የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የባለሙያዎች ቡድን በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የባለሙያዎች ቡድን በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ መወያየታቸው ተገለፀ።

ውይይቱም በኢትዮጵያ ተወካዮች፣ በፈረንሳይ መንግስት ተወካዮች እና በለሙያዎች እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ዓለም አቀፍ የቅርፅ ማዕከል መካከል ነው የተደረገው።

ውይይቱ በዓለም ቅርስነት በተመዘገቡት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ ለተጋረጠውን አደጋ ዙሪያ መፍትሄ ለማስቀመጥ እና መከላከል ያለመ ነው።

በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ እንደገለፁት፥ የኢትዮጵያ እና የፈረንሣይ የኤክስፐርቶች ቡድን በጋራ በመሆን ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የቱሪስት መዳረሻ የሆነውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለመጠበቅ የመፍትሔ ሃሳቦችን ያቀርባል።

አምባሳደር ሄኖክ የፈረንሳይ መንግስት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠገን የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱንም አስታውሰዋል።

ለዚህም ለፈረንሣይ መንግሥት በተለይም ለሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ምስጋና ማቅረባቸውን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።

በተያያዘ ዜና በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የአደጋ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

ዩኔስኮ ለሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የፋይናንስ ድጋፉን ያደረገው በኢትዮጵያ ጥያቄ መሰረት መሆኑን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።

የገንዘብ ድጋፉም ፓርኩ ላይ የደረሰውን አደጋ የሚያጠና እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መሠረት በማድረግ ሊወሰዱ ስለሚገቡ እርምጃዎች የመፍትሔ ሃሳቦችን የሚያቀርብ የኢትዮጵያ እና የዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ለመቀጥር የሚውል መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የባለሙያዎች ቡድን በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ ተወያዩ