ኢትዮ ቴሌኮም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 6 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይዎት ታምሩ አዲሱ ዓመት የብልጽግና እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የተቋሙ ሰፕላይ ቼን ዲቪዥን ኦፊሰር ወይዘሮ በለጡ ዴላሞ እንዳሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፥ አዲሱ ዓመት በጎ ተግባራት በስፋት የሚከናወኑበት እንዲሆን ተመኝተዋል።

የዋናው መስሪያ ቤት የሰፕላይ ቼን ዲቪዥን ክፍል ሰራተኞች በዛሬው ዕለት የ2012 አዲስ ዓመት ዋዜማን፥ ቦሌ ቡልቡላ በሚገኘው ክብረ አረጋውያን የአረጋውያን መርጃ ማዕከል በመገኘት አክብረዋል።

የዲቪዥኑ የስራ ሃላፊዎች እና ሰራተኞችም ለአረጋውያኑ የበግ፣ የአልባሳት እና የ45 ሺህ ብር ስጦታ ለማዕከሉ አበርክተዋል።

የሰፕላይ ቼን ዲቪዥን ኦፊሰር ወይዘሮ በለጡ ዴላሞ የዛሬው ድጋፍ ተቋሙ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገው ተሳትፎ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በማዕከሉ የሚገኙ አረጋውያን በበኩላቸው የተቋሙ ሰራተኞች የበዓሉን ዋዜማ አብረዋቸው ለማሳለፍ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የማዕከሉ መስራች እና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ አረጋውያንን መጎብኘት ከፍተኛ የመንፈስ እርካታ እንደሚሰጥ ጠቅሰው፥ ኢትዮ ቴሌኮም ላደረገው በጎ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።

ክብረ አረጋውያን የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ከ120 በላይ አረጋውያንን በመንከባከብ ላይ ይገኛል።

 

 

በመለሰ ምትኩ

 

 

 


ኢትዮ ቴሌኮም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ