“–ብዙ ተስፋ ይታየኛል፡፡ አሁን ትግሉ ጥሩ ፍሬ እያፈራ ይመስለኛል፡፡… ” ወይንሸት ሞላ

ወጣቷ ፖለቲከኛ፣ የእስር ቤት ተሞክሮዋና ተስፋዎቿ

“–ብዙ ተስፋ ይታየኛል፡፡ አሁን ትግሉ ጥሩ ፍሬ እያፈራ ይመስለኛል፡፡ ወደፊትም የተሻለች ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የበለጠ ትግል እንደሚያስፈልግ ጥርጥር የለውም፡፡ እኔም ለዚያ እውን መሆን መክፈል ያለብኝን መስዋዕትነት ሁሉ እከፍላለሁ፡፡—”

በ22 ዓመት ዕድሜዋ “ሰማያዊ” ፓርቲን የተቀላቀለችው ወጣቷ ፖለቲከኛ ወይንሸት ሞላ፤ በ5 ዓመት የተቃውሞ ፖለቲካ ተሳትፎዋ ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ ለእስር ስትዳረግ መቆየቷን ትገልጻለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲ የዓለማቀፍ ግንኙነት የ3ኛ ዓመት ተማሪ ስትሆን፤ ከቀድሞ የ”ሰማያዊ” ፓርቲ አመራሮች ጋር በመሆን “የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ ፓርቲ”ን እየመሰረተች ትገኛለች፡፡ ወጣት ወይንሸት እንዴት ወደ ፖለቲካ ገባች? ምን ዓይነት ፈተናዎች ተጋፈጠች? ለምን በተደጋጋሚ ለእስር ተዳረገች? ለአገሯ ያላት ተስፋ ምን ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ከወጣቷ ፖለቲከኛ ጋር የአፍታ ቆይታ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-

መቼና እንዴት ነው ወደ ፖለቲካ የገባሽው?
የፖለቲካ ተሳትፎ የጀመርኩት በ2005 ዓ.ም የ“ሰማያዊ” ፓርቲ አባል በመሆን ነው። በወቅቱ ወደ ፖለቲካ ለመግባት ያነሳሳኝ ባደግሁበት አካባቢ ያለው የማህበረሰቡ አስቸጋሪ የአኗኗር ሁኔታ ነበር፡፡ የማህበረሰቡን ችግር በቅርበት ስመለከት መፍትሄ ማበጀት እችል እንደሆነ በማለት ነው ወደ ፖለቲካው የገባሁት፡፡ በኋላ ግን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ላይ ያሉትን ችግሮች መመልከት ጀመርኩ። በዚህም ትግሌን አጠናክሬ መቀጠል እንዳለብኝ አምኜ፣ እስከ ዛሬ በፖለቲካው ገፍቼበታለሁ፡፡
እንዴት “ሰማያዊ” ፓርቲን ለመቀላቀል መረጥሽ?
“ሰማያዊ” ፓርቲ የወጣቶች ስብስብ በመሆኑ ወደ ድርጅቱ ብገባ የተሻለ አስተዋፅኦ አበረክታለሁ በሚል ነው የተቀላቀልኩት፡፡
እስካሁን በፖለቲካ ተሳትፎሽ የገጠሙሽ ከባድ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
ተግዳሮት እንኳንስ በፖለቲካ በመደበኛ የእለት ተእለት ኑሮም አይጠፋም፡፡ በተለይ ለሴቶች ፈተናው ይጠነክራል፡፡ ነገር ግን በፓርቲ ውስጥ እኔን በተለየ ሁኔታ የገጠመኝ ፈተና የለም። በተለያዩ ጊዜያት በመንግስት ከደረሱብኝ ወከባዎች፣ ግፎችና በደሎች በቀር ማለት ነው፡፡
የፓርቲ ፖለቲካ ከጀመርሽ 5 ዓመት ገደማ ሆኖሻል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ምን ያህል ጊዜ ታሰርሽ?
ወደ ዘጠኝ ጊዜ ያህል ታስሬአለሁ፡፡ በአብዛኛው “ሰማያዊ” ፓርቲ ውስጥ በነበርኩበት ሰዓት፣ ለሰላማዊ ሰልፍና ለህዝባዊ ስብሰባ የውጪ ቅስቀሳዎችና የመድረክ ስራዎችን ስሰራ ነው የሚያስሩኝ፡፡ አንዳንዴም ያለሁበት ቦታ ድረስ መጥተው “ትፈለጊያለሽ” ብለው ወስደው ያስሩኛል።
ምን ያህል ጊዜ ነው ክስ የተመሰረተብሽ?
ፍ/ቤት የቀረቡ ጉዳዮቼ አንድ ሶስት ያህል ናቸው፡፡ አንደኛው፤ በአንዋር መስጊድ አካባቢ የነበረውን ህዝበ ሙስሊሙን ተቃውሞ ለመከታተል በሄድኩበት ወቅት የታሰርኩበትን አጋጣሚ ተከትሎ የቀረበብኝ ክስ ነው፡፡ ክሱ እስካሁን ድረስ በፍ/ቤት እየታየ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ በስር ፍ/ቤት ነፃ ብወጣም አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆብኝ፣ አሁንም እየተከራከርኩ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሊቢያ የተገደሉ ወንድሞቻችንን አስመልክቶ አብዮት አደባባይ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ምክንያት ገና ቦታው ላይ ሳልደርስ ከመንገድ ላይ ወስደው፣ አስረውኝ፣ የመሰረቱብኝ ክስ ነው፡፡ በዚህ ክስ 3 ወር ተፈርዶብኝ፣ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወርጄ፣ የእስር ጊዜዬን ጨርሼ ወጥቻለሁ፡፡ ሌላኛው “በማርች 8” የሴቶች የጎዳና ላይ ሩጫ፣ ከአጋሮቼ ጋር ተቃውሞ በማሰማታችን ፍ/ቤት ክስ ተመስርቶብኝ ነበር። በአብዛኛው ግን ጣቢያ ያለ ምንም ምክንያት አቆይተውኝ፣ ዝም ብለው ነው የሚለቁኝ፡፡
በእስር ወቅት አያያዙ ምን ይመስላል?
ያው የተለመዱ ማዋከቦችና ድብደባዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በአንዋር መስጊድ ጉዳይ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞብኛል፡፡ መቼም መነኮሳትና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ትላልቅ ፖለቲከኞች በሚታሰሩባት ሀገር፣ በአደባባይ ሴቶችና እናቶች በሚገደሉበት አገዛዝ ውስጥ እያለን፣ የእኔን የእስር ሁኔታ ማውራታችን ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም። ምናልባት ላንቺ የትኛው የእስር ጊዜ ከበደሽ የምትለኝ ከሆነ፣ ባለፈው ዓመት በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት፣ ለ2 ወር ከ15 ቀን የታሰርኩበት አጋጣሚ ከባድ ነበር። ለአንድ ወር አካባቢ ታስሬ የቆየሁት ቦሌ አካባቢ ነው፡፡ ቀሪውን 1 ወር ከ15 ቀን ግን ግቤ በረሃ ውስጥ በሚገኘው ጦላይ የወታደር ማሰልጠኛ ነበር የታሰርኩት፡፡ ይሄ የእስር አጋጣሚ ለኔ በጣም ከባድና ፈታኝ ነበር፡፡ ከዚህ ውጭ የነበሩኝ የእስር ጊዜያቶች የተፈፀሙት ግን በቃሊቲ ማረሚያ ቤትና በተለያዩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያዎች ነው፡፡ የጣቢያዎች እስር ደግሞ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ይፈፀምባቸዋል፡፡
በአንቺ ዕይታ፤ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የወጣት ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ምን ይመስላል?
ቀደም ሲል በ“ሰማያዊ” ፓርቲ፣ አሁን ደግሞ አዲስ እየመሰረትነው ባለው “የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ” በተሰኘው ፓርቲ ውስጥም የራሳችንን አስተዋፅኦ እናደርጋለን ብለን ሴቶችም፣ ወጣቶችም እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን በሀገሪቱ ያለው የወጣቶች በተለይ ደግሞ የሴቶች ተሳትፎ ያን ያህል ጠንካራ ነው ወይም አጥጋቢ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይሄ የሆነበት ምክንያት ምናልባት በኢትዮጵያ በነበረው የፖለቲካ ባህል የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ሴቶችን ወደ ፖለቲካው የሚጋብዝ ሁኔታና የተመቻቸ ነገር አለመኖሩ ይመስለኛል ተሳትፎአቸውን የገደበው፡፡ ነገር ግን ዛሬም ቢሆን ጥቂት ጠንካራ ወጣት ሴት ፖለቲከኞች አሉ፡፡
ወቅታዊውን የአገር ውስጥ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ታይዋለሽ?
እንግዲህ እስካሁን ገዥዎቻችን ለሁሉም ነገር ምላሻቸው ፉከራና ግትርነት ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ነገሮች ተካረው የሚበጠሱበት ደረጃ ላይ የደረሱ ይመስል ነበር፡፡ አሁን ከዶ/ር አብይ መመረጥ በኋላ ግን ያ የተወጠረ ነገር የመርገብ ሁኔታ እያሳየ ይመስላል፡፡ መቼም ከሌሎች ሃገራት ተሞክሮም ስናየው፣ በአመፅና በግጭት የሚመጣ አብዮትን ተከትሎ የተረጋጋ ሃገር ያለ አይመስለኝም። ከዚህ አንፃር አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ጥሩ መሸጋገሪያ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ በአጠቃላይ ግን የኢህአዴግ ተክለ ቁመና በአንድ ሰው ብቻ ይለወጣል የሚል እምነት የለኝም። እንደ መሸጋገሪያ ግን ጥሩ ነው። በሌላ በኩል ዶ/ር አብይን በተመለከተ የሚሰጡ አስተያቶች ትንሽ የተጋነኑ ይመስለኛል። ሰውየው ብቻቸውን የሚያመጡት ብዙ ለውጥ አይኖርም።
በአሁኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተስፋ ይታይሻል?
ብዙ ተስፋ ይታየኛል፡፡ አሁን ትግሉ ጥሩ ፍሬ እያፈራ ይመስለኛል፡፡ ወደፊትም የተሻለች ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የበለጠ ትግል እንደሚያስፈልግ ጥርጥር የለውም። እኔም ለዚያ እውን መሆን መክፈል ያለብኝን መስዋዕትነት ሁሉ እከፍላለሁ፡፡

Source Addis Admass

“–ብዙ ተስፋ ይታየኛል፡፡ አሁን ትግሉ ጥሩ ፍሬ እያፈራ ይመስለኛል፡፡… ” ወይንሸት ሞላ