ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ ከሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጄኔራል ጋላለዲን አል ሼክ ከተመራ የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ መንግስት ለሱዳን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ለሱዳን የሚያደርገው ድጋፍ በመከባባር ላይ የተመሰረተ፣ የሱዳንን ሉዓላዊነት በማክበርና ከጣልቃ ገብነት የፀዳ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ሽግግሩን ሰላማዊና አካታች እንዲያደርግም አበረታተዋል።

በዚሁ ውይይትም ጄኔራሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሱዳንን ሪፐብሊክ ወቅታዊ ሁኔታ አስረድተዋል።

ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ስትራቴጅክ አጋርነት ጠቃሚ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዚህ የሽግግር ወቅትም የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን ጋር የነበረውን የቆየ ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Photo ፡- office of the prime minister-ethiopia

ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ ከሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ