የአማራን ሕዝብ ድምፅ የማፈን የገዥዎች ጉዞ ተጠናክሮ ቀጥሏል! – ጌታቸው ሽፈራው

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

በሰኔ 15ቱ ክስተት ሰበብ የተፈፀመው የጅምላ እስር እንቆቅልሾች!

የሰኔ 15ቱን ክስተት ገዥዎቹ “መፈንቅለ መንግስት” ብለው ተቻኩለው ሲፈርጁ ብዙዎች ከክስተቱ ጀርባ “ምን አለ?” ብለው እንዲጠራጠሩ ምክንያት ሆኗል። የሰኔ 15ቱ ክስተት መፈንቅለ መንግስት ተብሎ በችኮላ ቢፈረጅም በዚህ ሰበብ የታሰሩትን ጠርጥረናችኋል ያሏቸው የ”ለውጡ ኃይል” እፀየፈዋለሁ ብሎት በነበረው የ”ፀረ ሽብር አዋጅ” ነው። ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ “አሸባሪው ኢህአዴግ ነው” ብለው በፓርላማ ተናግረዋል። ይህን ያሉት በፀረ ሽብር አዋጁ ሲከሰሱ ለነበሩት ንፁሃን ጥብቅና ቆመው ነው፣ ይህን ሲሉ የፀረ ሽብር አዋጁ ያለ አግባብ ተግባር ላይ ሲውል እንደነበር ለመግለፅ የተጠቀሙበት ነው። ይሁንና ከአንድ አመት በኋላ የራሳቸው አስተዳደር እፀየፋለሁ ያለውን የሽብር አዋጅ በመፈንቅለ መንግስት ተጠርጥረዋለወ የተባሉትን በመክሰስ እየተጠቀመበት ይገኛል።በዚህ ሂደት በርካታብ ሀሰቶች ተስተውለዋል። ለምሳሌ ያህል ጥቂቶቹን ብቻ እንጥቀስ:_

1) ዋናውና ትልቁ ስህተት ከታሰሩት መካከል አብዛኛዎቹ ንፁሃን መሆናቸው ነው። የአስራት ጋዜጠኞች አዲሱን ገዥ ቡድን አጋለጣችሁ ተብለው እንደታሰሩ በምርመራ ወቅት የሚጠየቁትን ማስታወስ በቂ ነው። የአሥራት ጋዜጠኞች በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈፀሙ ጥቃትና ወረራዎችን (የአጣየና ከሚሴ) በማጋለጣቸው፣ በማንነት ስለሚፈናቀሉት በመዘገባቸው፣ የኦዴፓ አመራሮችን ስህተት በመዘገባቸው ወንጀል ሆኖባቸዋል። ተጠርጥራችኋላ የተባሉት በሰኔ 15 ክስተት ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ምርመራ አልተደረገባቸውም። በመፈንቅለ መንግስት ሰበብ ቢያስሯቸውም ፍርድ ቤት የሚያመላልሷቸው በሽብር ብለው ነው።

የአብን አባላትና አመራሮች የታሰሩት የአማራን ሕዝብ በማደራጀታቸው ካልሆነ በስተቀር በሰኔ 15ቱ ተሳትፎ ኖሯቸው አይደለም። የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት አባላት፣ በየ ክልሉ የሚኖሩ አማራዎች፣ የጉምሩክን ገመና ያጋለጡ አማራዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመድረክ የሞገቱ አማራ የሕግ ባለሙያዎች በጉዳዩ እንደሌሉበት ይታወቃል። እነዚህ ንፁሃን ሕዝብን ያነቃሉ በመባላቸው ብቻ ሰበብ ተፈልጎላቸው ታስረዋል። የመጀመርያው ስህተት ንፁሃንን ሰበብ ፈልጎ ማሰሩ ነበር።

2) የሰኔ 15ቱ ክስተት መፈንቅለ መንግስት አለመሆኑ ግልፅ ነው። የተፈፀመው ግድያ ነው። የሚጠየቁ አካላት መጠየቅ ከነበረባቸው መጠየቅ ይገባቸው የነበረው በግድያ ነው። የግድያ ወንጀል የሚዳኝበት ሕግ ደግሞ በወንጀለኛ መቅጫው በግልፅና በዝርዝር ተመልክቷል። ሆኖም ግድያ ሲሆን “መፈንቅለ መንግስት”፣ በ”ሽብር” እንደሚባለው የከበደ አያደርገውም።

3) የሰኔ 15ቱ ክስተት መፈንቅለ መንግስት ባይሆንም፣ በሀሰት መፈንቅለ መንግስት ነው ብለው ከፈረጁት ታሳሪዎቹ መጠርጠር የነበረባቸው ቢያንስ በሀሰት በፈረጁት ወንጀል ነበር። መፈንቅለ መንግስት የሚዳኝበት ሕግ ደግሞ በወንጀለኛ መቅጫው ላይ በግልፅ ሰፍሯል። ሆኖም ሰበብ ተፈጥሮላቸው የታሰሩት ንፁሃን ተጠረጠሩ የተባሉት በመፈንቅለ መንግስት ሳይሆን በድሮው የሽብር አዋጅ ነው። ይህ ትልቁ እንቆቅልሽ ነው።

4) ኢህአዴግ የፀረ ሽብር አዋጁ ያለ አግባብ እንደዋለ ገምግሜያለሁ ብሎ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “አሸባሪው ኢህአዴግ ነው” ብለው በይፋ በፓርላማ ተናግረዋል። ይሁንና እንደ አዲስ ንፁሃን በሽብር “ወንጀል” እየተጠረጠሩ ነው። ይህ ሌላኛው እንቆቅልሽ ነው። ሌላኛው የሰኔ 15 ሀሰት መገለጫ ነው።

5) የሰኔ 15ቱን ክስተት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ አዴፓ ጠቅልለው የሰጡት ለጄ/ል አሳምነው ፅጌ ነው። “መፈንቅለ መንግስት” ብለው ተሻኩለው እንደፈረጁት ሁሉ ለጄ/ል አሳምነው ሲሰጡ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ይህን ጉዳይ ፈፅመውታል ተብለው በኢህአዴግ ሊቀመንበርም፣በአዴፓም የተወነጀሉት ሰው የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ ናቸው። ጄ/ል አሳምነው ፅጌ ይህን ወንጀል ፈፅመውታል ከተባለ የአሥራት ጋዜጠኞች፣ የባለ አደራ ምክር ቤት አባላት፣ የአብን አባላትና አመራሮች የሚታሰሩበት ምክንያት የለም። ጄ/ል አሳምነው ፅጌ ፈፀሙት ከተባለ ሊታሰሩት የሚገባቸው፣ ሊመረመሩ የሚገባቸው የኢህአዴግ ሰዎች እንጅ የተቃዋሚው ጎራ ሰዎች አልነበሩም። ኢህአዴግም ሆነ አዴፓ ጉዳዩን ጄ/ል አሳምነው ፅጌ ላይ ከደፈደፈ ችግሩ የራሱ ነው የሚሆነው። አዴፓም ኢህአዴግም ከተጠያቂነት ሊያመልጡ አይችሉም። የአዴፓ አመራር ይህን ወንጀል ፈፀመው ብለው ካመኑ አስራት፣ አብን፣ ባለ አደራ፣ በየ ክልሉ ያሉ አማራዎች የሚያገባቸው ነገር አልነበረም።

ይህ ሁሉ እንቆቅልሽ የሰኔ 15ቱ ሀሰት መገለጫ ነው። ሰበብ፣ አማራን ማጥቂያ መሆኑን ማሳያ ነው። የአማራን ሕዝብን ትግል ለማዳከም ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ ሰበብ መሆኑን ጥሩ ማሳያ ነው።

 

ፖሊስ ዛሬ ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ እና ጌታቸው አምባቸውን ፍርድ ቤት ወስዷቸው ነበር። ዋናው አላማ በረራ ጋዜጣን ለመዝጋት ነው ተብሏል። የበረራ ጋዜጣ አሳታሚ የሆነውን ጋፋት ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ላይ ክስ ለመመስረት መሆኑ ተጠቁሟል። ጌታቸው አምባቸው “በስም መመሳሰል ነው” ተብሎ እንዲመለስ ተደርጓል ተብሏል።

በዚህ አጋጣሚ ለአማራው ልሳን የሆኑትን በረራ ጋዜጣና አስራት ቲቪ ላይም የሽብር ክስ ለመመስረት ወደኋላ እንደማይሉ መረጃዎች ደርሰውናል። የአማራውን ድምፅ ለማፈን የሚደረገው ጉዞ ቀጥሏል። ሆኖም የአማራውን ሰቆቃ እስካልቆመ ድረስ የአማራውን ድምፅ ማፈን እንደማይችሉ እሙን ነው!

ማስገንዘቢያ:_ በዚህ ገዥዎቹ የአማራን ድምፅ ለማፈን በሚጥሩበት ወቅት በተለይ በውጭ ያላችሁ ወገኖች አሥራትን ለማበርታት ትልቅ ግዴታ ተጥሎባችኋል። በዚህ ገዥዎች የአማራውን ድምፅ ለማፈን በሚሰሩበት ወቅት የአማራን ድምፅ የሚሆኑትን ተቋማት አለማገዝ ለአማራ እቆማለሁ ከሚባል የሚጠበቅ አይደለም። ገዥዎች ድምፅ ለማፈን በሚጥሩበት ወቅት ሆን ብሎም ይሁን፣ በተሳሳተ መንገድ፣ በመናቆርና እርስ በእርስ በመታገል የአማራ ተቋማትን ለማቀጨጭ የሚሰራ ካለ ደግሞ የገዥዎቹን ተግባር ለማገዝ እየሰራ መሆኑን ሊገነዘበው ይገባል።

The post የአማራን ሕዝብ ድምፅ የማፈን የገዥዎች ጉዞ ተጠናክሮ ቀጥሏል! – ጌታቸው ሽፈራው appeared first on ሳተናው: Satenaw Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!.


የአማራን ሕዝብ ድምፅ የማፈን የገዥዎች ጉዞ ተጠናክሮ ቀጥሏል! – ጌታቸው ሽፈራው