ቦሪስ ጆንሰን ሃገራቸው የአውሮፓ ህብረትን ለቃ በምትወጣበት መንገድ ዙሪያ አዲስ የድርድር ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችላሉ ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 12 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሃገራቸው የአውሮፓ ህብረትን ለቃ በምትወጣበት መንገድ ዙሪያ አዲስ የድርድር ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችላሉ ተባለ።

ቴሬዛ ሜይን የተኩት ቦሪስ ጆንሰን ሰሞኑን በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በሚያደርጉት ጉብኝት፥ ብሪታንያ ህብረቱን ለቃ ከምትወጣበት ሁኔታ ጋር በተያያዘ አዲስ የድርድር ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችላል እየተባለ ነው።

ብሪታንያ በመጭው ጥቅምት ወር መጨረሻ በስምምነት ወይም ያለ ስምምነት ህብረቱን ለቃ ትወጣለች ተብሎ ይጠበቃል።

እርሳቸውም ሃገራቸው በተቀመጠው ቀነ ገደብ መሰረት እንደሚያስወጧት ቃል ገብተዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ አፈትልከው የወጡ መረጃዎች ደግሞ ቦሪስ ጆንሰን በፈረንሳይና ጀርመን በሚያደርጉት የስራ ጉብኝት በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ድርድር እንደሚኖር ይገልጻሉ።

ሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የወጣው መረጃም ብሪታንያ ከህብረቱ ጋር ያለ ስምምነት ከተለያየች የቦሪስ ጆንሰን አስተዳደር በስጋትነት ያስቀመጣቸውን ጉዳዮችም ይፋ አድርጓል።

በዚህም የምግብና የህክምና መድሃኒት አቅርቦት እጥረት እንዲሁም የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪና የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ለብሪታንያ ቀጣይ ስጋቶች ተብለው ተለይተዋል።

ከዚህ ባለፈም ከአየርላንድ ጋር ያለው የድንበር ጉዳይም ትልቅ የተቃውሞ ምክንያት ሊሆን ይችላልም ነው የሚለው ጋዜጣው አገኘሁት ያለው መረጃ።

የዋጋ መወደድን ምክንያት ያደረገ ማህበራዊ ቀውስና የአውሮፕላን ትራንስፖርት መዘግየትና መስተጓጎልም በስጋትነት ተቀምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለህብረቱ አባል ሃገራት በፍቺው ዙሪያ አዲስ የመደራደሪያ ሃሳባቸውን ሊያቀርቡ ስለመዘጋጀታቻውም ነው የተሰማው።

ይሁን እንጅ የመደራደሪያ ሃሳቦቹ በስጋትነት በተቀመጡ ጉዳዮች ላይ ስለመሆን አለመሆናቸው ግን የተባለ ነገር የለም።

የቦሪስ ጆንሰን አካሄድ ግን በህብረቱ ሰዎች ዘንድ የተወደደ አይመስልም፥ የብራሰልስ ሰዎች አሁንም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አካሄዳቸውን ቆም ብለው እንዲያስቡበት ጠይቀዋል።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ

 


ቦሪስ ጆንሰን ሃገራቸው የአውሮፓ ህብረትን ለቃ በምትወጣበት መንገድ ዙሪያ አዲስ የድርድር ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችላሉ ተባለ