ሕገ-መንግሥቱ በምክክር ስላልመጣ ችግር አምጥቶአል። DW ዉይይት

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

ዉይይት፤ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄና ተግዳሮቶቹ

DW – «በሲዳማ እስካሁን አስር ብሔር ብሔረሰቦች የክልል ጥያቄን አቅርበዋል። ሕገ-መንግሥት ፈቀደ ማለት፤ ሕገ-መንግሥትን መሠረት አድርጎ የሚያፈርስ ኃይል መኖር የለበትም። መንግሥት ይሄን ካላደረገ ክልል አዉጃለሁ ማለት ከሕግ አኳያ ጥያቄ ዉስጥ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። ለተከሰተዉ አደጋ በሲዳማ ሕዝብ ይቅርታን እንጠይቃለን» ተወያዮች


የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ፤ ማወዛገቡ ቀጥሎአል። የዞኑ ምክር ቤት ከአንድ ዓመት በፊት ያፀደቀዉ ክልል የመሆን ጥያቄ ላይ ለመወሰን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቢያቀርብም ጥያቄዉ ምላሽ ባለማግኘቱ የሲዳማ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ አቀንቃኞች ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ሲዳማን አስረኛ ክልላዊ መንግስት ስንል እናዉጃለን ሲሉ ዝተዉ ነበር። የክልሉ ገዥ ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ ባወጣዉ መግለጫ ግን የሁሉንም ህዝቦች ተጠቃሚ ያረጋገጠ ውሳኔ ማስተላለፉን ገልፆ ነበር።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ጥያቄዉ የደረሰዉ ህዳር 12 ቀን 2011 መሆኑን በማሳወቅ በቀጣዩቹ 5 ወራት ህዝበ ውሳኔ ለማከናወን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታዉቋል። የቦርዱ መልስ የሲዳማ ልሒቃንን አቋም ከደኢሕዴን መግለጫ ይልቅ ያለዘበ መስሎአል ተብሎአል። ቀደም ሲል ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለፓርላማ የመንግሥታቸውን የአፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የክልል እንሁን ጥያቄ ጥናት እየተደረገ ነዉ፣ ጠያቂ ብሔር ብሔረሰቦች በትዕግሥት ሕጉን ተከትለው ማቅረብ እንዳለባቸው ማሳሰባቸዉ ይታወሳል።

ኤጄቶዎች በበኩላቸዉ ደኢህዴንም ይሁን ምርጫ ቦርድን አናምንም የሲዳማ ክልልነት ይታወጅልን ሲሉ መጠየቃቸዉ ተሰምቶአል። በሲዳማ ዞን የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን ) መላው የሲዳማ ብሔር እንዲረጋጋ ጠይቆም ነበር። የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ሂደቱና ዉዝግቡ የእለቱ መወያያ ርዕሳችን ነዉ። በዚህ ርዕስ ላይ እንዲወያዩልን አራት እንግዶችን ጋብዘናል። 1.አቶ ዴያሞ ዳሌ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የሕዝብ ግንኙነት ምሑር፤ 2.ዶ/ር ዘመላክ አይተነዉ፤ የፊደራሊዝምና የመልካም አስተዳደር ማዕከል ዳይሬክተር፤ 3. አቶ ደጀኔ ወልደአማኑኤል የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) መስራች፤ እንዲሁም 4.ዶ/ር ለማ ይፍራሸዋ፤ በኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ጥናት ያካሂዱ የፖለቲካ ሳይንስና የሕግ ምሁር ናቸዉ። ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

 

 

The post ሕገ-መንግሥቱ በምክክር ስላልመጣ ችግር አምጥቶአል። DW ዉይይት appeared first on ሳተናው: Satenaw Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!.


ሕገ-መንግሥቱ በምክክር ስላልመጣ ችግር አምጥቶአል። DW ዉይይት