ግምቱ 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሆነ የኮንትሮባንድ እቃ ተያዘ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 7 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ አርሲ ዶዶላ ወረዳ ግምቱ 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሆነ የኮንትሮባንድ እቃ መያዙን በጉሙሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በተሳቢ ተሽከርካሪ ተጭኖ ሲጓጓዝ የነበረው ልባሽ ጨርቅና አዳዲስ የሴት ጫማ ከባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ ወደ ሻሸመኔ ከተማ ሲያቀና እንደነበረም ተነግሯል።

ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩት አሽከርካሪውን ጨምሮ በአዳባ መቆጣጠሪያ ኬላ ፈታሽና በቦታው በአመራርነት የሚሰራ የፌደራል ፖሊስ አባልም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በጉሙሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ኢዴሳ ለማ ተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር እንዲውል ህብረተሰቡ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል ነዉ ያሉት።

አሁን ላይም በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።

በፌደራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ደቡብ ዲቪዥን ምክትል አዛዥ ኮማንደር ሙሳ ሄቦ በበኩላቸው አሽከርካሪው ለማምለጥ ቢሞክርም በፖሊስ ከፍተኛ ጥረት ሊያዝ መቻሉን ተናግረዋል።

 

በጌታቸው ሙለታ

ግምቱ 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሆነ የኮንትሮባንድ እቃ ተያዘ