በመንግስት ተቋማት በተፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 7 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ከተፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ባለፈው ሳምንት 59 ያህል የስራ ሃላፊዎች በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በዛሬው እለትም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት 20 ተጠርጣሪዎች ቀርበዋል።

በዛሬው ችሎት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የቀድሞ የስራ ሃላፊዎች እነ አትክልቲ ተካ መዝገብ የቀረበ ሲሆን፥ ግለሰቦቹ ወደ 65 ሚሊየን ብር ገደማ በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ከ2003 እስከ 2008 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የስራ ሃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲሰሩ የአርማታ ብረትና የህክምና መሳሪያዎች ግዥና ፕሮጀክቶቹ ስራ ባቆሙበት ወቅትም ለተሽከርካሪ ኪራይና ሌሎች ተያያዥ ስራዎች በሚል በመንግስት ላይ 65 ሚሊየን ያህል ብር ጉዳት አድርሰዋል በሚል ነው የተጠረጠሩት።

መርማሪ ፖሊስ እስካሁን ያከናወናቸውን የምርመራ ስራዎች በጽሁፍ ያቀረበ ሲሆን፥ የተጠርጣዎቹን የመግቢያ ቃል መቀበልና የተለያዩ የማስረጃ  ማሰባሰብ ስራዎች መስራቱን፣ የኦዲት ሪፖርቶችን ሙሉ በሙሉ ማሳባሳብ፣ የኦዲተሮችን ዝርዝር ቃል መቀበል፣ ለፎረንሲክ ምርመራ የሚረዱ ሰነዶችን ከሚመለከታቸው ተቋማት ማሰባሰብና ማመሰካሩንም ለችሎቱ አስረድቷል።

ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለማገባደድም ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜን ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ከተጠርጣሪዎች ማረፊያ ጋር በተያያዘ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው፥ የተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት ተከብሮ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡

መርማሪም ተጠርጣሪዎቹ ቢለቀቁ የምርመራ ስራውን ሊያደናቅፉ ስለሚችሉ ጉዳያቸውን በእስር ላይ ሆነው እንዲከታተሉም ጠይቋል፡፡

ግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱም በመዝገቡ ላይ አስተያየት ለመስጠት ለነገ 8 ሰዓት ቀጠሮ ሰጥቷል።

በተያያዘ ዜና በእነ አቶ ይገዙ ዳባ መዝገብ 3 የቀድሞ ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የስራ ሃላፊዎች በጥቅም በመመሳጠር፥ በአጠቃላይ 23 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በመንግስት ሃብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ግለሰቦቹ ከ400 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ጋር በተያያዘ በጥቅም በመመሳጠር ነው የተጠረጠሩት።

ተጠርጣሪዎቹ በግል ጠበቃ ማቆም የሚችሉ በመሆናቸው ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ጉዳያቸው እንዲታይ ባሰሙት አቤቱታ መሰረትም ፍርድ ቤቱ የፊታችን ረቡዕ 8 ሠዓት ላይ መዝገባቸውን ለመመልከት ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ ተጠርጣሪዎችን መዝገብም ተመልክቷል።

 

 

በአወል አበራ

 

 

በመንግስት ተቋማት በተፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ