በጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅላይ ምኒስትሩ አረጋገጡ

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋገጡ። ጠቅላይ ምኒስትሩ ከዕኩለ ለሊት በኋላ በብሔራዊ ቴሌቭዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ በባሕር ዳር በተፈጸመው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ በጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከባሕር ዳሩ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልጸዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ “በአማራ ክልል ያጋጠመውን ችግር እና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሆኖ እያስተባበረ እና እየመራ የነበረውን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በቅጥረኛ የተገዙ የቅርብ ሰዎች አሁን አመሻሽ ላይ የምንወደውን የምናከብረውን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም መሰል ጥቃት ተፈፅሞበታል” ብለዋል።

በኤታማዦር ሹሙ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል የተባሉ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ «በቀረንም ጊዜ በዚህ ጉዳይ ተባባሪ፤ ተሳታታፊ፣ አጋዥ የሆኑ በሕግ አግባብ ሊታዩ የሚገቡ ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር እናውላለን» ብለዋል።

ወታደራዊ መለዮ ለብሰው በቴሌቭዥን የቀረቡት ዐቢይ የመከለከያ ሰራዊት እና ለፌድራል ፖሊስ አባላት በመግለጫቸው ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ለአገሪቱ ጦር ባቀረቡት ጥሪ ዕዝ እና ቁጥጥር እንዲከበር አሳስበዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው በጥቂት ግለሰቦች እንጂ በአንድ ብሔር አለመሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ምኒስትሩ የሰራዊት አባላት የብሔር ጥቃት እንዳይሰማቸው ተማፅኖ አቅርበዋል።

«የመከላከያ ሰራዊታችን፤ የፌድራል ፖሊስ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ባንዲራውን እና አገሩን አስቀድሞ፤ በዘር ሊከፋፍሉን እና ይቺን ታላቅ አገር ሊበትኑ የሚያስቡ ሰዎች ከእነ ዕኩይ ሐሳባቸው ጥቃታቸውን የምንከላከል እና ኢትዮጵያን የምናስቀጥል እንጂ በተፈጠረብን ትንኮሳ፣ በከፈልንው አሳዛኝ እና አስከፊ መስዋዕትነት ሸብረክ የማንል መሆኑን ዳግም ጀግነቱን እንዲያረጋግጥ ጥሪ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ»

#DW

The post በጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅላይ ምኒስትሩ አረጋገጡ appeared first on ሳተናው: Satenaw Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!.


በጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅላይ ምኒስትሩ አረጋገጡ