Menu

ህገ ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ተጨማሪ 36 አዳዲስ ኬላዎች ተቋቁመዋል-የገቢዎች ሚንስቴር

ለህገወጥ የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ዝውውር ስጋት ናቸው የተባሉ ቦታዎችን በመለየት ተጨማሪ 36 አዳዲስ የጉምሩክ ኬላዎች መቋቋማቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡

አዳዲስ ኬላዎችን በመክፈት እንዲሁም ቦታቸው ትክክል ያልነበሩ ነባር ኬላዎችን ወደ ትክክለኛ ቦታ በመቀየር ህገወጥ የገንዘብና የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ይርጋ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመከላከል በተደረው ጥናት በኬላዎች ላይ 1 ሺህ 400 የፖሊስ ኃይል እንደሚያስፈልግ ተለይቷል ፡፡

ጥናቱን ተከትሎ ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ ስምሪቱ በጉምሩክ ኮሚሽን የሆነ ጥሩ ስነ ምግባር የተላበሰ፣ ለቦታው የሚመጥን የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ፖሊስ እንዲቋቋምና ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የተጠናከረ የጉምሩክ ስርዓት እና የተጠናከረ ኬላ ፍተሻ ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን ተከትሎ የሚያዙ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችና ገንዘቦችም ጨምረዋል ነው የተባለው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጀላል አብዲ በበኩላቸው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ የራሳቸውን ገንዘብ ለማግኘት በሚንቀሳቀሱ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ወደ ሃገር ውስጥ ይገባል ብለዋል፡፡

የጦር መሳያዎቹን መዳረሻ ለማወቅ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም ከሁኔታ ግምገማ በመነሳት በሃገር ውስጥ ጸጥታና የደህንነት ስጋት ያለ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ራሱን እና ንብረቱን ለመጠበቅ የጦር መሳሪያ ፍላጎት እንደ አንድ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል ብለዋል፡፡

የታጠቁ ቡድኖችም የጦር መሳሪያው መዳረሻ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁመዋል ዳይሬክተሩ፡፡ የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት መሆኑ ይታዋሳል፡፡

FBC

ህገ ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ተጨማሪ 36 አዳዲስ ኬላዎች ተቋቁመዋል-የገቢዎች ሚንስቴር