በ9 ወራት ኢትዮጵያን ከጎበኙ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢትዮጵያን ከጎበኙ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለከፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ነው።

የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳስታወቁት፥ ሀገሪቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ500 ሺህ በላይ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎችን አስተናግዳለች።

በዘጠኝ ወራቱ ኢትዮጵያን ከጎበኙ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች 2 ነጥብ 57 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱንም ነው ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው ያስታወቁት።

ዶክተር ሂሩት አያይዘውም፥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ በተሰራው ስራም፤ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር 23 ሚሊየን ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል።

ከቅርስ እድሳትና ጥገና ጋር በተያያዘም የአክሱም፣ ላሊበላ እና የጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግስት እድሳትን ለማከናወን በጥናት ላይ መሆኑን ገልፀው፤ በቅርቡ ወደ እድሳት ስራው ይገባልም ብለዋል።

በተጨማሪም ከቅርሶች  ምዝገባ  ቁጥጥር  ጋር በተያያዘ  የድሬ ሸክ ሁሴን እና የሶፍ ኦመር ዋሻን  እንዲሁም  በተለያዮ  አካባቢዎች የሚከናወኑ የአሽንዳ  ክብረ በአላትን  በዮኔስኮ  ለማስመዝገብ  የማስመረጫ  ሰነዶች መላካቸውንም አስታውቀዋል።

በፓርኮች ከሚከሰተው የእሳት አደጋ ጋር ተያይዞ ከምክር ቤቱ ለቀረበላቸው ጥያቄም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት በሰጡት ምላሽ፥ በፓርኮች ላይ የሚከሰተው የእሳት አደጋ መፍትሄ እንዲያገኝ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል።

በየጊዜው የሚከሰተውን የእሳት አደጋን የመከላከሉ ስራ ትኩረት እንዲሰጠው በማድረግ  ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ እየተሰራበት መሆኑን አስታውቀዋል።

 

በ9 ወራት ኢትዮጵያን ከጎበኙ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ