የኢህአዴግ ም/ቤት የመጀመሪያ ቀን ውሎ (አያሌው መንበረ)

የኢህአዴግ ጉባኤ በዛሬው ስብሰባ ከህወሃት ጋር ተያይዞ በተነሱትና ህወሃት ባነሳቸው ጉዳዮች መግባባት ላይ አልደረሰም

ኢህአዴግ ምክር ቤት በትናንት/ዛሬ ውሎው ቀደም ብለው በተለዩ ጉዳዮችና አሁን ለውጡ ባለበት ጉዳይ ውይይት ሲያደርግ ውሏል።

ስለሆነም በዚህ ስብሰባ በርካታ ነጥቦች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ብዙዎቹ መግባባት ስላልተቻለ ባለበት (ከዚህ በፊት በውይይት ሳይግባቡ በተለያዩበት) ቀጥለዋል።እርግጥ ስብሰባው ገና አልተጠቃለለም።

በዚህ “እምርታዊ ለውጥና ተግዳሮቶቹ” በሚል ከሁለት ወር በፊት በተዘጋጀውና ሳይግባቡት በቀሩት ሰነድ በህወሃት ዛሬም አቋም የያዘባቸው ተስተውለዋል።በሂደቱ ህወሃት ለአዴፓ እና ለኦዴፓ ብሎ ያዘጋጃቸው አጀንዳዎችም ነበሩ።በተለይም ኦዴፓ አዴፓን መካዱን ተመልክቶ ጋዝ ለማርከፍከፍ የሄደት መንገድ ብዙም የተሳካ አይመስልም።

ህወሃት ካናሳቸውና አቋም ከያዘባቸው ውስጥ

1.ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ሳይሆን ነውጥ ነው ያለ በሚል የገለፀ ሲሆን ከዚክ ጋር አያይዞ “ድሮ ወደነበርንበት መመለስ አለብን” በሚል ያቀረበው ሀሳብ በርካታ ትችትን አስከትሎበታል።
“ወደ ድሮው እንመለስ ሲባል እኮ የሰብኣዊ መብት ተረግጦ የጥቂቶች የፈላጭ ቆራጭነት ዘመን እንሂድ ማለት ነው በማለት አዴፓ ህወሃትን ተችቷል

2.በኢትዮጵያ ህገ ወጥነት ተስፋፍቷል፣ማዕከላዊ መንግስቱ ተዳክሟል የሚለው ሀሳብ በከፊል የተደገፈ ቢሆንም በማሳያነት የቀረበው ግን ትክክል ያልሆነ መሆኑም ተተችቷል።በተለይም ፋኖ፣ የጎበዝ አለቃ …የሚለውን ለመተቸት ሞክሮ ” አማራ ክልል ሁሉም በትጥቅ ይታገል የነበረ ሁሉ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ ነው ይህ ስጋት አይደለም” ተብሏል።

3.ህወሃት ወንጀለኞችን የመያዝ ጉዳይ “ብሄር ተኮር ነው” በማለት ሀሳብ አንስቷል።ሆኖም ይህ ጉዳይም ትክክል እንዳልሆነ ተነግሯል።

4.ህወሃት አማራ ክልልን “ልትወሩን ተዘጋጅታችኋል” በሚል ያቀረበ ሲሆን አዴፓ በበኩሉ “የመንግስትን ትጥቅ ጭምር እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም ጦር እየሰበቃችሁ ያላቸሁት እናንተ እንጅ እኛ አይደለንም፣ይህ ሊቆም ይገባል” በሚል አቅርቧል ተብሏል።

5.የተቋቋመው የወሰንና ማንነት ኮሚሽን ህገ መንግስቱን የተጋፋ፣የፌደሬሽን ም/ቤትን ስልጣንም ያላከበረ ነው በሚል ያቀረበ ሲሆን በሌሎች በኩል የተመለሰውም የህወሃት የያዘው አቋም ትክክል አይደለም የሚል ነው።

6.ኦዴፓ ደግሞ የአዲስ አበባ ጉዳይ እያጨቃጨቀ ስለሆነ ግልፅ አቋም ይያዝበት ብሎ ጥያቄ ያነሳ ሲሆን አዴፓ “የአዲስ አበባ ጉዳይ ግልፅ ነው፣አዲስ አበባ የጋራ ሀብታችን ናት፣ይህ ግን ትክክል አይደለም የሚል ካለ ሀሳብ ያቅርብ” በሚል መልሷል።ሆኖም በኦዳፓ በኩል ተጨማሪ ሀሳብ ሳይሰጥ ቀርቷል።

ውይይቱ ገና በመድረክ መሪዎቹ ደመቀና አብይ ማጠቃለያ ያልተሰጠበት ሲሆን በጥቅሉ ሲገመገም ህወሃት አሁንም የዛሬ ሁለት ወር ከያዘው አቋም ያልተለየ፣ኦዴፓ ደግሞ ጠንካራ አቋም ያላሳየበት፣አዴፓ አቋሙ ወጥ የሆነበት፣ደኢህዴን በተመልካችነት የቀጠለበት “የህወሃት፣የአዴፓና የኦዴፓ” ስብሰባ የሚመስል ነው ተብሏል።

በዚህ መድረክ አዴፓና ኦዴፓ ተቃራኒ አቋም ሊይዙ ይችላሉ ተብሎ ቢገመትም እስካሁን ከተነሱት ውስጥ ሁለቱም ሊያወዛግብ የሚችል አጀንዳ እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል።

የህወሃትን አቋም ከባለፈው የሚለየው ባለፈው “የዚች ሀገር ስጋት ትምክህት ሳይሆን አክራሪ ብሄርተኝነት ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ህወሃት አካራሪ ብሄርተኝነት ቢኖርም ስጋቱ ግን “ትምክህት ነው” በማለት በጠባብነት የሚከሰሰው ኦዴፓ በትምክህተኝነት የሚከሰሰውን አዴፓን እንዲጠራጠረው ታቅዶ ነበር።
ሆኖም ባለፈው ኦዴፓን ያልወቀሰው ህወሃት በአሁኑ መድረክ ኦዴፓ ጠባብ ነው በሚለውም ተሸንቁጧል።
የኢትዮጵያን ታሪክ መውደድና ማክበር ኢትዮጽያዊነትን ማቀንቀን ትምክህት ሳይሆን በሀገር መኩራት ነው ያሚለው ሀሳብ ተንፀባርቋል።ኦዴፓም ጠባብነት በሚለው ሀሳብ በስጨት ብሎ ነበር ተብሏል።

እንግዲህ የመጀመሪያው ቀን የኢህአዴግ ም/ቤት ውሎ ህወሃት ሁሉንም የኮነነበት እንደነበር ታውቋል።

አዴፓም ለህወሃት ክፍተት ላለመስጠት በጥንቃቄ እንዳለፈው የተገለፀ ሲሆን ኦዴፓ ችግሩን አስተካክሎ ወጥ አቋም ካልያዘ ግን ህወሃት ወደ መሃል የመሳብ እድል ሊኖረው ይችላል የሚል ድምዳሜ መድረስ ይቻላል።

ምክንያቱም ኦዴፓ ክህደቱን ከቀጠለበት አዴፓ ከኦዴፓ ሊሸሽ ይችላል።ይህም ለህወሃት ምቹጌ ነው።ህወሃት ደግሞ ኳስ እንዴት መጫዎት እንደሚችል ከኦዴፓ የተሻለ ልምድ አለውና።

አሁን ጥያቄው ኦዴፓ ወደ ቀድሞ አቋሙ ተመልሶ እኩልነትን በእውነተኛ ስሜት ይዞ ይጓዝ ይሆን? ወይስ ስራውን እየሰራ በብልጣብልጥነትና በሴራ ፖለቲካ ተጉዡ አሸንፋለው የሚለውን አሁንም ይቀጥልበት ይሆን? የሚለው ነው።

የሆነው ሁኖ ግን በምክር ቤቱ አቅጣጫ ከማስቀመጥ ያለፈ በኢትዮጵያ ጉዳይም ይሁን በፓርቲው ውስጥ መሰረታዊ ውሳኔ ይወሰናል ተብሎ አይጠበቅም።ልብ ትርታ የማዳመጥ፣ አቅም የመፈታተሽና ወዳጅ የማወቅ ሊሆን ይችላል።

The post የኢህአዴግ ም/ቤት የመጀመሪያ ቀን ውሎ (አያሌው መንበረ) appeared first on ሳተናው: የዕለቱ ዜናዎች እና ሰበር ዜናዎች – መረጃ ማግኘት መብትዎ ነው!.

የኢህአዴግ ም/ቤት የመጀመሪያ ቀን ውሎ (አያሌው መንበረ)