በሐይቆች ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም በዘላቂነት ለማስወገድ አዲስ የድርጊት መርሀ ግብር ሊተገበር ነው

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 4/2011ዓ.ም (አብመድ) ለእንቦጭ መከሰት ምክንያት የሆኑ ምንጮችን ከመከላከል ይልቅ እንቦጩ ላይ ትኩረት መደረጉ ችግሩን መቅረፍ እንዳላስቻለ ተገልጧል፡፡

የኢፌዴሪ ተፋሰስ ልማት ባለስልጣን በኢትዮጵያ ሐይቆች ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም በዘላቂነት ለማስወገድ ባዘጋጀው አዲስ የድርጊት መርሀ ግብር ላይ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምክር ቤት ተወካዮች፣ ከግብርና እና ከብዝሃ ሕይወት ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል፡፡ ከዚህ በፊት የተሠሩ የማስወገድ ስራዎች ሳይንሳዊ ባለመሆናቸው አረሙ በየዓመቱ ለስምንት ዓመታት ያክል እየተስፋፋ እንዲሄድ ዕድል እንደፈጠረለት የዘርፉ ተመራማሪው ዶክተር አያሌው ወንዴ ተናግረዋል።

የባሕር ሸሽ እርሻ እና የልቅ ግጦሽ መስፋፋት፣ የአፈር ማዳበሪያ በሀይቁ አከባቢ መጠቀም እና የኢንዱስትሪ እና የከተሞች ቆሻሻ ወደ ሐይቁ መግባታቸው ሐይቆች በእንቦጭ እንዲወረሩ እያደረጓቸው እንደሆነ ዶክተር አያሌው አስገንዝበዋል፡፡ ይህንንም በጥናት ማረጋገጣቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የተጋነኑ የአፈፃፀም ሪፖርቶች እና በሳይንሳዊ ቅደም ተከተል አወጋገድ ሳይሆን በዘመቻ መሠራቱ ባለፉት ዓመታት አረሙ እንዲስፋፋ እገዛ ማድረጋቸውንም አብራርተዋል፡፡

አዲሱ የድርጊት መርሀ ግብር በአግባቡ ከተተገበረ በዘላቂነት የማስወገድ ሥራውን ውጤታማ እንደሚያደርግም ዶክተር አያሌው አመላክተዋል።

የኢፌዴሪ የተፋሰስ ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከጣና ሀይቅ በተጨማሪ በቆጋ፣ በአባ ሳሙኤል፣ በዝዋይ፣ በአባያ እና ጫሞ ሀይቆች ላይ የእንቦጭ አረም ከተከሰተ ቆይቷል ብለዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል እና ለማስወገድ የሚያስችል አዲስ የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ሙያዊ አስተያዬቶች እየተሰጡበት እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

እንቦጭ ተከስቶ የነበረባቸው ሀገራት እንዴት እንዳስወገዱት ልምዳቸውን በመቀመር የአጭር እና የረጅም ጊዜ እቅድ በማውጣት ለማስተግበር እየሠሩ መሆናቸውንም ነው ዶክተር አዳነች የተናገሩት።

በምክክሩ የተሳተፉ ባለሙያዎች በበኩላቸው ለእንቦጭ መከሰት ምክንያት የሆኑ ምንጮችን ከመከላከል ይልቅ እንቦጩ ላይ ትኩረት በመደረጉ ችግሩን አባብሶታል ብለዋል። አዲሱ የድርጊት መርሀ ግብርም መገፋፋት ያለበትና እና ወጥነት የጎደለው እንዳይሆን በከፍተኛ ኃላፊነት መሥራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ግርማ ተጫነ

The post በሐይቆች ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም በዘላቂነት ለማስወገድ አዲስ የድርጊት መርሀ ግብር ሊተገበር ነው appeared first on ሳተናው: Satenaw Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!.

በሐይቆች ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም በዘላቂነት ለማስወገድ አዲስ የድርጊት መርሀ ግብር ሊተገበር ነው