ፍትህ የነገሰባት ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ሁሉም አካላት ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አሳሰቡ

“እኔ የህግ ተገዢ ነኝ!” በሚል መሪ ቃል ሲከበር የቆየውን የፍትህ ወርና በዛሬው ዕለት የተከበረው የፍትህ ቀን ማጠቃለያ ዝግጅት በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

በስነ ስርዓቱም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መአዛ አሸናፊን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ቀኑን አስመልክተው በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንተ ሳህለወርቅ ዘውዴ፥ ፍትህ ለአንድ ማህበረሰብ ዳኝነት ብቻ ሳይሆን አንድን ስራ በፍትሃዊነት ማከናወን መቻል ነው ብለዋል።

ከፍትህ ውጭ የሚታሰብም ሆነ ገቢራዊ የሚሆን ነገር እንደሌለ የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፥ ልማትና ዴሞክራሲን ለማፋጠን የፍትህ መስፈን የማይተካ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል።

ፍትህ የይስሙላ ወይም የግብር ይውጣ ስራ ከተደረገ ግን ዜጎች በፍትህ ተቋማት ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ ከማድረጉም በላይ እምነት እንዳይኖራቸው ያደርጋልም ነው ያሉት።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አክለውም የፍትህ ስርዓቱ በዜጎች ዘንድ ተቀባይነትና እምነት የማይኖረው ከሆነ አንድነትን በመሸርሸር ህዝብና ሀገርን የሚበትን መሆኑን ጠቁመዋል።


ፍትህ የነገሰባት ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ሁሉም አካላት ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አሳሰቡ