የለማና ገዱ ወደ ማዕከላዊ መንግስት መምጣትና አንዳንድ ነገሮች (ሰርፀ ደስታ)

የገዱና ለማ ሹመት፡-በዛሬው የለማና ገዱ ሹመት ብዙው ሕዝብ ቀዝቀዝ ባለ ስሜት ግን የተቀበለው ይመስላል፡፡ እምብዛም የከፋውም የተደሰትም ያለ አይመስለም፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ብዙ ከጠበቅን የጠበቅንው ነገር ሳይሳካ ሲቀር ችግር ይፈጠራል ብዙም ከተቃወምንው ከጀምሩ መልካም ሊሠራ የታሰበውን ልናበላሽ እንችላለንና፡፡ ይሄ ሹመት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በመሆኑ ቢያንስ የሆነ ጥሩ ዓላማ ይኖረዋል ብለን ተስፋ እናድርግ፡፡ የአማራው ክልል ፕሬዘዳንት ጉበዝ ነው እያሉ ያወሩለታል አዲስ የመጣው የኦሮሚያው ክልል ፕሬዘዳነት ምን ያህል ጎበዝ እንደሆነ እንጃ፡፡ የኦሮሚያ ክልል ችግሮች ደግሞ ከሁሉም የከፋ ነውና፡፡ ይክልሉን ችግር ለአዲስ ሰው ማስታቀፍም ልክ ላይሆን አይሆንም፡፡ አዲስ የምለው ለቦታው እንጂ ተሷሚው በክልሉም በፌደራልም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ላይ እንደነበር ሳላውቅ ቀርቼ አደለም፡፡ ማዕከላዊ መንግስቱም ትኩረት ሰጥቶ ያግዘዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የለማም ወደዛ መሄድ ለዚሁ ታስቦ ይሆናል ግን እንደተለመደው የክልሉን ጉዳይ የራሱ በሚል ከተተዋ ችግር ነው፡፡

ለማ በመከላከያ ሚኒስቴር ምን ሊሠራ ነው?፡–  አንዳንዶች ጭራሽ መከላከያውን በኦሮሞ ለማስያዝ ነው የሚል ትችት ሲያቀርቡ አይቻለሁ፡፡ ለእኔ ሄኛው ስጋት ሊያውም ከለማ ጋር አይታየኝም፡፡ የእኔ ጥያቄ ለማ እዚህ ቦታ ምን ሊሰራ ይችላል ነው፡፡ እኔ እስካሁን እንደታዘብኩት እንደውም ይሄ ቦታ የሚሰጠው ዝም ብሎ ስልጣኑን ብቻ ይዞ ለሚቀመጥ ሰው ነው፡፡ ይሄን ቦታ የሚፈልገውም ያለ አልመሰለኝም፡፡  እንግዲህ ለማን ወደዚህ ቦታ ማምጣት በእርግጥም ታስቦበት የሆነ ሥራ ለመስራት ከሆን ጥሩ፡፡ መከላከያው አዛዡ ብዙ ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒሰቴሩ ቀጥሎ በዋናነት የታማጆር ሹሙ የሚመራው፡፡ የአንድ አገር መሪ የመከላከያውን ኃይል የማዘዝ ሥልጣን የሁሉም አገሮች አሰራር ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የመከላከያ ሚኒስቴር ምን ያህል ተፅኖ ፈጣሪ እንደሆን አላውቅም፡፡ በኢትዮጵያ በተለይ የወያኔ ዘመን ግን የመከላከያ ሚኒሰቴር ምንም ማለት አደለም፡፡ምን ዓለባት በደርግና ንጉሱ ዘመን ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ አላት ተብሎ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አይታመንም፡፡ መከላከያው ከጀምሩ ሥሙ ኢሕአዴግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ሙሉ በሙሉ ወድሞ የኢሕአዴግን ሥልጣን ለመጠበቅ በተዋቀረ ኃይል መተካቱ ግልጽ ነው፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ሰው ወታደር ሲያይ ኢሕአዲጎች መጡ ነው የሚለው፡፡ በእርግጥም የመከላከያው አዛዦች የፓርቲ ስልጣን ያላቸውና በየፓርቲው ሥብሰባ የሚካፈሉ ነበሩ፡፡ አሁን አብይ በአዲስ መልክ አደራጀነው የሚለው እንዴት እንደሆነ አላውቅም፡፡ ያም ሆንኖ በመሠረታዊ አደረጃጀቱ አልተማመንበትም፡፡ መከላከያ መሠረት ሲኖረው ምን እንደሚያደርግ በግብፅ ሙባረክ ሲወረዱ፣ ከዛም በኋላ ግብፅ ተደጋጋሚ የመሪዎች ቀውስ በገጠማት ጊዜ ሁሉ አገሪቱንና ሕዝቡን ከጥፋት የታደገው መከላከያ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሰሞኑን በሱዳን ያየንው እንደዛ ነው፡፡ ቀጥሎ አምባ ገነናዊ ወታደራዊ መንግስት እንኳን ቢሆን መከላከያው አገራዊ መሠረት ላይ ስላለ በአገር የመጠበቅ ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡ ኃይለሥላሴ ከሥልጣን ሲወርዱ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በመሆኑ የቱንም ያህል ቀውስ ቢፈጠር ያው የኃይለሥላሴ መከላከያ በደርግ ስልጣኑን ወደራሱ አድርጎም ቢሆን ቀጥሏል፡፡ የአሁን የኢትዮጵያ መከላከያ የተባለው አደረጃጀት ግን እንጃለት ኢሕአዴግ ቢወድቅ አብሮ ሊናድ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ አገር አንድ ችግር ቢደርስባት እንደ ሱዳኖቹ በትረ መንግስቱን ተቆጣጥሮ ለጊዜው ሊመራ የሚችልበት ቁመና አለው ብዬ አላምንም፡፡ ይሄ በኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ ምክነያት መሠረቱ ስለጠፋ እንደ ኢትዮጵያ የሚያስብ ምን ያህል አዛዞች እንዳሉ አላውቅም፡፡ ግን ችግር አለ፡፡ እንግዲህ ለማ ይሄን ለማከም መጥቶ ከሆነ እንጠብቅ፡፡

አብንና ኦነግ፡- ሰሞኑን የሰጠሁትን አስተያየት ተከትሎ ስለአብን አንዳች ነገር ሳትናገር ኦነግን ብቻ ትኮንናለህ የሚል ነው፡፡ ውድድሩ ራሱ ለእኔ የሚገርም ነው፡፡ አብንን ከኦነግ ጋር ማወዳደር አሁን እውነትን ላለመቀበል ከአልሆነ አብንና ኦነግ ሊወዳደሩ አይችሉም፡፡ ሲጀምር ብዙዎች ያልተረዱት ነገር የአብን በአሁን ፖለቲካ ያለውን ሰላማዊ ተጽኖ ፈጣሪነት ነው፡፡ አብን ውስጥ ያልበሰሉ ሰዎች አሉበት ግን ለአገርም ሆነ ለማንም ስጋት አደሉም፡፡ ይልቁንም መንግስት ራሱ እየተጠቀመበት ያለ ቡድን ነው፡፡ በተለይ በለጠ የሚበለውን የአብን ቡድን ምክትል በብዙ አጋጣሚ አሁን ያለው የአብይ አመራር ሲጠቀምበት እናያለን፡፡ አብን የአማራ ቢሔር ወኪል ነኝ ብሎ የተደራጀ ቡድን ነው፡፡ ሆኖም በዜግነት ፖለቲካ የሚያምን ነው፡፡ እንደውም ከማንም በላይ ለዜግነት ፖለቲካው በተግባር እየሰራ ያለና ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሱ ጉዳዮችን ትኩረት እንዲሰጣቸው ያደረገ ነው፡፡ አሁን አብን ሥጋት እየሆነ የመጣው በእርግጥም ለኦነጋውያን ነው፡፡ ስለ አብን እኔም ከዚህ በፊት ተችቼ ነበር፡፡ አሁንም ውስጡ ያልበሰሉ ሰዎች አሉ ወይም ችግርም ያለባቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መሰረታዊ ፍልስፍናን በዋናነት የሚመሩት እንደነ በለጠ የመሣሰሉት ግን ትልቅ አስተዋጾ በተግባር እየሠሩ ነው፡፡ አብይ ራሱ ለማስተማሪያነት እየተጠቀመባቸው ነው፡፡ የሚገርመው ስህተት ሲሰሩ ራሱ ትክክል አደላችሁም ተብለው ይነገራቸዋል፡፡ ለማስፈራራት ወይም በጥላቻ ሳይሆን እንዲጠነክሩ በማሰብ ነው፡፡ አሁን አብን እየተከተለ ያለው ፖለቲካ በተለይ በእነ በለጠ የሚካሄደው ዜጎችን ሙሉ መብት እንዲኖራቸው ነው፡፡ በእርግጥም በተግባር ይሄ እንዲሆን እያደረገ ያለ ብቸው ቡድን ማለት የቀላል፡፡ እንደ አብን እምነት ሁሉም ቦታ ዜጎች በሚኖራቸው ድምጽ ስልጣንና መብታቸው ይከበር ነው፡፡ ይሄ አሁን ላለው የዘውጌ ፖለቲካ አደጋ ነው፡፡ ለዛም ይመስላል በልጅ አመካኝቶ አይነት አብንን ሁሉም የአፍ ማሟሻ ያደረገው፡፡ እውነቱ እንደ አብን አካሄድ አዲስ አበባም አዳማም፣ አዋሳም ድሬዳዋም የነዋሪዎቻቸው ናቸው፡፡ ምን አልባት የያዝኩት አማራወን ነው በሚል ሊመስል ይችላል፡፡ ግን ከዛ በላይ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ በየቀኑ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ አማካሪ እስከሚመስሉ ድረስ በሠላማዊና በሠለጠነ መልኩ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በተግባር እያሳደገ ያለውን አብን 50 ዓመት በጸረ- ኢትዮጵያዊነት የዘረኘንትና ጥላቻ ፖለቲካ የመረቀዘውን ብዙ ሕዝብም እየበከለ ያለውና አሁን አገር ታጥቆ በውንብድና ተግባር ከተሰማራው ኦነግ ጋር ማወዳደር አይቻልም፡፡ አብን ከፌደራሉም ሆነ ከክልሉ ጋር ጸብ የለበትም፡፡ ሲያጠፋም ተው በተባለበት የሚቆም ነው፡፡ ይሄን ወዶ ብቻም ሳይሆን ግዴታውም ጭምር ስለሆነ ነው፡፡

የባይሳ ዋቅ ጅራ በዳዊት ወልደ ጎርጊስ ላይ ትችት፡- ከባይሳ ጋር የምንስማማባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እኔ የአቶ ዳዊትን ጽሁፍ አላነበብኩም፡፡ ሆኖም በተለያዩ ሚዲያዎችና ማህበራዊ ድረ-ገጾች ስለዚሁ አንስተው ሲያወሩ ከሰማሁት በቀር፡፡ እንደ እውነቱ በሰማሁት አይነት ከሆነ (ይመስለኛልም ከባይሳም አተቻች ይሄኑ ነው የምረዳው) አቶ ዳዊት ትክክል አይመስሉኝም፡፡ የአገርን መውደቅ መናፈቅ ይመስልባቸዋል፡፡ ቢሆን እንኳን በዚህ መልኩ ሳይሆን በውስጥ ማሳሰቢያቸውን ሊነግሩ የሚችሉበት እድል መፍጠር ይችላሉ ባይ ነኝ፡፡ችግር እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ግን አገርን ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ መናገር ከአገር አሳቢነት ጋር አይሄድም፡፡ እንደውም እንዲህ ያለውን አስጊ ነገር ለሕዝብ ማውጣት ሕዝብን ተስፋ ማስቆረጥ ነው፡፡  ባይሳ ከአገር ሁኔታ ጋር ዳዊትን ቢተች ጥሩ ነበር፡፡ ሆኖም ትችቱ በኦሮሞነት ሆነ አልተመቸኝም፡፡ እኔ በጀዋር የአስተሳሰብ ሥር የወደቁ ሰዎች የሚያስቡት አስተሳሰብ ይገርመኛል፡፡ ጀዋር ተጽኖ ፈጣሪ ያደረጉት አላዋቂዎች ናቸው፡፡ ግለሰቡ ተቀዳሚ ስራው ንግድ ሲሆን የንግድ መሠረቱ ደግሞ አሁን ያለው የዘር ፖቲካ ነው፡፡ ይሄን እጅግ ይፈልገዋል፡፡ በሚሊየን የሚቆጠር ኦሮሞ የእሱ የአስተሳሰብ ባርነት ውስጥ እንዲወድቅና የንግድ ዕቃው እንዲሆን እንድል ሰጥቶታልና፡፡ ይሄ ከፈረሰ ጀዋርም ሆነ አሁን ጭራሽ የግል ነብረቱ ያደረገው ሚዲያው ያበቃላቸዋል፡፡ ሠላም ከሆን ምን ሊያወሩበት? ምን አልባትም ይሄ ግለሰብ ኢትዮጵያዊ ዜግነት የለውም፡፡ የሆነ ሆኖ የጀዋር ፖለቲካ ምን እያደረገ እንደሆነ ጊዜ ሳገኝ የደረስኩበትን እገልጻለሁ፡፡ ሌላው ባይሳ ያነሳው ዜጎች በየክልሉ የመኖር መብት እንዳላቸው የፌደራሉም ሆነ የክልሉ ሕገመንግስት ይፈቅዳል የሚል ነው፡፡ ባይሳን መጀመሪያ የየክልሎቹን ሕገ መነግስት የተባለውን እንዲያነብ እጋብዛለሁ፡፡ ለጊዜዎ ግን እስኪ የኦሮሚያን ከዚህ በታች ልተውልህ ለማነጻጸር የአማራንም ተመሳሳይ አንቀጽ፡፡ በዚህ አገላለጽ የኦሮሚያ ሕገመንግስት ከኦሮሞ ውጭ ላማንም የዜግነት መብት አይሰጥም፡፡ የክልሎ ሥልጣን የኦሮሞ ሕዝብ ነው ይላል እንጂ የኦሮሚያ ሕዝብ ነው አይልም፡፡ ይሄ ከአማራው ክልል ውጭ ሁሉም ተመሳሳይ መሠለኝ፡፡ ደጋግሜ ተናግሬያለሁ፡፡ እንደክልሉ ሕግ የኦሮሞ ከጂገጂጋ መፈናቀል ትክክል ነው፡፡ የሱማሌም ክልል ይሄው አንቀጽ ስላለው፡፡ ትርጉም ካለፈለግናችሁ የማስወጣትም የማኖሩም ሥልጣኑ የእኛ ነው ነው፡፡ በፍጹም በሕግ ሊያውም በሕገ-መንግስት መስፈር የሌለበት ነው፡፡ ለማንኛውም ግን የችግሮቹ ሁሉ መነሻ ሕገ መንግስት የተባለው እንደሆነ አረጋግጥልሀለሁ፡፡ አንብበው፡፡ አብዛኛው ሰው ሕገ መንግስት የሚባሉትን ሳያነብ በሥማ በለው ነው የሚያወራው፡፡ እባካችሁ አንብቡት፡፡ ለማንኛውም ለባይሳ እንሆ የኦሮሚያው ከግራ የአማራው ከቀኝ፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር አገራችንንና ሕዝቧን ይባርክ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

The post የለማና ገዱ ወደ ማዕከላዊ መንግስት መምጣትና አንዳንድ ነገሮች (ሰርፀ ደስታ) appeared first on ሳተናው: የዕለቱ ዜናዎች እና ሰበር ዜናዎች – መረጃ ማግኘት መብትዎ ነው!.

የለማና ገዱ ወደ ማዕከላዊ መንግስት መምጣትና አንዳንድ ነገሮች (ሰርፀ ደስታ)