ኢሕአዴግ በዓለም አቀፍ ጦር ወንጀለኝነት ሊጠየቅ ይገባል (ሰርፀ ደስታ)

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

ማንም ራሱን አይሸውድ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ሆን ተብሎ በሚታቀድ ሴራ እንጂ ድንገትና ሳይታሰብ አደለም፡፡ ለ27 ዓመት በሕወሀት የተመራው ኢሕዴግ ዛሬ ተራውን ለኦዴፓ/ኦነግ ሰጥቶ ጥፋቱ ቀጥሏል፡፡ ምርጫ የተባለው ጊዜ እየደረሰ ነው፡፡ አንድም ተቃዋሚ በሌለበት፡፡ በአዴን አብን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀጣው ስለተረዳ ከወዲሁ እያጸዳ ይመስላል፡፡ ኦፌኮም በተመሳሳይ ችግር እየገጠመኝ ነው እያለ ነው፡፡ ስንት ሲጠበቅ የነበረው አንዱ አለም አራጋውም አብይ ከእኛ በላይ ኢትዮጵያዊ ነው የሚል ሰባኪ ቡድን ተቀላቅሎ አርፎታል፡፡ ኢሕኤዴግ በትክክለኛ ምርጫ እንደማያሸነፍ አሳምሮ ስለሚያውቅ ያው የተለመደውን ድራማውን በሁሉም ቦታ ቀጥሏል፡፡ አውቃለሁ እርስ በእርስ የሆነ ፉክክር አለ ያም ሆኖ ግን ኢህዴግ ውስጥ ያሉት ስብስቦች ይሄ ዛሬ 30 ዓመት የሞላው ራሱን ኢህአዴግ እያለ የሚጠራ ቡድን በአለም አቀፍ የጦር ወንጀለኝነት መጠየቅ ያለበት የወንጀለኞች ስበስብ ነው፡፡ ከበደኖ ጀምሮ እስከዛሬ በጋምቤላ፣ በሱማሌ ይሄው አሁን ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች በ27 ዓመቱ የወያኔ መሩ ኢሕአዴግ እንደ ኦነግ ከመሳሰሉ ተባባሪዎቹ  ጋር ሆኖ ያደረሰውን  ሁሉ ይታወሳል፡፡ አሁን በኦዲፒ/ኦነግ መሪነት የቀጠለው ኢሕአዴግ በይፋ የሽብር ቡድኖችን በአገሪቱ በማሰማራት በአለም በተፈናቃይ በዛት ቀዳሚ የሆነች አገርን ከመፍጠሩም በላይ በአረመኔ ገዳዮች ሕዝብን እያስጨፈጨፈና ንብረታቸውን እያወደመ ይገኛል፡፡

ያ የባህርዳሩን ድንገተኛውን “መፈንቅለ መንስት” በ30 ደቂቃ ተቆጣጠርንው ያለው ሰውዬ ለወራት ቀን ሲቆጠርለት የነበረውን ጥፋት ሁሉ አዘጋጅቶ እሱ ለሽርሽር አስመራ ሲዝናና ነበር፡፡ ይሄ ነው መሪ እየተባለ የሚዘፈንለት ግለሰብ፡፡ አዎ መሪ ነው ግን መሪነቱ ኢሕዴግ የተባለን የሽብር ቡድን እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳልሆን የምታየውን እውነት መቀበል ስላልወደድህ እውነትን ባልፈለግካት መጠን ቆይቶ የሚመጣውን ትቀበላለህ፡፡ ትግሬ የወያኔ ደጋፊዎችን ምን ፍጡሮች ናቸው ሲል የነበረ ኦሮሞ ዛሬ ተራው ደርሶት በግልጽ ሕዝብን ክዶ አረመኔያዊ ድርጊት እያስፈጠጸም አሁንም እኔ የለሁበትም እያለ የሚቆምረውን ቡድን ዋና ደጋፊ ሆኗል፡፡ አዝናለሁ፡፡ እኔ ቀድሞውንም በሥመ ትግሬ አልነቀፍኩም፡፡ ትግራይ ያለውን ትግሬ አሳምሬ አውቀዋለሁና፡፡ አሁንም በሥመ ኦሮሞ የኦሮሞ ሕዝብን በሙሉ ፍረጃ አልወቅስም፡፡ የበለጠ አውቀዋለሁና፡፡ እየተናገርኩ ያለሁት እነዚህ የአረመኔው ቡድን አጃቢ በሆኑት ላይ ነው፡፡ በማወቅም ባለማወቅም፡፡ ዋናዎቹ ግን ያውቃሉ፡፡

ብዙዎች ጀዋር የሚባል ግለሰብ ለኦሮሞ እየታገለ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ጀዋር ከጅምሩ ጀምሮ የዚሁ ኢሕአዴግ የተባለ ቡድን ተቀጣሪ እንጂ ከኦሮሞ ትግል ጋር አይገናኝም፡፡ ማስተዋል ከቻላችሁ አብይ መጀመሪያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሲል ጀዋር ደንግጦ የነበረው ከወያኔዎች ጋር ሲሰራ የነበረውን ሴራ እንዳይጋለጥበት ነበር፡፡ ጀዋርን ሲንጋፖር የላከው ማን ነው? አሜሪካስ ምን ሚሺን ተሰጠው፡፡ በሳንፎርድ የፖለቲካል ሳይንስ ተምሬያለሁ ይልሀል፡፡ ሳንፎርድ እንደ ወያኔ ኢሕአዴግ ሚስጢሩን አይጠብቅለትም፡፡ ከሳንፎርድ በፖለቲላል ሳይንስ የተመረቁ ተማሪዎቹን ሁሉ በዳታ ቋቱ  አስቀምጦ ያሳያል፡፡ ጀዋር መሀመድን የሚባል ሥም አያውቅም፡፡ ጀዋርን የሚያውቀው ከልጅነት ጀምሮ ያሳደገው ኢሕአዴግ የተባለ የሽብር ቡድን ነው፡፡ አብይ ሚኒሶታ ከመጣ በኋላ  ጀዋር አገር ቤት ገብቶ ሊሰራ የሚችለውን ተመካክሮ እንደነበር አሁን እያየን ነው፡፡ እስከዛ ጊዜ ድረስ ጀዋር እጅግ ደንግጦ ነበር፡፡ እንደሚገባኝ አብይ ጀዋር እንደፈራው ሳይሆን አንድ መስመር ላይ እንደሆኑ ተማምነው ነው የተለያዩት፡፡ ጀዋር አገር ቤት ከገባ በኋላ በይፋ በመንግስት ድጋፍ በየቦታው እየተንቀሳቀሰ ዋነኛ ሥራው ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት ነበር፡፡ አሶሳ ሄዶ የተናገረውን፣ በሻሸመኔ የሆነውን፣ በሀረር በባሌ፣ በበለጠ ግን አጄቶ የተባለን የገዳይ ቡድን ማደራጀትን ነበር፡፡ ሲዳማን በጉልበትም ቢሆን ክልል እናደርጋለን ይልሀል፡፡ የኦሮሞው ጀዋር የሲዳማ አጄቶ አደራጅ፡፡ አጄቶን ለማደራጀት ከፍተኛ ድጋፍ ያደረገለት ደግሞ የአብይ ቡድን ነው፡፡ አጠቃላይ ኦዲፒ/ኦነግ፣ ዋናው ኦነግ እንዲሁም ሌንጮ ባቲ ጨምሮ በዚህ ጉዳይ እንዳሉበት ነው እኔ የሚገባኝ፡፡ ሌጮ ባቲ በከፊል ከሲዳማ ጋር ስለሚተዋወቅ (የኮኮሳ/ዶዶላ) አካባቢ በመሆኑ፡፡

ከመጀመሪያው እየመሰለን ጉዳዩን ለማሳሰብ የሞከርን ነበርን፡፡ ሆን ተብሎ እየተሴረ እንደሆነ ሳንረዳ፡፡ ኦሮሞ በመሆንህ እውነት ክደህ የአብይ ደጋፊ መሆን መብትህ ነው፡፡ የሕዝብህን ሰቆቃ ግን እያበዛሕው ምን አለባትም እስከ መቼም ይሆናል የማትለው አደጋ እየጠራህ እንደሆነ አስብ፡፡ በትግሬነት ወያኔን መደገፍ መብትህ ነው 27 ዓመት ወያኔ በመራው ዘመን ግን ለትግራይ ሕዝብ የሆነለት የተለየ ነገር እንደሌለ ይበልጠውንም በሌሎች እንዲጠላ እንሆነ ግን እንደሆነ ከማንም በላይ ታውቃለህ፡፡ በኦሮሞ እየሆነ ያለው ይሄ ነው ዛሬ፡፡ ከመቼውም በላይ ኦሮሞ በሌሎች ሕዝቦች አይን ጥርጣሬ ውስጥ የገባው ዛሬ ነው፡፡ አሁንም ባለተራ በሚጣ እንዲሁ ከማሰብ የሚከለክለው የለም፡፡ እውነት ግን እውነት ነው፡፡ ዛሬ ኦሮሞና ሲዳማ አንድ ነው በሚል ለሴራቸው እያዘጋጁህ ያጃጅሉሀል፡፡ ከወዲሁ ከአልታሰበበት ነገ ታላቁ መተላለቅ በኦሮሞና ሲዳማ እንደሚሆን አለማሰብ መሬት ላይ ያለውን አውንት አለማወቅ ወይም በሴራው ውስጥ መኖርን ነው፡፡ ይሄን ቃል የምናገረው ሁሉም እንዲያስብበት ነው፡፡ ከምንም ተነስቼ ይሄን አልልም፡፡ የማውቀውን እውነት ግን ሰዎች እንዲያስተውሉ ነው እያጋራሁ ያለሁት፡፡ ወደ ዝርዝሩ አልገባም፡፡  ሲዳማና ኦሮሞ (ሴረኞቹን) ዛሬ ሌሎችን ለማጥፋት አንድ ነን ባሉበት ነገ የሚሆነውን መገመት ብልሕነት ነው፡፡ ይሄ የነጀዋር ዘመዶች ሁለተኛ ሙከራ ነው፡፡ የከዚህ በፊቱን የደርግ ጊዜው እዚህ ላይ አሁን አልጠቅስም፡፡ ለዚህ ግን የአርሲና አካባቢው ክርስቲያን ኦሮሞዎች ራሳቸው ምስክር እንዲሆኑ እጋብዛለሁ፡፡ ምንም እንኳን እውነትን ዛሬ ላይ በኦዲፒ/ኦነግ ደጋፊነት ቢክዷትም፡፡

የዛሬው የኢሕአዴግ መሪን ወደ ውጭ አገር አንድ ነገር እንዲሰራ እያዘዘ የሚወጣ ነው የሚመስለው፡፡ የአሁኑ የሲዳማ ሽብር በተጀመረበት ቀን የአደረጋት የአስመራ ጉዞው ግን ከሁሉም ጊዜ የተሻሻለች ነች፡፡  እስካሁን ከየትኛውም ተቃዋሚ በሲዳማው  በተደራጀው የሽብር ቡድን እልቂት መግለጫ የሰጠ አንድም የተቃዋሚ ድርጅት አልሰማሁም፡፡ በዜጎች ሥም የሚቀልደውና ወደፊትም ለዜጎች ጠንካራ የሆነ ቡድን እንዳይመጣ ለአብይ በቡድን የካድሬነት ሥራ የሚሰራው ኢዜማ የተባለው ቡድን ዛሬም አብይ ከእኔ በላይ ኢትዮጵያዊ ነው የሚሉ ሰባኪዎቹን ወደ ሕዝብ ይልክ ይሆን? በመንግስት ሥልጣን ላይ ያለውም ከኢሕአዴግ  ምንም አንጠብቅም፡፡ ኢሕአዴግ የተባለው የሽብር ቡድን በአለምአቀፍ የጦር ወንጀለኝነት እንዲጠየቅ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጅ የሕግ ባለሙያዎች ቢመክሩበት ጥሩ ነው፡፡ የሚቀጥለውን ምርጫ የተባለውን ሕዝብ ባይጠብቅ ጥሩ ነው፡፡ ኤች  አር 128 ተብሎ ተጀምሮ የነበረውስ ጉዳይ እንዴት ሆኖ ነው ያለቀው?

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከጠላት ይታደግ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

The post ኢሕአዴግ በዓለም አቀፍ ጦር ወንጀለኝነት ሊጠየቅ ይገባል (ሰርፀ ደስታ) appeared first on ሳተናው: Satenaw Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!.


ኢሕአዴግ በዓለም አቀፍ ጦር ወንጀለኝነት ሊጠየቅ ይገባል (ሰርፀ ደስታ)