ሃዋሳን የጎብኝዎች መዳረሻ እና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ይሰራል –  አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ  

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 7 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀዋሳን ሃይቅ ዳርቻ በማልማትና በማፅዳት ከተማዋን በዓለም በማስተዋወቅና የጎብኝዎች መዳረሻ እና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራ የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ተናገሩ።

በጅግጅጋ በተካሄደው 8ኛው የከተሞች ፎረምን ጨምሮ ለ7ኛ ጊዜ ራስን በማስተዋወቅ ሀዋሳ ከተማ 1ኛ መውጣቷን ምክንያት በማድረግ ለከተማው ማህበረሰብና ባለሀብቶች እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።

ከተማዋ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ተሻግራ 1ኛ መውጣቷ ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶች እንዲሁም እያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ያደረጉት ጉልህ ተሳትፎ ስለታከለበት መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት ተናግረዋል።

አሁንም ቢሆን ከተማዋን በማልማት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በተለይም ባለሀብቱ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚያደርግ እምነቴ ነው ብለዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ 25 ባለሀብቶች ሲሸለሙ ከተማዋ ራሷን በማስተዋወቅ ከፍተኛ ቦታ እንድታገኝ የሰሩ 244 ባለሙያዎችም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

 

 

በያሬድ ጌታቸው

ሃዋሳን የጎብኝዎች መዳረሻ እና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ይሰራል –  አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ