የ+ኦሮማራ ፖ+ለ+ቲካ++ም አይዘልቅም! በኢትዮጵያዊነት ማሰብ ካልተቻለ! (ሰርፀ ደስታ)

ሰሞኑን አዲስ የኦሮሚያ ፕሬዘደንት ሆኖ የተሾመው ወጣት የሚመስለው ሽመልስ አብዲሳ ብዙዎች ጎበዝ አስተዋይ እንደሆነ እየተናገሩለት ነው፡፡ ይሄ መልካም ነገር ነው፡፡ የሚፈለገውም ይሄው ነው፡፡ ሽመልስ አሁን ሰዎች እንደሚያወሩለት ከሆነና እገዛ ካገኘ የተፈለገውን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ይህ ሲባል እደግመዋለሁ ቢያንስ አብዛኛው ሕዝብም ሆነ በስልጣን ላይ ያሉት ከተባበሩት ነው፡፡ በተመሳሳይ የአማራው ክልልም አምባቸው እንዲሁ ይወራለታል፡፡ እንግዲህ ከአንጀት ከአለቀሱ ነው፡፡ የፌደራል መንግስቱም እንደ ኢትዮጵያ መንግስት (ከፌስቡክ ፖለቲካ ወጥቶ) መሠረት ባለው ነገር መሥራትና ክልሎቹን ወደሚፈለገው ለውጥ መምራት ከቻለ የተናፈቀው ለውጥ ይመጣል፡፡

ይሄ በዚህ እንዳለ የኦሮማራ ፖለቲካ ከዚህ መዝለል የለበትም፡፡ እንግዲህ እንደመንግስት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያማከለ እንጂ የሁለት ብሔረሰብን በአላስፈላጊ ሁኔታ የፖለቲካ ሙቀት መስጫ ማድረግ ጥሩ አደለም፡፡ የመንግስትነት ኃላፊነትንም ያስረሳል፡፡ ሌሎችን ማስታወስንም ያስረሳል፡፡ አሁን ራሱ እየሆነ ባለው እኔ ያልተመቹኝ ነገሮች አሉ፡፡ ሥልጣን ሲባል እየታሰበ ያለው ስንት አማራ ስንት ኦሮሞ ነው እንጂ ኢትዮጵያዊነት አደለም፡፡ የፌደራል ስልጣኑ ፉክክር አሁን በአማራነትና በኦሮሞነት ይመስላል፡፡ ይሄ ጉዳይ አሁኑኑ ይታሰብበት፡፡ አንዳንድ መ/ቤቶች ሙሉ ዋና መዋቅራቸው ወይ በአሮሞ ወይ በኦሮሞ የሆነም ይመስላል፡፡ እዛው እንኳን በአንድ ተቋም ተሰባጥሮ ስልጣን መያዝ ሳይሆን ተቋማቱን የመከፋፋፈል አይነት ይመስላል፡፡ እንግዲህ ከቀደመው ከወያኔ የተወረሰ ባሕል ከአልሆነ ሕጉም፣ መንግስታዊ አሰራርም፣ የማህበረሰባችንም ሁኔታ ይሄን የሚፈቅድ አይመስለኝም፡፡ ይሄ አደጋ እንዳለው በደንብ ይታሰብበት፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከአራቱ ቡድኖች እንኳን ሕወሐት ገሸሽ ተደርጓል፡፡ ከደቡብ ጭራሽ ትዝም ያለው ያለ አይመስለኝም፡፡ የሠላምሚኒስቴር በሚል (መኖር የሌለበት፣ ምንም ያማይሰራ) ከተሰየሙት በቀር ሌላ አልታየኝም፡፡ ከተሳሳትሁ አላውቅም፡፡ አጋር ተብለው ከኖሩትም ብዙ ስንጠብቅ አሁንም ያው ነው፡፡ ለምሳሌ ከሱማሌ ክልል ጥሩ ጥሩ እውቀትና ፍልስፍና ያላቸው ሰዎች አሁን በክልሉ ፖለቲካ ተሳታፊነት እየገቡ ይመስላል፡፡ ሙስጠፌን ወደ ፌደራል ማምጣት አሁን ጊዜው አለመሆኑንና የበለጠ ሥራም ሊሰራ የሚችለው በሱማሌ ክልል እንደሆነ ብረዳም ሌሎች ግን በፌደራል ደረጃ በተሻለ እውቀት ሊመሩ የሚችሉ የክልሉ ተወላጆች አሁን እየተነበቡ ይመስላል፡፡ በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ አቅም ያላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የፌደራል መንግሽቱ ከብሔር ተዋጽኦ ይልቅ በአገር ደረጃ ሊሰሩ የሚችሉ ሰዎችን ወደ ሥልጣን ማምጣት አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይሄ እግረ መንገድ ከዘር ፖለቲካ የምንወጣበት አንዱ ግብዓተም ሊሆን ይችላልና፡፡ እንደአስፈላጊነቱ ከአጋ ርም ከአራቱም ቡድን ውጭ የሆንን ሰው መመደብም ያስፈል

ል፡፡ በተለይ በተለይ ከፖለቲካ ይልቅ ሙያን በሚጠይቁ ተቋማት፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከትግራይ ሕዝብም የፖለቲካውን ተሳትፎ በአዳዲስ ወጣት ፖለቲከኞች ቢተካ ጥሩ ነው፡፡ አሁንም ስናይ ሕወሐት የተያዘው በ60ዎቹ ትውልድ መሆኑም ብቻ ሳይሆን ጥሩ ባአልሆነ አይዶሎጂ የተሞሉ ናቸው፡፡

በባለፈው ጽሁፌ አንድ አለም የተባሉ አስተያየት ሰጭ ስለ አንባቸው ጉብዝና አንስተህ ስለ አዲሱ የኦሮሚያ ፕሬዘደንት አላውቅም ማለትህ ማንነትህን ያሳያል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አይቸኩሉ እስኪ ሠርፀ መረጃው ካለው በዚህ አይታማም፡፡ ለማንኛውም በእርግትም መረጃው ስለሌለኝ ነው፡፡ ስለ አንባቸው ቀደም ተብሎ ብዙዎች ሲያወሩ ስለሰማሁ ነው፡፡ ይሄው በጥቂት ቀናት ስለሽመልሽም የተለያዩ ሰዎች ምስክርነታቸውን እየገለጹ ነው፡፡መልካም እንግዲህ የምንፈልገውም እንደዛ ነው፡፡ በተመሳሳይ የአማራንና ኦሮሚያን ሕገመንግሰት የአማራን ሁለት ንዑስ አንቀጽ አስቀምጠህ የኦሮሚያን ሆን ብለህ ቆረጥከው ሊሉ የፈለጉ መሠለች አለም፡፡ሁለቱንም ራስዎ ቢያነቡት ጥሩ ነበር እኔ ቆርጬ የለጠፍኩትን ትተው፡፡ ለማንኛውም ሁለቱም ያቺ አንቀጽ እንደተጻፈችው ነው የለጠፍኩት፡፡ የኦሮሚያው ብንዑስ አንቀጽ አልተከለም፡፡ የአማራው በሁለት ንዑስ አንቀጽ ነው፡፡ የሁሉም ንዑስ አንቀጽ የለውም ከአማራ በቀር፡፡ ሻለቃ ዳዊትን አቶ ያልኩት ሳላስተውል ነው፡፡ ይቀርታ፡፡ ሆን ብዬ ግን አደለም፡፡ ብዙ ጊዜ እንደዛ ይቀናኛል፡፡ አሁንም እንደዛ መጻፌን ያየሁት ከእርሶ አስተያየት ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ለግለሰብ አስተያየት መልስ አልሰጥም፡፡ አስተያየትዎ ከልብ በሆነ ቅሬታ ስለመሰለኝ እንጂ፡፡

በመጨረሻም የክልላቱም ሆኑ የፌደራል መንግስቱ እንደመንግስት አቋምና እቅድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በአክቲቪስት ደሀ አስተሳሰብ እየተመሩ ብዙ ጊዜ አይተናል፡፡ ሲጀምር ዛሬ ማንም ተራ ተነስቶ አክቲቪስትና የፖለቲካ ተንታኝ የሆነበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ እውቀት የማያሻው መሆኑ እንጂ አገርና ሕዝብን ያሰበ ፖለቲካ ቢሆን ከሌሎችም አገራት በሣል ሰዎች ይታዩበት ነበር፡፡ አሁን የወንበዴዎች መፈንጫና መነገጃ ነው፡፡ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፖለቲካውን ብቻ ሳይሆን ወጣቱን ለልማት ሥራ ማሠማራት ግድ ይላል፡፡ ሥራ ያጣ ቀኑን ሙሉ ስለነገር ፌስ ቡክ ላይ አክቲቪስት ሆኖ ይውላል፡፡ መንግስት እንደመንግስት ራሱን ማረቅ ከቻለ የሥራ ፈጠራውን ብዙዎች አገር ወዳድ ዜጎች ሊያግዙት ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ምንም ያልተሰራች አገር ነች፡፡ እድሉን ቢያገኙ ከሚታሰበው በላይ አገር ሊለውጡ የሚችሉ ዜጎች ግን አሏት፡፡ አገራዊ ሠላሙንና ሕዝብን በትክክለኛ አስተሳሰብ መምራት የሚችል መንግስት ከተፈጠረ  ኢትዮጵያን የመቀየር ኃላፊነት የብዙዎች ነው፡፡ በባለፈው አመት አብይ ትንሽ ተስፋ የሰጠ በመምሰሉ ብዙዎች ለአገራችን ምን እናድርግ እያሉ መነጋገርና ራሳቸውንም ማደራጀት ጀምረው ነበር፡፡ እኔ ራሴ አንድ ኢትዮጵያን በሙያ ሊያግዝ ከተነሳ ትልቅ ኔትወርክ ውስጥ በአማልነት አለሁበት፡፡ አሁን ግን ብዙዎቻችን የነበረን ተስፋና ተነሳሽነት ቀዝቅዟል፡፡ ከመንግስት አምስት ሳንቲም ሳይጠይቁ ትልልቅ ፕሮጄክቶችን ለአገር ማበርከት የሚችሉ ባለሙያዎችን መንግስት እንደመንግስት ቆሞ ማስተናገድ ከአልቻለ አገር አታድግም፡፡ ከምንም በላይ ግን መንግስት ምንም የማያስተውሉ አክቲቪስቶችን አስተሳሰብ ከማስተናገድ እንዲታቀብ ያስፈልጋል፡፡ ይታሰብበት፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር አገራችንንና ሕዝባችንን ይባርክ! አሜን

ሰርፀ ደስታ

 

 

The post የ+ኦሮማራ ፖ+ለ+ቲካ++ም አይዘልቅም! በኢትዮጵያዊነት ማሰብ ካልተቻለ! (ሰርፀ ደስታ) appeared first on ሳተናው: የዕለቱ ዜናዎች እና ሰበር ዜናዎች – መረጃ ማግኘት መብትዎ ነው!.

የ+ኦሮማራ ፖ+ለ+ቲካ++ም አይዘልቅም! በኢትዮጵያዊነት ማሰብ ካልተቻለ! (ሰርፀ ደስታ)