ቦይንግ ኩባንያ የ737 ማክስ አውሮፕላን አብራሪዎች የሰለጠኑበት የምሥለ-በረራ ሶፍትዌር እንከን እንደነበረበት አመነ

ኩባንያው በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አብራሪዎች የሰለጠኑበት ምሥለ-በረራ በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዥያ አየር መንገዶች ለደረሱ የመከስከስ አደጋዎች አስተዋፅዖ ያበረከቱ የተወሰኑ የበረራ ሁኔታዎችን በሥልጠና ወቅት በትክክል መከሰት የሚችል አልነበረም ብሏል። በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዥያ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ተከስክሰው በአጠቃላይ 346 ሰዎች አልቀዋል።

በኢትዮጵያ የደረሰው አደጋ የመጀመሪያ የምርመራ ውጤት በከፍተኛ ፍጥነት ይበር የነበረው የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ አብራሪዎች የአውሮፕላኑን አፍንጫ እየደፈቀ ያስቸገራቸውን ኤምካስ (MCAS) የተባለ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ቦይንግ ያዘዘውን ቅድመ-ሁኔታ በመጠቀም መቆጣጠር አለመቻላቸውን አሳይቷል።
በተለይ በኢትዮጵያ የደረሰው አደጋ የመጀመሪያ የምርመራ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ ተዓማኒነቱ ጥያቄ ውስጥ የወደቀው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ “ቦይንግ ለ737 ማክስ የምሥለ-በረራ ሶፍትዌር ማስተካከያ” ማድረጉን አስታውቋል። ኩባንያው እንዳለው በምሥለ-በረራው የሚገኝ ልምድ የተለያዩ የበረራ ሁኔታዎችን መወከል እንዲችል ለባለሙያዎች ተጨማሪ መረጃዎች አቅርቧል።

ምሥለ-በረራው ያለበትን እንከን ቦይንግ መቼ እንዳወቀ ያለው ነገር የለም። ቦይንግ ኩባንያ ከ737 ማክስ አውሮፕላን ጋር በተገናኘ የንድፍ ችግር እንደነበረ ሲያምን የትናንትናው መግለጫ የመጀመሪያው ነው።

DW

The post ቦይንግ ኩባንያ የ737 ማክስ አውሮፕላን አብራሪዎች የሰለጠኑበት የምሥለ-በረራ ሶፍትዌር እንከን እንደነበረበት አመነ appeared first on ሳተናው: Satenaw Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!.

ቦይንግ ኩባንያ የ737 ማክስ አውሮፕላን አብራሪዎች የሰለጠኑበት የምሥለ-በረራ ሶፍትዌር እንከን እንደነበረበት አመነ