በአዲሱ አመት የሚያራርቁ ሀሳቦችን በውይይት መፍታትያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመጭው አዲስ አመት የሚያራርቁ ሀሳቦችን በውይይት ለመፍታት ሀገራዊ የዕርቅ ዕሴቶችን በመጠቀም ለህዝቦች ሰላምና አንድነት ለመስራት መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ታዋቂ ግለሰቦች እና ፖለቲከኞች ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና የኢጋድ አባል ሀገራት በንግድ የተሰማሩ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ፥ ከሚያራርቁ ሀሳቦች ይልቅ በሚያቀራርቡን ዕሴቶች ላይ መስራትን በመሸጋገሪያው ጳጉሜን ወር ላይ ቆመን ማሰብ አለብን ብለዋል።

በየማህበረሰቡ መሰረት የሆነው ቤተሰብ በልጆቹ ላይ መስራት ይኖርበታል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ የጋራ እሴቶችን ጠንቅቀው እንዲያውቁና በውይይት ችግሮችን የሚፈቱ እንዲሆኑ ቤተሰብ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ነው ያሉት።

ሰላምና ፍቅር የሚነግሱበት አመት ይሆን ዘንድም መንግስት ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ መስራትና የውይይት ባህል ማደግ ይኖርበታል ሲሉም ሃሳባቸውን ያጋራሉ።

የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ የኋልዮሽ ማረም የማይቻሉ ክስተቶች በመጭው አዲስ አመት ኑረት ውስጥ የሚከተቡ እንደማይሆኑ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ፖለቲከኛው አቶ ገብሩ አስራት ደግሞ መንግስት ህግና ስርዓትን ማስጠበቅ የአዲሱ አመት የመንግስት ቀዳሚው የቤት ስራ መሆን እንዳለበት ያነሳሉ።

የዜጎች መፈናቅልና ተንቀሳቅሶ የመስራት ህገ መንግስታዊ መብቶች እንዲጠበቁም መንግስት እንዲሰራ አሳስበዋል።

ፖለቲከኛው አቶ መሸሻ ዮሴፍ በበኩላቸው የሀገሪቱን ሰላም ያናጋውና መረጋጋትን ህዝቦች እንዲናፍቁ ያደረገው 2011፥ ለዘርፈ ብዙ ክስረትና የሀገሪቱን አንድነት በመፈታተን በጥላቻ የተደፈቁ ፖለቲከኞችም እርስ በእርስ ህዝቦችን ለማጋጨት የተንቀሳቀሱበት እንደነበረም አስታውሰዋል።

ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም በበኩሉ በመጭው አመት አለመግባባት እንኳን ድንገት ቢከሰት በኢትዮጵያዊ የእርቅ ዕሴቶች መፈታትን በመለማመድ ልንሻገርው ጫፍ ላይ በደረስንበት አመት የተከሰቱ ጥፋቶች ሊታረሙ ይገባል ብሏል።

ከጳጉሜን ቆፈን ከሚያላቅቀው መስከረም ወዲያ ባሉት ጊዜያትም የህዝቦች የተጋመደ እሴት ሊጠበቅ እንደሚገባውም አንስቷል።

በአዲሱ አመት መከባበር ጎልብቶ የከረረ ጥላቻ በፍቅርና አንድነት ሙግት የሚላላበት እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ሀላፊነት መወጣት እንዳለበት አስተያየት ሰጭዎቹ ይገልጻሉ።

 

በሀይለየሱስ መኮንን


በአዲሱ አመት የሚያራርቁ ሀሳቦችን በውይይት መፍታትያስፈልጋል ተባለ