ሐኪሞች ሆይ! ለገሰ ዜናዊ ታደቆናቸው ፍትህ መጠበቅ ከሳጥናኤል መዳፍ ህብስተ መና እንደመጠበቅ ነው! (በላይነህ አባተ)

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

የጤና አገልግሎት ጥያቄ ያነሱ ሐኪሞችን የለገሰ ዜናዊ የጡት ልጅ እንደ አባቱ አሸማቆ መመለሱ ከቡራዮ፣ ከጉጅ፣ ከለገጣፎና ከሌሎች ሥፍራዎችም እንደ ጫካ ከሚጨፈጨፉትና ከሚሰደዱት ዜጎች በላይ እያነጋገረ ነው፡፡
የለገሰ የጡት ልጅ እነዚህን ሐኪሞች እርሱና የሚመራው ድርጅት ሕዝብን እንደ ደን ሲጨፈጪፉ፣ ሲያመክኑ፣ አስረው ሲሰልቡና በኮረንቲ ሲጠብሱ፣ ሲያፈናቅሉና ንብረቱን ሲቀሙ ለምን ድምፅ እንዳላሰሙ አፋጦ ቢጠይቃቸው ኖሮ ለእርሱ ለሐጥያቱ ኑዛዜ ለሐኪሞቹም የታሪክ ተወቃሽነት አባዜ በሆነ ነበር፡፡

የለገሰ የጡት ልጅ ጆሮ እንደ ጡጦ እየጠባና ስልክ እንደ ጡት እየመገመገ መረጃ በሚሰጠው አጋዚ ወጣቶች ጭንቅላታቸውና ደረቶቻቸው እየተበረቀሱ ከሆስፒታል ደጃፍ ነፍሳቸው ስታልፍ “በድንገተኛ ሕመም ሞቱ” የሚሉ የውሸት “ማስረጃዎች” የሚጽፉ ሐኪሞች እንደነበሩ የሚታወቅ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን ብልሹ ምግባር ሲያበረታታ የኖረው ድርጅት መሪ እንደ ካህናትና ሼሆች ሁሉ ሐኪሞቹንም በንቀት ተመልክቷቸዋል፡፡ ስለናቃቸውም የሰበሰባቸውን ሐኪሞች በዓይኑ እሬብ እያዬ እንደ ጡት አባቱ በስድብ አጠረግርጎ መልሷቸዋል፡፡ ልብሳቸውን የማያጥቡ ቆሻሻዎች እንደሆኑ ነግሯቸዋል፡፡ አንድ መኪና እንደሚገዛላቸውና ይኸንን መኪና በየተራ ከደጃቸው እያሳደሩ የመኪና ናፍቆታቸውን መወጣት እንደሚችሉም ተሳልቆባቸዋል፡፡

የለገሰ የጡት ልጅ እርሱ አዳዲስ ልብስ እያቀያየር የሚለብሰው ሐኪሞቹ በሚከፍሉት ግብር መሆኑን የተቀመጠበት ወንበር አስረስቶታል፡፡ ይህ ስንቱን እንዳልሰከነች ኮረዳ “በጅንጀና” ሙክክ የሚያደርገው አሻንጉሊት ሙሴ በቻርተር አውሮፕላን የሰፈሩን ጎረምሳዎች እያስከተለ የአረቦችን እጅ ለመሳም እንደ ውሀ ቀጅ እሚመላለሰው በሐኪሞች ግብር መሆኑኑ እንደ ጡት አባቱ ለገሰ ሙልጭ አርጎ ክዷል፡፡ አሻንጉሊቱ ሙሴ ስንቱን እንደ ነጋዴ ፓስተር በውሸት ስብከት እያማለለ ቤተ-መንግስት የተንፈላሰሰው ከሐኪሞቹ በእውቀት፣ በጥበብና በሙያ ስለላቀ መስሎት ሐኪሞቹን ሽቅብ ቁልቁል አይቶ አባሯቸዋል፡፡
ብዙ ተመራማሪ ጋዜጠኞች የየፍሪካ አረመኔ ገዥዎች የማይጠቀሙት የአፍሪካ ጤና አገልግሎት ደንታ እንደማይሰጣቸው ጥፈዋል፡፡ [1-3] ዘ ኮንቨርሴሽን(The Conversation) የሚባለው ጋዜጣ እንደፃፈው እ. ኤ. አ በ2016 ዓ.ም ብቻ የአፍሪካ ገዥዎችና ተገዥዎቹ እየተመሳጠሩ የከበሩ ቱጃሮች ከስድት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ለህክምና ከአፍሪካ ውጪ አጥፍተዋል፡፡[1] ከአፍሪካ መሪዎች በራሳቸው አገር የጤና አገልግሎት ተጠቅመው የሞቱ ክቡር ኔልሰን ማንዴላ ብቻ መሆናቸውም ተዘግቧል፡፡ [2]

የኢትዮጵያ ሱስ ክፉኛ ያጠናገረውን ሱሰኛውን ለማን ጨምሮ ሌሎች አምባገነን ገዥዎች የአሜሪካን፣ የአውሮጳና የኤሽያ የጤና አገልግሎት ጥገቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የአሻንጉሊቱ ሙሴ የጡት አባትና ሌሎች ዘራፊ ወንበዴዎች ለቁንጣን ቁርጠት፣ ለመንፈስ መናወጥና ለ”ውበት” አውሮጳ፣ አሜሪካ፣ እስራኤልና ኤሽያ ያፈሰሱት ገንዘብ በየገበሬ ማህበሩ ሆስፒታል መስራት ያስችል እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡

እነዚህ ዘራፊ ወንበዴዎች በጤና ዘርፍ እድገት እንዳመጡ በሚቆጣጠሩት ሬዲዮና ቴለቪዥን ይናገሩና ምራቃቸው ሳይደርቅ ቁንጣን ለመታከም አውሮጳ፣ አሜሪካና ኤሽያ ለእያንዳንዳቸው አውሮፕላን አዝዘው እንደሚበሩ የትግሬ ነፃ አውጪዎችንና ከእነሱ ተሻርከው ሲዘርፉ የኖሩ ባንዳዎችን ጉድ ያዬ ያስታውሳል፡፡ ከማያልቀው በረራቸው ሲመለሱም እንደ አሻንጉሊቱ ሙሴ ሐኪሞቾንም ሆነ ሌሎቹን ባለሙያዎች እንደ ባርያ አሳዳሪ እንደሚያንቋሽሹ ይታወቃል፡፡

አሻንጉሊቱ ሙሴ ሐኪሞቹ ያነሱት የጤና አገልግሎት ችግር የተፈጠረው እርሱ በወታደርነትና በጆሮ ጠቢነት ባገለገለውና አሁን በሚመራው ድርጅት መሆኑን ማመን አልፈቀደም፡፡ አሻንጉሊቱ ሙሴ በሚመራው ድርጅት ደባ ጠንሳሽነትና በቴድሮስ አዳኖም ደባ ደፍዳፊነት በኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በ”ጨቋኙ” አማራ የጤና አገልግሎት የፈጠመውን የዘር ማጥዳት ወንጀል ማመን አይፈልግም፡፡ እንዲወላልቁ የተፈረደባቸው የአማራ “ጤና አገልግሎት” መስጫ ጣቢያዎች የወጣት ሴቶች ማምከኛ እንደነበሩ ታሪክም ጥናትም የከተበው መሆኑን የለገሰ የጡት ልጅ ማስታወስ አልፈለገም፡፡ [4-7]

ጤናና ትምህርት የማንኛውም ማህበረሰብ ህልውና መሰረት መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ በእወቀት ያልበለጸገና በጤና ያልጎለበተ ሕዝብ ምንጊዜም ውራ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ ሳይዶከትር ዶክተር እሚባለው አሻንጉሊቱ ሙሴ ቅድሚያ እሚሰጠው ግን በሐኪሞቹ ግብር የሚጋብዛቸው የውጪ እንግዶቹ “አገሪቱ በልጽጋለች!” እያሉ እንዲያሞካሹት ለቤተመንግስትና ለከተማ ውበት ነው፡፡

እንደ ለገሰና ጓደኞቹ አሻንጉሊቱ ሙሴና ሱሰኛው ጓደኛውም የኢትዮጵያን ጤና አገልግሎት ጣቢያዎች ለፎቶ እንጅ ለአገልግሎታቸው እንደማይጠቀሙባቸው እየታየ ነው፡፡ ስለዚህ እነሱ የአምስት ሚሊዮን ብር እራት እየበሉ ከተማና ቢሯቸውን ከማሳመር ቅዠት እንጅ ጦም ከሚያድረውና የቆሸሸ ከሚለብሰው የኢትዮጵያ ሕዝብና ጤና አገልግሎቱ ምን አላቸው?
ስለጤና አገልግሎት ፓስተሩ ሲጠየቅ እንደልማዱ በሥራ የማይታይ የቆሌ ስብከቱን አዥጎደጎደው፡፡ በጤና አገልግሎቱ መጥፋት እርሱና ድርጅቱ ተጠያቂ እንዳልሆኑ ሁሉ ሐኪሞቹን በጥፋተኝነት ፈርጆ በዘልዛላዎች ልብ ዳግም እንደ ቄጠማ ለመጎዝጎዝ ጣረና አረፈው። እሚሰማ ጠፋ እንጅ ለገሰ ዜናዊ እያደቆነ ታቀሰሳቸው ወንጀለኞች ፍትህ መጠበቅ ከሳጥናኤል መዳፍ ህብስተ መና እንደመጠበቅ ነው፡፡

ዋቢ፡-
1. The Conversation: http://theconversation.com/african-politicians-seeking-medical-help-abroad-is-shameful-and-harms-health-care-82771 (last accessed in May, 2019)
2. African Leaders Who Have Sought Healthcare Outside Africahttps://scitechafrica.com/2018/03/17/african-leaders-who-have-sought-healthcare-outside-africa/ (last accessed in May, 2019)

3. African politicians seeking medical help abroad is shameful, and harms health care https://www.news24.com/Africa/News/african-politicians-seeking-medical-help-abroad-is-shameful-and-harms-health-care-20170825 (last accessed in May, 2019)
4. Genocide watch documents on Ethiopia http://www.genocidewatch.org/ethiopia.html (last accessed in May, 2019)
5. Three million Amhars Missing, Berhanu Abegaz https://www.youtube.com/watch?v=3-g-YWYBdbM (last accessed in May, 2019)
6. Three Million Amara are Missing: An Analysis based on the 1994 and the 2007 Ethiopian Population Censuses,Berhanu Abegaz, http://ethiomedia.com/101facts/45139
7. Human right violation of Amharas Muluken Tesfaw http://video.ethsat.com/?p=24983 (last accessed in May, 2019)
ሐኪምን በሚመለከት ሌላ ጽሑፍ፡
ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ሆይ! በናዚ ሐኪሞች የደም ታሪክ ከመዘፈቅ ታቀቡ ( በላይነህ አባተ ) https://www.satenaw.com/amharic/archives/40102

ግንቦት ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.

The post ሐኪሞች ሆይ! ለገሰ ዜናዊ ታደቆናቸው ፍትህ መጠበቅ ከሳጥናኤል መዳፍ ህብስተ መና እንደመጠበቅ ነው! (በላይነህ አባተ) appeared first on ሳተናው: Satenaw Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!.

ሐኪሞች ሆይ! ለገሰ ዜናዊ ታደቆናቸው ፍትህ መጠበቅ ከሳጥናኤል መዳፍ ህብስተ መና እንደመጠበቅ ነው! (በላይነህ አባተ)