ያልተከፋፈልንበትን ፈልጉና ንገሩኝ (ግርማ በላይ)

ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ በዘርና መሰል ጉዳዮች የተከፋፈሉት በዚህ ዘመን ነው፡፡ ቀጣዮቹን ልብ በሉ፤

 • ባንኮችና ዘረኝነት፡ – 1. አዋሽ ባንክ … ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ … ወጋገን ባክ፣ አንበሣ ባንክ፣ …3. ዳሸን ባንክ፣ አባይ ባንክ፣ …  4. ንብ ባንክ፣ ቡና ባንክ፣ ኅብረት ባንክ…
 • ባንኮችና ፆታ – እናት ባንክ፣ አባት ባንክ (በዚህ ከቀጠልን ወደፊት ሳይመሠረት አይቀርም)
 • ባንኮችና ሃይማኖት – ብርሃን ባንክ…
 • ተንቀሳቃሽ ንብረትና ዘረኝነት – ለአብነት የመኪና ታርጋዎች – አማ 000፤ ትግ 0000 ፤  አሮ 00000  …
 • ዘረኝነትና ሃይማኖት – አቡነ አረጋይ… አቡነ ተክለ ሃይማኖት … አቡነ ኪሮስ …
 • ዘረኝነትና ሚዲያ – ኦኤም ኤን፣ ኦቢኤን፣ ኦቢኤስ፣ ኦኤንኤን፣ አማራቲቪ፣ ትግራይቲቪ፣ ዲምፂ ወያነ ቲቪና ሬዲዮ…
 • ዘረኝነትና ሥልጣን – ጠ/ሚኒስትር፣ መከላከያ ሚኒስትር፣ ምርጥ ምርጥ የፌዴራል የሚኒስቴርና ሌሎች የኃላፊነት ቦታዎች…
 • ዘረኝነትና የቦታ ስሞች ውዝግብ – አዲስ አበባ/ፊንፊኔ፣ ናዝሬት/አዳማ፣ ደብረ ዘይት/ ቢሾፍቱ፣ …
 • ጎጠኝነትና የቦታ ስያሜዎች – አዲስ አበባ/በረራ/ሸገር፤ አጣየ/ኤፌሦን፤ ደብረ ማርቆስ/ መንቆረር….
 • ዘረኝነትና የሰው ስሞች – ሌንጮ ለታ/ዮሐንስ ለታ፣ አባዱላ/ምናሤ፣ ኩማ ደመቅሳ/(እውነተኛ ስሙን ረሳሁት)፣
 • ቋንቋ ላይ የተመሠረተ ዘረኝነትና ክልል – ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌ፣አፋር…
 • ዘረኝነትና ልማት – ጎንደር አቧራ፣ መቀሌ ፓሪስ፣ ውቅሮ አበባ/ወልዲያ ላባ፣ አክሱም ለንደን/ደብረ ታቦር አሌፖ
 • ዘረኝነትና ትምህርት – ትግራይ አሜሪካ/ አማራ ኒጀር፣ መቀሌ ቀለሚኖ/ባህር ዳር ማይሚኖ …. ፐ! ፐ! ፐ! ፐ! ምን ዓይነት ዘመን ናት መጥታ በማለፍ ላይ ያለችው ጎበዝ! በዚህች አጭር ዕድሜየ ይህን መሰል ግራ አጋቢ ሰይጣናዊ ለውጥ አያለሁ ብዬ እንኳንስ በውኔ በልሜም አስቤው አላውቅም፡፡ አገሬ ላይ ቁጭ ብዬ በሰው ሀገር ውስጥ ያለሁ ይመስለኛል፡፡
 • አላስፈላጊ የቃላት ጨዋታ – ግልጸኝነት(ግልጽነት ለማለት)፣ ሕዝበኝነት (ሕዝባዊነት ለማለት)፣ አቅጣጫ ማስቀመጥ፣…

… የፈለገውን ወርቅ ንግግር ቢናገር፣ የፈለጋትን ወርቅ ንግግር ብትናገር ሚስቱ የማትሰማው፣ ባሏ የማይሰማት እንደዘመኑ ኢትዮጵያውያን፣ እንደክፍለ ዘመናችን የሀበሻ ባቢሎናውያን የማይደማመጡና  የማይግባቡ ባልና ሚስት ነበሩ – ዱሮ፡፡ ባል “እንሂድ” ሲል ሚስት “እንቀመጥ”፣ ሚስት “እንተኛ” ስትል ባል “እናውራ”፣ ባል “እንብላ” ሲል ሚስት “እ…ራ” (መጸዳጃ ቤት እንሂድ) የሚሉ ሆን ብለው በሚመስል መንገድ ተቃራኒ ሆነው ግን በአንድ ጣርያ ሥር የሚኖሩ ጅሎች ነበሩ – እነኚያ ባልና ሚስት፡፡

አንድ ምሽት አንድ አሳደሩኝ ባይ ጥቁር እንግዳ ወደነዚህ ባልና ሚስት ቤት መጣ፡፡ በዚያች ብቻ ተስማሙና ሊያሳድሩት ወደዱ – “ቤት የእግዜር ነው” ይባላልና ለነፍሳቸው ሲሉ በዚህች ብቻ አንድ ሆኑ፡፡ እራት ተበላ፤ ቡና ተጠጣ፡፡ የምኝታም ሰዓት ደረሰ፡፡

ባል – እኔና እንግዶ እዚህኛው መደብ ላይ እንተኛለን – አንቺ ልጆችሽን ይዘሽ ቆጡ ላይ ተኝ፡፡

ሚስት – የለም!  እኔና እንግዶ እዚህ መደብ ላይ አንተ ልጆችህን ይዘህ እቆጥ ላይ፡፡ የባል ክርክር ዋጋ አልነበረውም ….

ዘመን አለፈ፡ ዘመን ተተካ፡፡ ሞት ለማንም አይቀርም፡፡ ሴትዮዋ ወንዝ ስታቋርጥ ደራሽ ጎርፍ ወሰዳትና መሞቷ ለባል መርዶ መጣለት፡፡ ሬሣውን ለማግኘት ግን ችግር ሆነ፡፡ ሁሉም በያቅጣጫው ቢፈልጋትም ልትገኝ አልቻለችም፡፡ ያኔ ባል አንድ ነገር ትዝ አለውና አስከሬን ፈላጊው መንደርተኛ ሁሉ ወደርሱ እንዲመጣ ጮክ ብሎ ተናገረ፡፡  ከዚያም እንዲህ አላቸው “ውድ ጎረቤቶቼ! ሚስቴን ወደታች መፈለግ አድካሚ ነው፡፡ ከወንዙ መውረጃ በተቃራኒ ወደላይ እንፈልጋት፡፡ ምክንያቱም ነገረ ሥራዋ ሁሉ የተገላቢጦሽ ስለነበር ለውኃውም አትታዘዘውም፡፡ ስለዚህ ወደታች ሳይሆን ወደላይ ነው ይዟት የሚመለስና ሽቅብ እንፈልጋት፡፡ ገባችሁ ወገኖቼ?”

አዎ፣ የኛም ነገር ከዚህ የተለዬ አይደለም፡፡ ሁለ ነገራችን እንዳይሆን እንዳይሆን ነው፡፡ ቆም ብሎ ላየው ሰው የዚህች ሀገር ነገር የህልምና የቅዠት እንጂ የእውን አይመስልም፡፡ ለነገሩ የመላው ዓለም ሁኔታም ከዚህ ብዙም የሚለይ አይደለም፡፡ የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች አንድ በአንድ በሁሉም ሥፍራ እየተገለጡ ነው፡፡ እምቢልታ ነፊውን መልአክ ዕንቅልፍ ቢጤ አታልሎት ሸለብ አድርጎት የፈጣሪን ትዕዛዝ እያዛባ መሆን አለበት እንጂ ወቅቱ እያለፈ ነው፡፡ ከኔ የጉርምስና ዘመን ጀምሮ ዓለም እጅግ እንደተከፋች አለች፡፡…

ማይምነት ገነነ፡፡ ዕውቀትና ጥበብ ጠወለጉ፡፡ ቅንነትና መተሳሰብ በጥልቅ ጉድጓድ ተቀበሩ፡፡ መተዛዘንና መተሳሰብ ገደል ገቡ፡፡ ሆድ ነገሠ፤ ኅሊና ታወረ፤ ፍትኅ ጠፋ፤ ጎሠኝነትና ዘረኝነት የኅሊና ሚዛንን አንሻፈፉት፡፡  ሰውነት ረከሰ፣ ገንዘብ ተመለከ፤ ሃይማኖት በከርስ ከመለወጡም በተጨማሪ የአጭበርባሪዎችና የአጋንንት ሎሌዎች ቁማር መቆመሪያና የግል ፒኤልሲ ሆነ፤ … ያልሆነ ነገር ቢኖር በቅርቡ እንደሚሆን የሚጠበቀው የምፅዓት ቀን በይፋ መከሰት ብቻ ነው፡፡ ያልተባለ አልሆነም፤ ከተባለውም ሣይሆን የቀረ የለም፡፡

ሶዶምና ገሞራ በሚጠፉበት ወቅት፣ ቀድሞም በኖኅ ዘመን ምድር በንፍር ውኃ እየጠፋች በነበረበት ቅጽበት ሰዎች ኅሊናቸው ታውሮ፣ ዕዝነ-ልቦናቸው ደንቁሮ እየወረደባቸው የነበረውን የቅጣት ዶፍ በአካላዊ ዐይኖቻቸው  እየተመለከቱ እንኳን እየሆነ የነበረው አልገባቸውም ነበር፡፡ እኛም እንደነሱ ሆነን ዐረፍነው፡፡ የኛን ኃጢኣት ከነሱ የሚያከፋው ግን በኛ ዘመን ዕውቀትና ጥበብ እንደልብ መገኘታቸው፣ መምህራንና መጻሕፍትም በየትም ሥፍራ መዳረሳቸው ነው፡፡ አስተዋይነት በመጥፋቱ ግን አልተጠቀምንባቸውም፡፡ አንድ ሰው ማወቅ እየተገባው አለማወቅን መርጦ በገዛ ፈቃዱ ከደነቆረ ደግሞ ከፍርድ አያመልጥም፤ አመክሮ የሌለው ጥፋትም እያጠፋ ነው፡፡

The post ያልተከፋፈልንበትን ፈልጉና ንገሩኝ (ግርማ በላይ) appeared first on ሳተናው: የዕለቱ ዜናዎች እና ሰበር ዜናዎች – መረጃ ማግኘት መብትዎ ነው!.

ያልተከፋፈልንበትን ፈልጉና ንገሩኝ (ግርማ በላይ)