የመከላከያ ሚኒስትሩ በጀኔራል ሰዓረ መኮንን እና በዶክተር አምባቸው መኮንን ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 16 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ በጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሰዓረ መኮንን እና በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ።

ሚኒስትሩ የተፈጸመው ጥቃት ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጠና አሳዛኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በድርጊቱ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽም ለወዳጅ ዘመዶችና ቤተሰብ መጽናናትን ተመኝተዋል።

ሚኒስትሩ ሃገሪቱ ለውጥ ላይ መሆኗን ጠቅሰው፥ የለውጡ ሂደት በፖለቲካው ምቹ መደላድል ይፈጥራል ብለን እናምናለንም ነው ያሉት።

በዚህ ጊዜም ለውጡን ተባብሮ ወደተሻለ ምዕራፍ ማድረስ ይገባ እንደነበርም አንስተዋል።

የሃገር መከላከያ ሰራዊትም ድርጊቱ ከተፈጸመበት እለት ጀምሮ ሰላምን ለማስፈን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መላው ኢትዮጵያውያንም ከመንግስት ጎን በመቆም ለሰላምና መረጋጋት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

በተያያዘም የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተፈጸመው ጥቃት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጥቃቱ ተገቢነት የሌለውና የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ያለመ መሆኑንም አውስተዋል።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትም በአማራ ክልል ሰላምን ለማስፈን ለሚደረግ ጥረት ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፤ ለሟች ቤተሰቦችም መፅናናትን ተመኝተዋል።

በሌላ በኩል የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጥቃቱን በማውገዝ የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ድርጊቱ ፌደራላዊ ስርዓትን እና ህገ መንግስቱን ለማፍረስ የሚደረግ እንቅስቃሴ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የክልሉ መንግስትም ሰላምን ለማስከበርና ወንጀለኞችን በቁጥጥር ለማዋል በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው በጥቃቱ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

አቶ ሙስጠፌ ጥቃቱ የሚያሳዝን ቢሆንም ለውጡን እንዳሰቡት የሚቀለብስ አይደለም ነው ያሉት።

ለወዳጅ ዘመዶችና ቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ተመኝተዋል።

EBC

The post የመከላከያ ሚኒስትሩ በጀኔራል ሰዓረ መኮንን እና በዶክተር አምባቸው መኮንን ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ appeared first on ሳተናው: Satenaw Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!.


የመከላከያ ሚኒስትሩ በጀኔራል ሰዓረ መኮንን እና በዶክተር አምባቸው መኮንን ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ