የዘረኝነት ትርጉም ምንድነው ? ዘረኛ እሚባለውስ ማን ነው?? በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ያሉ ዘረኞች ማንነት!! (ወንድወሰን ተክሉ)

ዘረኛ ነህ ወይም ዘረኝነት ነው የሚሉ ክሶችና ወቀሳዎች ከየአቅጣጫው በእኔም ሆነ በሌሎች ፍትሃዊ እኩልነትን ጠያቂዎች ላይ ሲወነጨፍ እያየሁ፣እየሰማሁና ብሎም እያነበብኩኝ ስለሆነ ይህንን አርእስት በጥልቀት ማየት ይኖርብኛል ብዬ ተረዳሁ፡፡

ለምሳሌ አንዱ ወዳጄ በጣም የማከብረው፣የምወደውና የማደንቀው ትውልዱ ከነገደ ኦሮሞ የሆነ ሰው የእስክንድርን ተቋውሞ ከዘረኝነት ጋር አዋህዶት «…እንደ እስክንድር ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን ጥላቻ በአደባባይ ስላለገለጸ ነውን …» ካለ በኃላ ይህንንም አባባሉንም በማስረጃ እንዲያስደግፍ ላቀረብኩለት ጥያቄ «እስክንድር ኢንጂነር ታከለ ኡማን በመቃወም እንዲህ የተብከነከነው ለኦሮሞ ህዝብ ካለው ጥላቻ አይደለምን..» በማለት ያስቀምጣል፡፡

እንግዲህ ለዚህ ለወዳጄ የእስክንድርና መሰሎቻችን በአዲስ አበባ ጉዳይ ያነሳነው ተቃውሞ በዘረኝነታችን ምክንያት መክንያትና ኢንጂነር ታከለ ኡማ ኦሮሞ በመሆኑ ነው ብሎ ያምናል፡፡

በሌላ ወገን ያሉት ደግሞ በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ላይ ለሚነሱ ትችቶችና ወቀሳዎች መንስኤው በዘረኝነት ምክንያት ነው ዶ/ር ብርሃኑን በጉራጌነቱ እንጂ በተግባሮቹ አይደለም የምትቃወሙት በማለት የተቃውሟችንን ምክንያታዊነትን ከዘር ጋር በማቆራኘት ዘረኝነት ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ ማለት በሚቻል መልኩ የትኛውንም ድጋፍና ተቃውሞን ከዘርጋር አቆራኝቶና ፈርጆ መግለጽ በእጅጉ የተስፋፋ ከመሆኑም በላይ ዘረኝነትን እንጠየፋለን በማለት ዘረኞችንና ዘረኝነትን የሚያወግዙ ሰዎች እንኳን ሳያስቡት እራሳቸውን ዘረኛ በሚያስብል ደረጃ ወርደው እነሱ የሚደግፉትን ማንኛውንም ሰው ወይም ድርጅትን የተቸ ወይም አካሄዳቸውን ያወገዘን ሰው በሞላ በአንድ የዘረኝነት ቅርጫት ውስጥ በመክተት ተቺዎቹን ሲፈርጁና ሲያወግዙ ይታያሉ፡፡

ለመሆኑ ዘረኛ ማለት ምን ማለት ነው ?? የዘረኝነት መገለጫ ባህሪያቱና ድርጊቶቹ ምንድናቸው ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ እጅግ የተገላቢጦሽ መልስ ሆኖ እናያለን፡፡

እስቲ ዘርዘር አድርገን እንየው

ዘረኝነት ወይም Racism ምን ማለት እንደሆነ ዊኪፒዲያ እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል

Racism – Noun ወይም ስም ነው ካለ በኃላ ትርጓሜውንም ሲያብራራ prejudice, discrimination, or antagonism directed against someone of a different race based on the belief that one’s own race is superior.

ብሎ ያስቀምጠዋል፡፡
the belief that all members of each race possess characteristics, abilities, or qualities specific to that race, especially so as to distinguish it as inferior or superior to another race or races.

በአጭሩ ጠቅለል አድርገን ስንፈታው አንድን ሰው በተወለደበት የዘር የትውልድ ነገዱ ምክንያት አድልኦ ሲደረግበትና በዚሁ በዘር ተኮር ማንነቱ ምክንያት አለአግባብ ሲፈረድበት፣ሲገለልና ብሎም ሲወገዝ ዘረኝነት መሆኑን ይገልጽና ዘረኞች እሚባሉትም የራሳቸውን ዘር ከሌሎች ዘሮች የተለየ ችሎታና ብቃት እንዳላቸው በማመን ከሌሎች ነገዶች ሁሉ የበላይነት የሚያሳዩና የሚሰማቸው ናቸው ብሎ በአንጻሩም የዘረኞቹ ማንነትን በዘሯቸው ምክንያትም የበታቸኝነት ስሜትም የተጠናወታቸው ሲል ይገልጻቸዋል፡፡

ስለ Tribalism ሲገልጽ ደግሞ እንደሚከተለው አስቀምጦታል
Tribalism -noun ስም መሆኑን ያስፈርና ትርጓሜውንም እንደሚከተለው አስፍሯል፡፡

tribalism
the state or fact of being organized in a tribe or tribes.
DEROGATORY
the behaviour and attitudes that stem from strong loyalty to one’s own tribe or social group.
“a society motivated by cultural tribalism”

ይህ ማለት በሀገራችን ከ1987 ጀምሮ የሀገሪቱ መተዳደሪያ የሆነው ሕገ መንግስት እና ይህንን ሕገ መንግስት ያጸደቀውና በ1983 ዓ ም ወደ ስልጣን የመጣው ህወሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት የለየለት ጎሰኛ ወይም Tribalism ስርዓት መሆኑን ትርጓሜው በይፋ ሲናገር እናያለን ማለት ነው፡፡

በሁለቱም የዘረኝነትና የጎሰኝ እት ትርጓሜ ውስጥ ዘረኛና ጎሰኛ የሚባለው
1ኛ-አንድን ሰው ወይም ህዝብን በማንነቱ ምክንያት ለይቶና ነጥሎ መድልኦ የሚፈጽም
2ኛ-የራሱን ዘር ወይም ነገድ ከሌሎች አስበልጦ የበላይ የሚያደርግ (እንደ መለስ የትግራይን ህዝብ ወርቅ ሌላውን ጨርቅ ብሎ እንደሰየመው ማለት ነው)እና የበላይነቱንም ለማስጠበቅ በሌሎች ላይ መድሎአዊና አድሎአዊ እርምጃን የሚወስድ
3ኛ-አንድን ሰው ወይም ማህበረሰብን በማንነቱ ምክንያት እንደ አጥፊ ፈርጆና ፈርዶ ማግለልና የበታች አድርጎ መፈረጅ
4ኛ-ከእኔ ዘር ወይም ነገድ በስተቀር ሌላ አላይም የእኔን ዘር የሚስተካከል ምንም ዘር የለም በማለት የዘሩን የበላይነት የሚገነባና የሚሰብክ ….ወዘተ የአንድ ዘረኛ የሚባል ሰውም ሆነ ስብስብ መገለጫዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ስነመገለጫ ባህሪያቶች ናቸው፡፡

እስቲ ይህንን ትርጓሜ ወደ ነባራዊውና የዛሬይቱ ኢትዮያ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ አውርደን እንየው፡፡

ከሁሉ በፊት የጎሰኝነት Tribalism ትርጓሜን ሀገራችንን እየገዛ ያለው የትናንቱ ህወሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስትና የዛሬው ኦዴፓ መራሹ የኢህአዴግ መንግስት አይነተኛ መገለጫ መሆኑን እና ይህም የጎሳኛ መንግስት ከ1983 ጀምሮ ስልጣን ላይ ያለና ዛሬም በተመሳሳይ ፖሊሲና አይዲኦሎጂ ሀገሪቷን እየገዛ ያለ ጎሰኛ መንግስት መሆኑን ቢመረንም ሀቅ ነውና መቀበል ይኖርብናል፡፡

በዚህ መሰረት የጎሰኝነቱን ዛር ተሸካሚውና መልሶ እያስተጋባ ያለው ገዛፊው እራሱ መንግስት እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ይህ ጎሰኛ መንግስት በህገ መንግስቱ ባጸደቀው ጎሳ ተኮር አወቃቀርና አደረጃጀት መሰረት በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ከመቶ በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ከ90% በላይ የሆኑት በጎሳ ላይ ተመርኩዘው የተደራጁ የጎሳ ድርጅቶች ሲሆኑ ይህንንም አደረጃጀት ዛሬም ጭምር ያለው የለውጥ መራሹ መንግስት እያየና እያወቀ ሲያስተናግድ እንጂ እሚታየው ከጎሳ አደረጃጀት የሚገላግለንን የአደረጃጀትን ህግ ሲያወጣልን አልታየምና በዚሁ መሰረት እያንዳንዱ ነገድ/ጎሳ ከሁለት ሶስት በላይ በሆኑ ጎሳዊ ድርጅቶች ሲወከል እያየን እንገኛለን፡፡

ለምሳሌ ያህልም የኦሮሞን ህዝብ እንወክላለን የሚሉ 17 የኦሮሞ ድርጅቶችን እያስተናገድን ሲሆን ትግሬ ከሶስት በላይ ሶማሌ ሶስት በላይ አፋር ከሁለት በላይ ቤኒሻንጉል ከሁለት በላይ እያለ ይሄድና ሁሉም በጎሳ ተሸንሽኖ በተዋቀረው ክልል ውስጥ ከአንድ በላይ ጎሳ ተኮር ድርጅት በተደራጀበት ሁኔታ የአማራው ክልል ግን እስከ ሰኔ 2ቀን 2018 ድረስ በአንድ በገዢው ፓርቲ የተጠፈጠፈለት ብአዴን ተብዬ ድርጅት በስተቀር ሌላ እውነተኛ በሆነ የአማራ ልጅ ድርጅት እንዳይወከልና እንዳይደራጅ በግልጽና በስውር ታግዶ የነበረበትን የዘረኝነትን ተግባር እንድናስታውስ ያስፈልገናል፡፡

የአማራው ህዝብ ከሁሉም ነገዶች በስተመጨረሻ ላይ ለራሱ ህልውና ተገዶ በአማራነቱ መደራጀት ሳይፈልግ ግን በተከፈተበት ዘርፈ ብዙ ጥቃት ምክንያት እራሱን ለመከላከል ሲል እንደማንኛውም አቻ ኢትዮጵያዊ ወገኑ መደራጀት ከቻለ ገና አንደኛ አመቱን ከትናት በስቲያ ባከበረበት ሂደት ላይ በርካታ የአንድነት ጎራ አቀንቃኞች ይህንን እርምጃ ዘረኝነት ነው ሲሉ በመግለጽ ሲኮንኑት ይታያሉ፡፡

አረ ለመሆኑ ዘረኛው ማን ነው??

በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው ግንቦት7 ድርጅት በአማራ ህዝብ ተጋድሎ ላይ ከፍተኛ በደል ፈጽሟልና ዛሬ ዶ/ር ብርሃኑን እና የሚመራውን ድርጅት አልደግፍም የሚለውን የአማራን ህዝብ አሁንም እነዚሁ ወገኖች ከዘረኝነት የመነጨ ነው በማለት የዶ/ር ብርሃኑን አመራርና ድርጅትን አንደግፍም የሚሉትን ወገኖች ዘረኞች ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

እዚህ ላይ ማንኛው እጅግ የለየለት ዘረኛ እየሆነ እንደሆነ ለእነዚህ ወገኖቻችን የምንገልጽበትና ሳያውቁ ግን ቀስበቀስ እየገቡበትና እየተዘፈቁበት ካለው የዘረኝነት ተግባር ከወዲሁ እራሳቸውን ይነጥሉ ዘንድ ልንነግራቸው ይገባል፡፡

ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን
ፍትሃዊ የስልጣንና የስራ ክፍፍልን
ፍትሃዊ የፖለቲካ ውክልናን
ፍትሃዊ እኩልነትን
ፍትሃዊ ፍትህን መጠየቅ እንዴት ሆኖ የዘረኝነት ጥያቄ ሊባል እንደቻለ እራሳቸው ጉዳዩን ወይም ጥያቄዎቹንና ተቃውሞዎቹን በዘረኝነት መነጽር በሚያዩ ሰዎች ዘረኝነት ሊባል ቻለ እንጂ የማንኛውም ፍትህ የራቀው ሰው ፍትሃዊ ጥያቄና ተቃውሞ እንደሆነ በግልጽ ሊያውቁትና ከእዚህ መሰሉም አመለካከት በፍጥነት እራሳቸውን ያርቁ ዘንድ ያስፈልጋቸዋል፡፡

በዘርና በጎሳ ተኮር ፖሊሲው እየተበደልኩኝ ነው የሚለውን አማራ የለም አልተበደልክም እያለ የሚያወግዘው ነው ዘረኛው ወይንስ ተብድያለሁና መብቴ ይከበርልኝ እያለ ያለው ህዝብ ነው ዘረኛ ??

ሌላውና አስደናቂ ፖለቲካዊ ቧልት ሆኖብኝ በአንክሮና በአርምሞ እያየሁ ያለሁት ሁኔታ የዶ/ር ብርሃኑ መራሹን ድርጅት መቃወምና የዶ/ር አቢይን ጥፋትና ስህተት ገልጾ መተቸትን እንደ በኢትዮጵያዊነት ላይ እንደተቃጣ ጥቃት አድርገው የሚገልጹትን ሁኔታ ነው፡፡ ዶ/ር ብርሃኑን አሜን ብሎ መሸከምና ብሎም ዶ/ር አቢይና ኢንጂነር ታከለ ኡማና መሰል የዛሬዎቹ ገዢዎች የሚያደርጉትን ማንኛውንም አይነት እርምጃን እሰይ እያሉ መቀበል የጥሩ ኢትዮያዊነት መገለጫ ነው የሚሉን እንዴት ሆኖ ነው እያልኩ በአርምሞ የምመለከተው መልካም ያልሆነ ልምድና ተመኩሮ ሆኗል፡፡

**ዘረኝነት የተበደሉትን ድምጽ ማፈን ነው
**ዘረኝነት ከእኛ በስተቀር ለምን ሌላ አማራጭ ትፈልጋለህ ማለት ነው
**ዘረኝነት መብትህን ስትጠይቅ ይህ ዘረኝነት ነው ብሎ መፈረጅ ነው

እናም እስቲ መጀመሪያ እራሳችሁን ከዚህ መሰል ተውሳክ አጽዱና የዜጎችን ፍትሃዊ ጥያቄን በዘር ፈርጆ ከመደፍጠጥ ተቀብሎ በማስተናገድ ለመፍታት ተዘጋጁና ነው ዘረኝነትን ልታወግዙና ልትኮንኑ ሞራሉ እሚኖራችሁ በማለት ጽሁፌን እደመድማለሁ፡፡

The post የዘረኝነት ትርጉም ምንድነው ? ዘረኛ እሚባለውስ ማን ነው?? በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ያሉ ዘረኞች ማንነት!! (ወንድወሰን ተክሉ) appeared first on ሳተናው: Satenaw Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!.

የዘረኝነት ትርጉም ምንድነው ? ዘረኛ እሚባለውስ ማን ነው?? በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ያሉ ዘረኞች ማንነት!! (ወንድወሰን ተክሉ)