ይድረስ ለወንድ አባዊርቱ – አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)

አባዊርቱ ሰላምታየ ይድረስህ፡፡ አንተ ብል አትቀየምም ብዬ አስባለሁ፡፡ ጽሑፍህን ሁልጊዜ እከታተላለሁ፡፡ አንድ የሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀምህን ላስታውስህ እልና እዘነጋዋለሁ፡፡ አሁን ግን ሳልረሳ እዚች ላይ ላስታውስህ ወደድኩ፡፡ (ይህን አስተያየት በሣተናው ድረገፅ ላይ በወጣው መጣጥፍህ ሥር ላስቀምጥ ነበር – ግን በዛ አለብኝና ሌላም ሃሳብ ተወነጋግሮ ገባብኝና ለብቻው ላክሁት፡፡ ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡)

በአራት ነጥብ ቦታ(፡፡) ድርብ ሠረዝ(፤) መጠቀምህን አስታውስና ለወደፊቱ አስተካክላት፡፡

ይህን የምለው መምህር ስለሆንኩ ነው፡፡ ነጥቦች ሁሉ አጠቃቀማቸው ይለያያል፡፡ ምንም እንኳን በትርጉም ረገድ በአንተው አጠቃቀም ውስጥ ይህ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ልዩነት ባይኖርም በደንቡ መሠረት መጓዙ ጥሩ ነው፡፡ የሚከተሉትን ምሣሌዎች ከየነጥቦቹ ላስቀምጥ፡-

  1. ነጠላ ሠረዝ (፣) ፡-  ሐጎስ፣ ደስታ፣ ሻመና፣ ገመቹና ዘበርጋ ጓደኞቼ ናቸው፡፡ (ይህ ነጥብ እንደ “እና” ሊያገለግለን የሚችል ጠቃሚ ነጥብ ነው፡፡ በዚህ ምሣሌ መሠረት በሥርዓተ ነጥቡ ምክንያት የሰውዬው ጓደኞች ቁጥር ሊያንስና ሊበዛ ይችላል፡፡ ለአብነት – ሐጎስ ደስታ፣ ሻመና ገመቹና ዘበርጋ ጓደኞቼ ናቸው – ቢል የጓደኞቹ ብዛት ከአምስት ወደ ሦስት ወረዱ)፡፡ በሌላም በኩል ራሳቸውን ያልቻሉ ሐረጋትን ከዋናው ዐረፍተ ነገር ያያይዝልናል፡፡ ምሣሌ፡- ወንድሜ አባዊርቱ ጧት ከተገናኘን ጀምሮ ስለየግል ጉዳያችን ስንጫወት፣ ስንወያይ፣ ስንመካከርና ስላገራችን የጋራ ችግርም መላ ስንፈልግ ዋልን፡፡ … እንደገናም የሚዘረዘሩ ነገሮችን ለመዘርዘር ይህን ነጥብ እንጠቀማለን፡- ለምሣሌ – በአቶ ኑራዲስ የሸቀጣ ሸቀጦች መደብር ውስጥ መጥረጊያ፣ ባልዲ፣ ሣሙና፣ ኦሞ፣ የጥርስ ቡርሽና የመሳሰለው ይገኛል፡፡
  2. ድርብ ሠረዝ (፤) – ጥገኛ ዐረፍተ ነገሮችን እንለይበታለን፡፡ ለምሣሌ፡- ጓደኛየ አባዊርቱና እኔ ከተገናኘን ጀምሮ ብዙ ተጫወትን፤ በጠቃሚ ሃሳቦች ዙሪያም ተወያየን፤ በብዙ ነገሮች ተግባባን፤ አሁን ግን ምሽቱ ስለተቃረበ ወደየቤታችን እንሂድና ዐረፍ እንበል፡፡
  3. አራት ነጥብ (፡፡) አንድ ሙሉ ሃሳብ በአራት ነጥብ ይዘጋል፡፡ ምሣሌ (ከአባዊርቱ ጽሑፍ ቀጣዩን ልውሰድ – በቅንፍ ውስጥ ያሉት ቀድመው የነበሩት ናቸው፡፡)

“ሰርፀ ለምትባለው ካንተ ልጀምር እስቲ፡፡ (፤፤) ይሄን «ጉድህን» አየሁት፡፡ (፤፤) ያንተም ጥርጣሬ በዛ፡፡ (፤፤) የንግድ ባንኩን ሆነ መሰል ተቁዋማት ተጠሪነታቸው ለ PEHAA ነው፡፡ (፤፤) አቢይ በቀጥታ አይሾሙም – እንደገባኝ፡፡ (፤፤) ያ ከሆነ ደሞ ሹዋሚው በየነ ገ/መስቀል ሊሆን ነው፡፡ (፤፤) የአቢይን ስብእና ብሎም ኢንቴሌክት ያየ (ለኔ ይታየኛል) አቢይ አህመድ እ(አ)ንዲህ ወርዶ በጎጥ ይቀጥራል ልትለኝ ነው ሃላፊነቱ እንኩዋ ቢሆን? የቅዋሜም ወግ እያጣ መጣ እኮ! (፤፤) ይልቅ  መፍትሄ የምትላቸውን አንድ ሁለት እያልክ አቅርብ፡፡(፤፤) ለአገር ብዙ ትጠቅማለህ እንደዛ ሲሆን፡፡ (፤፤)”

በተረፈ ጥረትህን እንደማደንቅ በዚህ አጋጣሚ መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ ይሁንና የሀገራችን ችግር አንተ ቀለል አድርገህ ለማየት እንደምትሞክረው እንዳልሆነ ላስታውስህ እወዳለሁ፡፡ እንደዚያ በሆነ በማን ዕድላችን! ሆኖም ጥሩ መመኘት ጥሩ ነውና እንደምኞትህ ያድርግልን፡፡ አንድ ጸሎት ደግሞ አለኝ – እንደታዘብኩህ ለሀገርህ ያለህ ፍቅር በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ያንና ያንን ለማሰባሰብ ያለህንም ፍላጎት እረዳለሁ፡፡ በዚህ መሀል ግን በዚህ የበሸቀጠ የጎሠኝነት አዙሪታዊ ልክፍት እንዳትመረዝብኝ በሚል ሰው ከማጣት አንጻር ለራሴ እሰጋለሁ፡፡ ሰው እያጣን ነውና አይፈረድብኝም፡፡ ይሄ ዘረኝነት የሚሉት ጣጣ ሰዎችን ባስቀመጥናቸው እንዳናገኛቸው እያደረገን ነውና በበኩሌ በጋራ ሀብትነት የፈረጅኩትን ሰው ባጣ ልቤ ይሰበራል ብዬ እፈራለሁ፡፡

ሁሉም በየፊናው የዘሩን ትልም እያነፈነፈ ከሄደ ሀገራችን የእሪያዎች መፈንጪያ ሆና መቅረቷ ነውና ወደሚያለያየው ሣይሆን ወደሚያገናኘው የወል መድረክ መምጣት አለብን፡፡ ሰዎች ተሳሳቱ ብለንም መሳሳት የለብንም፡፡ ቢቻለን ያለመሳሳት መለኪያዎች ብንሆን እኛም ሀገራችንም ትጠቀማለች፡፡ የኛ የምንላቸው ሰዎች ቢሳሳቱ እንኳ ልንመልሳቸው ይገባል እንጂ እነሱን ለመሸፈን ብዙ ርቀት መጓዙ ለነሱም ለኛም አይጠቅምም፡፡ ይሄን “ትንሽ ሥጋ እንደመርፌ ትወጋ” የሚባልን ያረጀ ያፈጀ አባባል ከማደስ ይልቅ በሰው ልጆች የጋራ ማንነት ብናምን ይበልጥ እንጠቀማለን፡፡

ሥጋቶችን ደግሞ መቀበል ተገቢ ነው፡፡ እርግጥ ነው – ሥጋቶችን የምናይበት መነጽር ሊለያይ ይችላል፡፡ ይህም ያለ ነው፡፡ መነጽሩ ሲለያይ ደግሞ ክብደት ቅለቱም እንዲሁ ይለያያል፡፡ ይሄ “የኔ” እና “የነሱ” የሚል ፍረጃ ደግሞ በአስቸኳይ መቅረት አለበት፡፡ የኔ የምለው ሲሳሳትና የነሱ የምለው ሲሳሳት የሚኖረኝ ፍርድና አስተያየት የሚለያይ ከሆነ መሠረታዊ ችግር አለብኝ ማለት ነውና ራሴን መፈተሽ ይኖርብኛል፡፡ ስለዚህ ሰዎች እኛ ከምናውቀው እውነታ በብዙ ተለዩ ብለን ወቀሳችንን ከመሸከም አቅማቸው በላይ ብናዥጎደጉድባቸው ይበልጥ እንቃቃርና ክፍተታችን ይጨምራል፡፡ ያኔ በእልህ እየተጎዳዳን እንሄድና ማንም አያተርፍም፡፡ እልህ መጥፎ በሽታ ነው፡፡

ወንድሜ አባዊርቱ አሁን የወቀስካቸውን ሰዎች ሥጋት እንደነሱ ሆነህ እነሱ የጠቀሷቸውን ሥጋቶች ብትመረምር አንተ የያዝከውን አቋም እንደምትመረምር አልጠራጠርም፡፡ ይሄን አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣… የምንለውን ሰውኛ ክፍፍል እንተወው፡፡ ስለኢትዮጵያችን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ግን ከምንም ዓይነት የዘር መነጽር ውጪ እንመልከት፡፡ በአማራው አካባቢ እየተሠራ ያለውን ተደጋጋሚውን የደን ቃጠሎ ጨምረህ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን ሆን ተብሎ በዕቅድ የማጥፋት ተግባር ( መናፈሻውም ሆነ ሌሎቹ የቱሪስት መስህቦች ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደማይጠቅሙ ሁሉ)፣ ጣናን በአረም የማስወረር ሥውር ተንኮል፣ በየአካባቢው የሚጠመደውን ፈንጅና የፈንጁን ፍንዳታ ከዚያም በበላይ አካል የሚሰጠውን እጅግ አሣፋሪ ሰበብ፣ አማርኛ ተናጋሪን ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ መስተዳድር ዋና ዋና የሥራ ኃላፊነቶች የማባረርና በሌሎች ወንድምና እህቶቹ አላግባብ የመተካት ዕኩይ ድርጊት፣ ከአዲስ አበባ አካባቢዎች ተበድሮ ተለቅቶ በችግር እየተቆራመደ ከሠራው መኖሪያ ቤቱ  የሚፈናቀለውን ዜጋ፣ ብቻ … ሁሉንምና በአብዛኛው የዚህችን ያለፈች ዓመት የዶ/ር አቢይ የሥልጣን ዘመን እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዐይናችንን ጨፍነን በጥሞና እናጢን፡፡ ብዙ እጅግ ብዙ እፎይታ ያላገኘነውን ያህል በዚያው መጠን እጅግ ብዙ አሳሳቢ ነገሮች ተከስተዋል – በጤናማ ኅሊና የነገሮችን አካሄድ ካየን፡፡ በምንም ምክንያት ይሁን እነዚህን ነገሮች ለማየት አለመሞከር ወይም አለመፈለግ በኔ ዕይታ የሁለት መነጽሮች ጌታ የሚያስብል ይመስለኛል፡፡ አንድ እውነት ደግሞ ከየትኛውም አቅጣጫ ቢታይ አይለወጥም – ተመልካቹ ማየት የማይፈልገውን ላለማየት በይሁንታ ዐይኑን ካልጨፈነ በስተቀር፡፡ ከበደ ሲያጠፋ እኔ በይሉኝታ ወይም በዘር ጥልፍልግፍ ተሸመድምጄ ዝም ብልና ደቻሳ ሲያጠፋ ትንታግ ምላሴን የምዘረጋ ከሆነ ከንቱ ነኝ – እንደሰውም ልቆጠር አይገባኝም፡፡ ከእንስሳዊ የደምና አጥንት አነፍናፊነት በሽታም አልወጣሁም፡፡ ሐጎስ ሲያጠፋ ፍትዊ የሐጎስን ስህተት ለመናገር አንደበቱ ከተሳሰረ ሰው ለመሆን ብዙ ይቀረዋል፡፡ ፈይሣ ሲያጠፋ ሌሊሣ ፊቱን አዙሮ ያላዬ ቢመስል ድመትና ውሻ በፍትህ አሰጣጥ ያስከንዱታል፡፡ ነገሮችን ከዚህ አኳያም ብናያቸውና ራሳችንን ብናስተካክል  የዛሬና የነገ ኢትዮጵያችን ወግ ደርሷት እንዳደጉትና እንደበለጸጉት ሀገሮች ትሆናለች፡፡ በብዙ ችግሮች እየተገረፍን ያለን የአንዲት ሀገር ዜጎች የሀገር ውስጥ ምንደኞችና ውድቀታችንን የሚመኙ የውጭ ኃይሎች ባዘጋጁልን ወጥመድ ዘው ብለን እየገባን በረባ ባልረባው ልክ እንደታሪካዊ ባላንጣዎች ስንወዛገብና ስንጨራረስ ሌላው ዓለም ቀድሞን ሄደ፡፡ እኛ ግን ሆዳችንንም መሙላት አቅቶን በጥቂት አልቅቶችና ነቀዞች ተወርረን በርሀብና በበሽታ ማለቅ የዘላለም ፍርዳችን ሆኖ ቀረ፡፡ በአንድ ወር ደሞዙ አፍሪካን የሚጎበኝ አፍሪካዊ ምሁር መኖሩን እንደማንሰማ ሁሉ በአንድ ወር ደሞዙ ቤት ኪራዩንና ሆዱን መሸፈን አቅቶት በረንዳ የሚያድር የኮሌጅ ምሩቅ የምታስተናግድ ጉደኛ ሀገር ሊኖረን የቻለው ጠባያችን በመክፋቱ፣ ቢሮክራሲያችን በሙስናና በዘረኝነት በመከርፋቱ፣ እንዲሁም በዕውቀትና በጥበብ እየጫጫን በመሄዳችን ምክንያት ነው – ሌላ አይደለም፤ እርግማንም አይደለም፡፡

ለጥቂት ነገር ተነስቼ ብዙ ዘበዘብኩ፡፡ በአባዊርቱ መጣጥፍ ሥር እንደአስተያየት ላስቀምጥ ነበር ከፍ ሲል ስለ ሥርዓተ ነጥቦቹ ያነሳሁትን ጉዳይ፡፡ አሁንማ ርዕስ ልስጠውና ራሱን ችሎ ይውጣልኝ እንጂ፡፡  አባዊርቱ በርታልኝ፤ እኔንም ተረዳኝ፡፡ ያለን ምድራዊ ጊዜ በጣም አጭር ነው – እንኳንስ ተጣልተን ተፋቅረንም በሆነልን፡፡ እንማማር፣ እንመካከርምና በተቻለን ራሳችንን ሰውተንም ቢሆን የተፈጠርንባትን ምድር ከተደገሰላት ሊቀርም ላይቀርም የሚችል የሞት ድግስ ለማትረፍ የበኩላችንን እንሞክር፡፡ ጥረት አነሰ አደገ አይባልም፡፡ አንድ ወንዝ የሚሞላው ከየምንጩና መጋቢው በሚገኝ ውኃ ነውና ራሳችንን ሳንንቅ የተቻለንን ሁሉ አሁን እየቻልን እናድርግ፡፡ ሩዋንዳን ያየ በዘረኝነት እሳት አይጫወትም፡፡ አንተም ባለህ መንገድ ሁሉ ወንድሞቻችንን ምከራው፡፡ የሚያዩት ሁሉ፣ የሚጨቨብጡት ሁሉ፣ የሚሆኑት ሁሉ … ዘላቂነት የለውም፡፡ እኔ ከኮሎጅ ተመርቄ  ሥራ እንደያዝኩ የሱዳንን በትረ መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥት የጨበጠው አልበሽር እንኳን ጊዜውን ጠብቆ ሰሞኑን ውርደትን ተከናነበ (ሥልጣን እንደያዘ አላንዳች ሥጋት አዲስ አበባ ላይ ይደረግ ወደነበረው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ መምጣቱ ብዙዎቻችንን አስደንቆን ስለነበር ያንን ወቅት አልረሳውም)፡፡ ለማንኛውም ዓለም እንዲህ ናት፡፡ ያዝኳት ስትላት ትለቅሃለች፤ አሞቀችኝ ከማለትህ በብርድ ታንቀጠቅጥሃለች፡፡ ከሁሉም ለሁሉም የሚበጀው ታዲያ ምክንያታዊነትና ሰብኣዊነት መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ሰላም፡፡

(ይህን ጽሑፍ ከትናንት ወዲያ ቅዳሜ ጽፌ ልልክ ስል ኔትውርክ ጠፋ፡፡ ዛሬ ሰኞ ነው – 7/8/2011ዓ.ም፡፡ ሌሊት ድረገፆችን ስቃኝ በአባዊርቱና በነሠርፀ መካከል “ጦርነቱ” ተፋፍሞ መቀጠሉን ከተለጠፉ መጣጥፎች ተረዳሁ – አነበብኳቸውም – እንደመዝናኛ፡፡ አጭር ቃል መናገር ፈለግ አሁን ታዲያ፡፡ የለውጡን ኃይል ገመና ለመሸፈን የዓለማችን የጨርቅ ጣቃዎች ሁሉ በአንድነት ተሰባስበው ካባና ቀሚስ ቢሰፉ አንዱንም ሊሸፍኑ አይቻላቸውም፡፡ ገሃድ የወጣውን የለውጡን ኃይል የአካሄድ ችግር ለማድበስበስና ነውሮችን በምክንያት ለመጀቦን ቢፈለግ ከትዝብት በስተቀር ትርፍ የለውም፡፡ ስለዚህ ሰዎች በከንቱ ባይደክሙ የሚል የራሴ እምነት አለኝ፡፡ መሆን ያለበት ከመሆን ላይዘል አንዱ ሌላውን በነገርና በአሽሙር መጎሰሙ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ “እከሌ ስለእከሌ እንዲህ አለ” ከሚል ከንቱ ውዳሤ በስተቀር በዚህ ጭቅጭቅ የሚያተርፍ የለም፡፡ ያደለው ውስጠኛ ዐይኑን ከፍቶ ግራ ቀኙን ቢመለከት መልካምና ለችግሮቻችን መፍትሔ ለማግኘት ግማሽ ያህል መንገድ በተጓዝን፡፡ በዘርም ይሁን በአመለካከት ተቧድኖ ወርቃማ ጊዜን ማባከን ዕድሜን መጨረስ ይመስለኛል – ልክ እንደኔ፡፡)

ma74085@gmail.com

 

The post ይድረስ ለወንድ አባዊርቱ – አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ) appeared first on ሳተናው: የዕለቱ ዜናዎች እና ሰበር ዜናዎች – መረጃ ማግኘት መብትዎ ነው!.

ይድረስ ለወንድ አባዊርቱ – አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)