን አቁሞ ለእርቅና ለድርድር መዘጋት ነው፡፡ የእስካሁኑ መንገድ የዕብሪት መንገድ በመሆኑ አውዳሚ ነው፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ጨርሶ አይጠቅምም፡፡ ይኽን መሠረታዊ ሐቅ መቀበልና ወደፊት መራመድ ብቻ ነው ለኢሕአዴግ ሰዎችም ለመላው ኢትዮጵያዊያንም የሚጠቅመው፡፡

ትዕምርታዊ እርምጃ!
***

‹ኤች.አር 128› መፅደቁ ለኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትልቅ ድል ነው፡፡ በውጭ አገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተናጠል ወገኖቻቸውን ቢረዱም፣ ኅብረት ፈጥረው አገር ቤት ያለውን አፋኝ የፖለቲካ ሥርዓት በማሻሻልና በመቀየር ረገድ ብዙ እንደሚቀራቸው በስፋት ሲተች ቆይቷል፡፡ ይኽ የውሳኔ ሐሳብ መፅደቁ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ በኅብረት መሥራትና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መጀመሩን የሚያበስር ነው፡፡

ይኽ የውሳኔ ሐሳብ እንዲፀድቅ አሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ትግል አድርገዋል፡፡ ብዙ ወገኖች እንቅልፍ አጥተው ያለ መታከት ወደየአካባቢው የሕዝብ ተወካዮች ቤት እየሄዱ በኢትዮጵያዊያን ላይ ስለሚደርሰው ሁኔታ አስረድተዋል፤ ቀስቅሰዋል፡፡ ልፋታቸው ፍሬ አፍርቶ የውሳኔ ሐሳቡ የመጀመሪያውን ደረጃ አልፏል፡፡ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሲተባበሩ ምን መሥራት እንደሚችሉ የታየበት አጋጣሚም ነው፡፡ ወደፊትም ቢሆን በውጭ የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከሌሎች አገሮች፣ በተለይም ከእስራኤል፣ ሕንድ፣ ሜክሲኮ ወዘተ. ዲያስፖራ ትምህርት ቀስመው በጋራና በተቀናጀ መልኩ እየተንቀሳቀሰ በአገራቸው ጉዳይ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አለባቸው፡፡ ለኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ መብትና ሰብአዊ መብት መከበር መታገል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊነት መከበር መታገል ነው፡፡

ለዜጎች ሰብአዊ ክብር መታገል እጅግ የተቀደሰ ተግባር ነው!!

ትዕምርታዊ እርምጃ! (የሱፍ ያሲን )