‹‹በውስጣችን የጠነከረ አንድነት ያለን ከአማራ ሕዝብ አብራክ የወጣን ለአማራ ሕዝብ የቆምን ኃይሎች ነን።›› የክልሉ የፀጥታ ኃይል

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 3/2011 ዓ.ም (አብመድ) ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ላይ በተፈፀመው ጥቃት ሳቢያ በደረሰው ጉዳት እና ከዚያም በኋላ የነበረውን የሠላማዊ ሕይወት ማስቀጠል በሚቻልበት ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የአማራ ክልል የፀጥታ አካላት እየመከሩ ነው።

በፍኖተ ሠላም ከተማ አስተዳደር እየተካሄደ ባለው ምክክር የምሥራቅ ጎጃምና የምዕራብ ጎጃም ዞኖች፣ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደርና ከክልል የተውጣጡ የፀጥታ ኃይል ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው፡፡

የፀጥታ አካሉ በደረሰው ጉዳት የፀጥታ ኃይሉ የሥራ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል እና ወደፊትም አንድነቱን ጠብቆ የሕዝቡን አስተማማኝ ሠላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ መሠራት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ በስፋት መክሯል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በጥቃቱ ማዘናቸውን ገልፀው በአንዳንድ ሚዲያዎች እና በማኅበራዊ መድረክ እንደሚወራው የፀጥታ ኃይሉ በሁለት ጎራ የተከፈለ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ የፀጥታ ኃይል በአንድነቱ ፀንቶ ለአንድ ሕዝብና ለአንድ ዓላማ የቆመ ነውም ብለዋል።

የፀጥታ አካላቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ሰንደቅ ዓላማ ለረጅም ዓመታት በየድንበሩ የተዋደቁ፣ የደከሙ እና ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹የሞቀ ትዳራችን ጥለን ዳግም ወደ ትግል የገባነው የአማራን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ነው›› ብለዋል። የክልሉን ሕዝብ አንድነት እና ሠላም የማይፈልጉ ኃይሎች የሚያሰራጩት ወሬ የፀጥታ ኃይሉን ዓላማና ግብ ያላገናዘበ የደካሞች ሴራ እንደሆነም አስታውቀዋል። ‹‹በውስጣችን የጠነከረ አንድነት ያለን ከአማራ ሕዝብ አብራክ የወጣን ለአማራ ሕዝብ የቆምን ኃይሎች ነን፡፡ ሕዝቡ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ሳይታለል በቅንነት እና በታማኝነት ለማገልገል ቆራጥ መሆናችንን ሊረዳ ይገባል›› ብለዋል።

የፀጥታ ኃይሉ ለአማራ ሕዝብ ህልውና እና ለሕግ መከበር በሕግ አግባብ ሌት ከቀን እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡ ክልሉ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ ዜጎች በነፃነት ሰርተው የሚኖሩበት እና ዋስትናቸው የተረጋገጠበት እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ቃል ገብተዋል። የክልሉ ሕዝብም ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን አብሮ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል። የአማራ ክልል ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ቀለሙ ሙሉነህ በመድረኩ ተገኝተው የክልሉን የፀጥታ ኃይል አባላት አወያይተዋል፤ በከፍተኛ ተነሳሽነትና በአንድነት ለሕግ የበላይነት ለመሥራት ቃል መግባታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ምክክሩ እስከታችኛው የፀጥታ ኃይል መዋቅር እንደሚወርድም አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ -ከፍኖተ ሰላም