ጥብቅ ማሳሰቢያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ (ሰርፀ ደስታ)

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

ሰሞኑን በባሕርዳር መፈንቅለ መንግስት በሚል በክልሉ ባለስልጣናት እንዲሁም የተያያዘ በሚል በመከላከያ ከፍተኛ ጀነራሎች ላይ የተፈጸመው ግድያ እስካሁን ድረስ አሳማኝ የሚባል መረጃ ለሕዝብ ያልደረሰ ሲሆን ይልቁንም ይበልጥ ሕዝብን ወደ አላስፈላጊ ጥርጣሬ እንዲገባ ዳርጎታል፡፡ አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ሁሉ ራሱን የለውጥ አራማጅ ነኝ ከሚለው ቡድን ሲሆን ጉዳዩን በአሳማኝ መረጃዎች ሕዝብን ማሳመን ሳይሆን የተያያዘው እናንተ ዝም በሉ እኔ የምነግራችሁን ብቻ ስሙና እመኑ አይነት ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ ለአገርና ሕዝብ ደህንነት ሲባል እስኪ ትዕግስት ይኑር የሚለውን ሰምተን የተሻለ መረጃ ይወጣል ብለን ብንጠብቅም  የተሳከረና በዚህ ምክነያት ተብሎ ለማመን የሚያስችል አንድም መረጃ ሊወጣ አልቻለም፡፡ ሕዝብ ግን የሚከተሉትን ነጥቦች በጥሞና ያስተውል፡፡

  1. በባሕርዳር ጥቃት ከደረሰባቸው አንዳቸው እንኳን በሕይወት ከተረፎ ቢተርፉ መቼም በራሳቸው የመጣን ጉዳይ አይሸሽጉትምና አሳማኝ መረጃ ይወጣል ይሚል እምነት አለኝ፡፡ ሆኖም በሕወት አሉ የተባሉት አቶ ምግባሩ ናቸው እሳቸውም በሕወት የመትረፋቸው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ በዚህ አደጋ ጫፋቸው እንኳን ያልተነካ (በድንገት እንኳን ያልቆሰሉ) ከዚህ ሴራ ነጻ ናቻ ማለት ስለማያስደፍር እነሱ የሚሉትን ማመን እስከ ዛሬ የኖርንበትን የኢሕአዴግ የተባለ ቡድን ሴራን መዘንጋት ነው
  2. አሳምነው ጽጌ ነው ይሄን የሠራው የሚለው አሁንም ይሄው ምንም ችረት እንኳን ያልደረሰበትና ከማዕከላዊው መንግሰት ነው፡፡ ከቀን በፊት ግን አሳምነው ከማዕላዊው መንግሰት የሆን የሴራ ቡድን በክልሉ እንደገባ ተናግረው ነበር፡፡ እኝህ ሰው ይሄን ጉዳይ እንዴት ሊናገሩት ቻሉ? አሳምነው ጉዳዩ ገብቷቸው ነበር፡፡ ምን አልባት ያልጠበቁት አሁን በሆነው አይነት ይሆናል ብለው አልገመቱ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን አሁን የሆነው አሳምነው ከአስጠነቀቁት የተለየ አደለም
  3. የሳዕረ መኮንንና የወዳጃቸው ሌላው ጀነራል መገደልና እየወጣ ያለው መረጃ ሌላው በጣም አጠያያቂ ነገር ነው፡፡ አሁንም የሳዕረ ሞትን በአሳምነው ተቀነባበረ አይነት በማስመሰል ነው እየተነገረን ያለው፡፡ በየትኛውም አመክንዮ ግን አንድን ሊየውም የአገሪቱ የመከላከያ የመጨረሻውን ማዕረግ ያለው ሰው ከግለሰቡም በላይ የአገር ለዋላዊነት ጉዳይ ከመሆኑ አንጻር ምን አልባትም አገሪቱን ከሚመራው ጠ/ሚኒሰቴር በላይ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ይሄን አልፎ በመከላከያው የታማጆር ሹም ላይ ጥቃት ሊፈጽም የሚችል ከደህንነት መዋቅሩ ውጭ የመኖሩ እድል የመነመነ ነው፡፡ በሳዕረና ጓደኛቻ ላይ የተፈጸመውን የቅርብ ጠባቂያቸው በሚል ማለፍ አይቻልም፡፡ ግልጽ ነው እንዲህ ያሉ ሰዎች የሚገደሉት እንደተባለውም በቅርብ ጠባቂ ነው፡፡ ሆኖም የቅርብ ጠባቂ የተባለውን በዚህ ደረጃ ሊያሳምነውና ዋስትና ሊሰጠው የሚችል አካል ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ለዚህ ጠባቂ ትዕዛዝና ዋስትና ሊሰጥ የሚችለው ከባሕርዳር ሳይሆን አሁንም በስልጣን ላይ ከአለው ቡድን እንደሚሆን አለመገመት ሞኝነት ነው፡፡ ወይም እነሱ እንዳሉት እነሱን እየሰማን መቀበል ነው፡፡ ከዚህ በፊት ስመኘው ሞተ የተባለበት ሁኔታም ከዚሁ ጋር ልናስታውስ ይገባል፡፡ ከዛ በፊት የደህንነት ሹም የነበተው ክንፈና ኃይሎምንም የተገደሉበትን ሁኔታ እናስታውስ፡፡
  4. መረጃ ከእኛ ሥሙ የሚሉት ይሄ ነው የሚባል መረጃ አለመስጠታቸው ሳያንስ አሁንም ዛሬ ወደ 30 ዓመት በዛግንበት የአገርና የሕዝብ መሠረታዊ ጠላት የሆነው እነሱ ሕገ-መንግሰት የሚሉትን እየጠቀሱ ሊያወክቡትነ ይፈልጋሉ፡፡ የባሕርዳሩን ክስተትም ሕዝቡ በትግሉ ያመጣውን ነጻነት ለመንጠቅ ብለውታል፡፡ እነዚህ ዜማዎች 30 ዓመት እየተጠጋው ባለ ጊዜ ሳይቋረጡ የምንሰማቸው አፍዝ አደንግዝ የሆኑብን ይመስላል፡፡ የትኛውን ነጻነት ለየትኛው ሕዝብ ነው? አንዴ እንኳን ሕዝቡ በነጻነት የመረጠው የራሱ መንግስት በሌለበት፣ በየቦታው እየተፈናቀለና እየሞተ ባለበት፡፡ ባኃል ለመናድ ይሉሃል፡፡

በርካታ ሌሎች ጥያቄዎች አሉኝ፡፡ ሆኖም ዛሬ ራሱን መንግስት ያደረገው ቡድን ለ30 ዓመት የተጠጋ ጊዜ ከሥልጣን እንዳይወርድ እየተጠነቀቀ ያለ ከወረደም በብዙ ወንጀሎች ሊጠየቅ የሚችል እንደሆነ አስቦ እየሰራ እንደሆነ አለማሰብ አለማስተዋል ነው፡፡ እሺ የሆነው ሁሉ እንዳሉት ነው እንበልና ዛሬ ጠቃቱን ፈጽመዋል እየተባሉ በአዋጅ ከሚከሰሱት ከእነአሳምነውስ ምን ሊሰማ ይችል ይሆን? ይሄ ጉዳይ ፍጹም ገለልተኛ የሆነ አካል ተገኝቶ ቢያንስ መረጃ እንኳን እንዲሰጥን ያስፈልገዋል፡፡ አሳምነውም ሆነ ሌላው ከብዙዎቻችን በተሻለ ሴራውንም ያውቁታል፣ መሆን የሚገባውንም ያስባሉ፡፡ አሁን ሆነ እየተባለ ያለው እነ አሳምነው ይቅርና ተራ ሰውም አንዳች ትርፍ እንደሌለው ይረዳዋል፡፡ አሁን ላይ የሚናገረው አንድ ወግን ሊያውም በሴራ የሚታወቀው 30 ዓመት ለተጠጋ ጊዜ ሕዝብ በመግደልና በመዝረፍ የሚታወቀው እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የመረጃዎቹን ቅንብርም ማስተዋል ይገባል፡፡ የባህርዳርም ሆነ ሌላው ሕዝብ ምን እንደተከሰተ አንኳን አያውቅም፡፡ እንደሁላችንም ከቴሌቪዥን ከመስማት በቀር፡፡ ሁሉም ለሕሊናውና ለራሱ ሲል ያስተውል፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በአንድነት መቆም ግድ ይለዋል፡፡ ጉዳዩ የአማራ ብቻ አደለም፡፡ ጉዳዩ የሁሉም ነው፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከጥፋት ይጠብቅ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

The post ጥብቅ ማሳሰቢያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ (ሰርፀ ደስታ) appeared first on ሳተናው: Satenaw Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!.


ጥብቅ ማሳሰቢያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ (ሰርፀ ደስታ)