የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የተነሳውን እሳት ለመቆጣጠር በሄሊኮፕተር የሚደረገው ጥረት በቂ አለመሆኑ ተገለጸ

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 07/2011ዓ.ም (አብመድ) የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ለምለሙ ለአብመድ እንዳስታወቁት ውኃ በመርጨት ለማጥፋት ጥረት የጀመረችው አንድ ሄሊኮፕተር ትናንት በአምስት ዙሮች በእሳቱ ላይ ውኃ ረጭታለች፡፡ ዛሬም ከረፋድ ጀምሮ የማጥፋት ሥራውን አጠናክራ መቀጠሏን ተናግረዋል፡፡

ነዳጅ ከጎንደር የሚሞላ መሆኑና ሄሊኮፕተሯ ውኃ የምትቀዳው ከደባርቅ አሠራ ወንዝ መሆኑ በሄሊኮፕተሯ እሳቱን የመቆጣጠር ውጤታማነት ላይ ችግር መፍጠሩን አቶ ወርቁ ተናግረዋል፡፡ በፓርኩ የእሳት አደጋውን ሁኔታ የተመለከቱት የእስራኤል ባለሙያዎች በየአምስት ደቂቃው ሄሊኮፕተሯ ውኃ መርጨት ከቻለች ተጨማሪ ሄሊኮፕተር እንደማያስፈልግ መናገራቸውን አቶ ወርቁ አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ውኃው የሚቀዳበት ስፍራ ከፓርኩ ስለሚርቅ ሄሊኮፕተሯ ከ20 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ውኃ መርጨት እንደማትችል ታውቋል፡፡

የውኃው ቶሎ ቶሎ አለመረጨት እሳቱ እንዲያገግም ዕድል እንደሚሰጥ ባለሙያዎቹ መግለጻቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የባለሙያዎቹ ቡድን ምክረ ሐሳብ እንደሚያመለክተው በየአምስት ደቂቃው ለመርጨት አሁን ውኃ ከሚቀደባት የቀረበ ወንዝ ካልተገኘ የሄሊኮፕተሮቹን ቁጥር ወደ አራት ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡

የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከመጋቢት 30 ቀን 2011ዓ.ም ምሽት ጀምሮ የእሳት ቃጠሎ አጋጥሞታል፡፡ ከመጋቢት 19 እስከ 26 ባሉት ቀናትም ቃጠሎ አጋጥሞት 342 ሄክታር የፓርኩ ክፍል መጎዳቱ የሚታወስ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

ፎቶ፡- ባያብል ሙላቴ

The post የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የተነሳውን እሳት ለመቆጣጠር በሄሊኮፕተር የሚደረገው ጥረት በቂ አለመሆኑ ተገለጸ appeared first on ሳተናው: የዕለቱ ዜናዎች እና ሰበር ዜናዎች – መረጃ ማግኘት መብትዎ ነው!.

የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የተነሳውን እሳት ለመቆጣጠር በሄሊኮፕተር የሚደረገው ጥረት በቂ አለመሆኑ ተገለጸ