ጠ/ሚ ዶክተር ዐቢይ አባቶች ሕዝቡን ስለ ሰላም፣ ፍቅርና ዕርቅ እንዲያስተምሩ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2011 (ኤፍቢሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አባቶች በየአካባቢው ከሚገኙ የመስተዳድር አካላት ጋር በመሆን ሕዝቡን ስለ ሰላም፣ ፍቅርና ዕርቅ እንዲያስተምሩም ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተካሄደ ባለው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አዳራሽ በመገኘት፥ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ያላቸውን መልካም ምኞት ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክትም አባቶች በየአካባቢው ከሚገኙ የመስተዳድር አካላት ጋር በመሆን ሕዝቡን ስለ ሰላም፣ ፍቅርና ዕርቅ እንዲያስተምሩ አደራ ብለዋል።

ለሲኖዶሱ ጉባኤም ቤተ ክህነት ጠንካራ፣ ከሙስና የጸዳና ግልጽነት ያለው ተቋም እንዲሆን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከዚህ ባለፈም ካህናትና ምዕመናን ፍትሕ ፍለጋ በየመንግሥት ተቋማቱ መሄድ እንዳልነበረባቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር በመሆን ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ የዕርዳታ ተቋማትን እና የአካል ጉዳተኛ መርጃዎችን እንዲያቋቁሙም ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ምዕመኑ ለበዓል ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ለመሳለም ስለሚሄድ፥ አጋጣሚውን ሕዝቡን ለማቀራረብ፣ ለማገናኘትና አንድ ለማድረግ መጠቀም እንደሚገባም አንስተዋል።

እንዲሁም በረመዳን ጾም የመጨረሻዎቹ ቀናት ሕዝበ ክርስቲያኑ መስጊዶችንና አካባቢውን በማጽዳት አንድነቱን እንዲያሳይም ጥሪ አቅርበዋል።

በመጭው ክረምትም በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ ለመትከል አስበናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባቶች ሕዝቡን እንዲያስተባብሩ መጠየቃቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መምጣት የነበረውን ታሪክ የቀየረ ነው ብለዋል።

ፓትርያርኩ ከዚህ ቀደም አባቶች ወደ ባለ ሥልጣናት ይሄዱ እንደነበር አስታውሰው፥ መሪዎች ወደ አባቶች መምጣት ትተው እንደነበር ጠቅሰዋል።

ለቅዱስ ሲኖዶስ አንድነትና ከ42 ዓመት በኋላ ለተመለሱት የ4 ኪሎ ሕንፃዎችም ጉባኤው ምስጋናውን አቅርቧል።

ጠ/ሚ ዶክተር ዐቢይ አባቶች ሕዝቡን ስለ ሰላም፣ ፍቅርና ዕርቅ እንዲያስተምሩ ጥሪ አቀረቡ