አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከ190 ሺህ ዶላር በላይ ህገወጥ ገንዘብ በቁጥጥር ስር አዋለ

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከ190 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር፣ 2 ሺህ 100 ዩሮ እና ከ729 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ብር ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት፣ ከከተማው ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ እንዲሁም ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሠው ሠራሽ የዋጋ ግሽበትን እና በህገ-ወጥ መንገድ የሚከናወኑ የውጪ ሃገራት ገንዘቦች ምንዛሬን ለመቆጣጠር እርምጃ ወስዷል፡፡

በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 7 በተለምዶ ቀይ መስቀል አካባቢ በግለሠቦች ቤት እና በተሸከርካሪ ውስጥ ጭምር በህገ-ወጥ መንገድ የሚከናወኑ የውጪ ሃገራት ገንዘቦችን ይመነዝራሉ በተባሉ ግለሰቦች ላይ በተደረገው ክትትል ውጤቱ ሊገኝ ችሏል፡፡

በሸቀጦች ላይ የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት በሚያደርጉ ግለሠቦች መጋዘን ላይ በተደረገው ድንገተኛ ቁጥጥርም 198 ኩንታል ቡና፣ 21 ኩንታል ዱቄት 205 ኩንታል በርበሬ እና በርካታ ጀሪካን የፓልም ዘይት ተከማችተው ተገኝተዋል፡፡

በተጨማሪም 100 የንግድ ተቋማት ፈቃድ ሳይኖራቸው የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሲሸጡ ተገኝተው እንዲታሸጉና 8 የንግድ ቤቶች ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው መደረጉን የአ/አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

እንደዚህ አይነት ወንጀሎች የሀገርን ኢኮኖሚ የሚጎዱና የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮን የሚያቃውሱ በመሆኑ ወንጀሎቹን ለመከላከል ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር ተባብሮ የመስራት እና ጥቆማ የመስጠት ልምዱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽኑ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ፖሊስ ኮሚሽን/ EBC