የሕዝብን በደል ዳር ላይ ቆመው የሚያዩ “ምሑራን” ፕ/ር አሥራትን ሲያስቡ ማፈር አለባቸው! መሸማቀቅ አለባቸው!

ጌታቸው ሽፈራው

ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ አንቱ የተባሉ ምሁር ነበሩ። ታዋቂ ባለሙያ ነበሩ። የሙሁር ተግባር መፍትሔ ማምጣት ነው። የምሁር ሚና ለሕዝብ ማገልገል ነው። ይህ ሲሆን ግን ደሞዝ በሚቆረጥለት ስራው ብቻ አይደለም። አውቃለሁ ካለ በሚያውቀው ሁሉ ሕዝቡን ማገዝ ነው ምሁር ማለት። ፕሮፌሰር አሥራት የህክምና ባለሙያ ሲሆኑ ሀኪም ቤት የመጣውን በማከም ብቻ ግዴታቸውን አልወሰኑትም። የትም ለሚገደለው፣ ለሚጎዳው ሁሉ ሀኪም ሆኑ። ተቆጥሮ የተሰጣቸውን ብቻ ሳይሆን፣ በሚከፈላቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ምሁር የሰው ልጅ መጎዳት የለበትም ያላቸውን ሕሊናቸውን ሰምተው ለተገፉት ቆሙ። ስለተገፉት ቆመው፣ የሚገደሉትን እያዳኑ፣ ለማጥፋት የታቀደባቸው እንዳይጠፉ ሕሊናቸው ያዘዛቸውን ሰርተው አለፉ።

በዚህ ወቅት ምሁር ነኝ የሚለው ብዙ ነው። ነገር ግን የሚታጠረው በሚከፈለው ስራ ብቻ ነው። አሊያም ከቢሮ ወጥተው ሕሊናቸው ያዘዛቸውን የሚሰሩት እጅግ በጣም ትንሽ ናቸው። በጣት የሚቆጠሩ። ይህ አባዜ በአማራ ምሁራን ዘንድ የከፋ ነው። ዳር ቆሞ ሕዝብ ሲያልቅ ማየት፣ ትግል ላይ ያሉትንና ተገድደው የገቡትን ውጭ ሆኖ ማነወር፣ ፖለቲካው ውስጥ ብገባ ጭቃ ይነካኛል ብሎ ራቅ ብሎ የሚሆነውን ፈዝዞ ማየት የምሁራኑ መገለጫ ሆኗል።

ብዙዎቹ ደግሞ ሲመቻቸው ለሕሊናቸው ኖረው ያለፉትን እነ ፕሮፌሰር አሥራትን ሲያደንቁ የሚውሉ ናቸው። ተግባራቸውን ወርሰው ግን የምሁርነታቸውን አያበረክቱም። ከርቀት ማየትን ይመርጣሉ። ቢቀርቡ “ክብራቸው” የሚቀንስ ይመስላቸዋል። ሰው እየሞተ፣ ሰው እየተጎዳ የሚያስጨንቃቸው የእነሱ “ክብር” ነው። ሰው እየሞተ ለክብር እየተጨነቁ ግዴታቸውን የተወጡትን እነ ፕሮፌሰር አሥራትን ሲያከብሩ ማየት አሳዘኝ ነው።

በሌላ በኩል የግድ ሆኖበት ፖለቲካ ውስጥ ሆኖ የሚንደፋደፈው ላይ ሲቀልዱ ይታያሉ። ይህን ሲያደርጉ ግን ራሳቸውን የሚያሸክሙትም “ምሁርነት” እንዲሸራረፍ አይፈልጉም። የራሳቸውን “ምሁርነት” ሲያስታውሱ ምሁሩ ፕ/ር አሥራት ሰርተው ያለፉትን የምሁርነት ተግባር ይረሱታል። ክብር ከሚጎዱት ርቀው ሊያስከብሩ ሲጥሩ ለተከበረ ሙያቸው ቆመው፣ ለሕሊናቸው ታዝዘው ለሰው ልጅ ህይወትና ደሕንነት ሰርተው በማለፋቸው የተከበሩትን የእነ ፕሮፌሰር አሥራት ተግባር ይረሱታል!

በተለይ የአማራ ሕዝብ በሚሰቃይበት በዚህ ወቅት በየጓዳው ከማንሾካሾክ ያለፈ እውቀታቸውን ለማበርከት የማይደፍሩት ማፈር ይገባቸዋል። ፕ/ር አሥራት የምሁር ቁንጮ ሆነው የፈፀሙት ከሚጠበቅባቸው በላይ ነው። ግን ለሰው ልጅ በመቆማቸው ተሰድበዋል። ስም ተለጥፎባቸዋል። በዚህ በለየለት ዘመን እንኳ ዳር ቆመው ሕፃናት ሲገደሉ፣ እናቶች ሲሰቃዩ፣ ሕዝብ በጅምላ ሲፈጅ የሚያዩ “ምሁራን” ፕ/ር አሥራትን ሲያስቡ ማፈር፣ መሸማቀቅ ይገባቸዋል። ምክንያቱም ማድረግ የነበረባቸው ምሁሩ ፕ/ር አሥራት ያደረጉትን ነው። ፕ/ር አሥራት የፈፀሙትን በጎ ተግባር ሁሉ መፈፀም የግድ ባይሆንም ዳር ቆሞ ማየት ግን ሊያሳፍራቸው ይገባል፣ ሊያሸማቅቃቸው ይገባል!

ክብር ለሙያቸው፣ ለሕሊናቸው ሲሉ ለተገፉት ቆመው መስዋዕትነት ለከፈሉት ታላቅ ምሁር ይሁን!

The post የሕዝብን በደል ዳር ላይ ቆመው የሚያዩ “ምሑራን” ፕ/ር አሥራትን ሲያስቡ ማፈር አለባቸው! መሸማቀቅ አለባቸው! appeared first on ሳተናው: Satenaw Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!.

የሕዝብን በደል ዳር ላይ ቆመው የሚያዩ “ምሑራን” ፕ/ር አሥራትን ሲያስቡ ማፈር አለባቸው! መሸማቀቅ አለባቸው!