የኢሳትን ውዝግብ ለመፍታት ቁልፉ ያለው እነ ዶ/ር ብርሃኑ ጋር ነው (ግርማ ካሳ)

ኢሳት ችግር አጋጥሞታል። ንአመን ዘለቀና አበበ ገላው እየተላጣጡ ነው። ንአመንማ አበበ ገላው በጻፈው መበሳጨቱን ሁሉ ገልጿል። የኢሳት የዲሲ ዳይሬክተር ታማኝ በየነ ኢትዮጵያ ነው። እኔ ወደ አሜሪካ እስክመለስ ትንሽ ረጋ በሉ ብሎ ነበር።

ይህ በዚህ እዳለ በቦርድ ተብዬው የተባረሩትና በፍቃዳቸውን የለቀቁት የኢሳት ጋዜጠኞች፣ ሕዝብን ማገልገላቸውን ማቆም ስለሌለባቸው ሜዲያ 360 የሚል አዲስ ሜዲያ ከፍተዋል።

የኢሳት ሱብስክሪፕሺን በጣም ወርዷል። እለታዊ የተባለው ተወዳጅ ፕሮግራም አሁን ብዙ የሚያዳጠው የለም። በአንጻሩ ሰው አዲሱን ሜዲያ በጉጉት እየተጠባበቀ ነው። በጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ ለአዲሱ ሜዲያ ብዙ ገንዘብ ተሰብስቧል።

በኔ እይታ ችግሩ ያለው ቦርዱ ጋር ስለሆነ፣ የቀድሞ የግንቦት ሰባት ሰዎች ገለል ቢሉና ቦርዱ እንደገና በአዲስ መልክ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ቢዋቀር ፣ ሜዲያ 360ም እንደገና የኢሳት አካል ሆኖ ቢሰሩ ጥሩ ነው። እንደ ፕሮፌሽናል ሜዲያ ኢሳት ሁሉንም አመለካከቶች በነጻነት የሚያስተናግድ ሜዲያ እንዲሆን ቢደረግ በጣም የተሻለ አማራጭ ነው የሚሆነው። ሲሳይ አጌና አሁን የሚያራምደውን በነጻነት ያራምድ። እነ ርዮት አለሙም ያራምዱ። ሲሳይ አጌና በሚያዘጋጀው ፕሮግራም የፈለገውን ይጋብዝ። ቢፈልግ ዶ/ር ደብረጽዮንን ወይንም ዳዎድ ኢብሳን። እነ ርዮትም በምያዘጋጁት ፕሮግራም የፈለጉት ይጋብዙ። እኔንም ልጋበዝ፡)፡) ዋናው ነገር ኢሳት ለማንም በሩ አይዘጋ። ሁሉንም አመለካከቶች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ያስተናግድ። በማን ፓርቲ ወይንም በመንግስት ተጽኖ ስር አይሁን።

ኢሳት ከአንድ ድርጅት ተጽኖ ወጥቶ ነጻና ገለልተኛ እንዲሆን አሁን ሳይሆን ለአመታት ስጠይቅ ነበር። ችግሩ አሁን ፈነዳ እንጂ ፣ ችግሩ የጀመረው ከመጀመሪያ ነው። ዶ/ር ብርሃኑ መጀመሪያ የነበረውን ቦርድ አፍርሶ ቦርዱን የግንቦት ሰባት አመራሮች(ጓደኞቹ) እንዲቆጣጠሩት ካደረገ በኋላ። ኢሳት ገለልተኛ መሆን አለበት በሚል አቋሜም ብዙ ትችትን አስተናግጃለሁ። ሊሰሙንም ፍቃደኛ አልነበሩም።

አሁንም ኳሷ ያለችው እነዚህ ቦርድ የተባሉትና ዶ/ር ብርሃኑ ጋር ነው። ሁሉንም እኛ ካልተቆጣጠርን ከሚል ጎጂ አመለካከት ወጥተው ኢሳት ነጻና ገለልተኛ በአዲስ ቦርድ እንዲመራ ማድረግ ይችላሉ። ጥያቄው ግን ይፈልጋሉ ወይ ? የሚለው ነው።

—–

የኢሳት የቦርድ አባላት፡

አዲሱ መንገሻ (ገድሉ) – የግንቦት ሰባት አመራር
ንአምን ዘለቀ – የግንቦት ሰባት አመራር
ዶ/ር አዚዝ መሐመድ – የግንቦት ሰባት አመራር
ዶ/ር ሙሉዓለም – (የዶር ታደሰ ብሩ ባለቤት ሳትሆን አትቀርም፤ ዶር ታደሰ የግንቦት ሰባት አመራር ነው። ዶ/ር ሙሉ አለምም ትሁን አትሁን አላውቅም፡
አቶ ዘላለም – ብዙ መረጃ የለኝም።

በኢትዮጵያ ብሮድካት የተመዘገቡ የኢሳት ብቸኛ አክሲዮን ባለቤቶች የግንቦት ሰባት አመራር የሆኑት ፡

አዲሱ መንገሻ (ገድሉ) – የግንቦት ሰባት አመራር
ኤፍሬም ማዴቦና – የግንቦት ሰባት አመራር
የኢሳት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆነችው ወይዘሮ ሳባ አታሮ – ብዙ መረጃ የለኝም
ሁለት ሰዎችን ገና ለማውቅ አልቻልኩም።

ከነዚህ ሰዎች ጀርባ ደግሞ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እንዳለ በግልጽ የሚታውቅ ነው። ኢሳት ሲቋቋም መጀመሪያ የነበሩ የቢርድ አባላት ተወግደው የግንቦት ሰባት አመራሮች ብቻ የቦርድ አባላት እንዲሆኑ ያደረገውን ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ነውና።
—–

The post የኢሳትን ውዝግብ ለመፍታት ቁልፉ ያለው እነ ዶ/ር ብርሃኑ ጋር ነው (ግርማ ካሳ) appeared first on ሳተናው: Satenaw Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!.

የኢሳትን ውዝግብ ለመፍታት ቁልፉ ያለው እነ ዶ/ር ብርሃኑ ጋር ነው (ግርማ ካሳ)