በበጀት አመቱ 6 አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ይጀመራል

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት አመቱ 6 አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚጀመር የውሀ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ ተናገሩ።

የመስኖ ልማት በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ እና ወቅትን ጠብቀው ምርት ለሚያመርቱ ሀገራት አማራጭ ነው።

የውሀ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ በዚህ አመት ለመስኖ ዘርፍ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በበጀት አመቱም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ ይችላሉ የተባሉ እና ለመስኖ ልማት አመች የሆኑ ቦታዎች ተመርጠዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት ባለፈው አመት የዲዛይን ስራ የተከናወነላቸው 6 አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማልማት እየተሰራ ነው።

በአሁኑ ሰአትም የመስኖ ፕሮጀክቶቹ የሚገነቡባቸውን ቦታዎች ከመለየት አልፎ የጨረታ ሂደታቸውን በማጠናቀቅ ግንባታቸውን ከሚያከናውኑ የስራ ተቋራጮች ጋር ውል ታስሮ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቶቹ በተለያዩ ክልሎች የሚገነቡ ሲሆን በአዲስ አበባ አቅራቢያም አንድ የመስኖ ፕሮጀክት ይገነባል ነው የተባለው።

ከሚገነቡት አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች ውስጥ በአዲስ አበባ ዙሪያ አድአ በቾ 5 ሺህ ሄክታር መሬት የሚያለማ የመስኖ ፕሮጀክት ይገኝበታል።

እንዲሁም በአማራ ክልል 5 ሺህ ሄክታር መሬት የሚያለማና በላይኛው ርብ የሚገነባና ፎገራን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመስኖ ፕሮጀክትም አዲስ ከሚገነቡት መካከል ይጠቀሳል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

ፕሮጀክቶቹ አጠቃላይ 32 ሺህ ሄክታር መሬትን ማልማት የሚችሉ ሲሆን፥ 64 ሺህ ቤተሰቦችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ፕሮጀክቶቹ ከግንባታ ጀምሮ እስከ መስኖ ልማት ድረስ ከ2 እስከ 3 መቶ ሺህ ለሚሆኑ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩም ይታመናል።

አዳዲሶቹ የመስኖ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደታቸው ከ1 እስከ 3 አመት ጊዜ ይወስዳል ተብሏል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዳዲስ የመስኖ ግንባታዎችን ከማከናወን ባለፈ የተጓተቱ የመስኖ ፕሮጀክቶችንም በዚህ አመት ለማጠናቀቅ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።

በተለይም ከ15 ቢሊየን ብር በላይ ወጪን የሚጠይቀው እና የግንባታ ሂደቱ የዘገየው የዛሪማ የመስኖ ግድብን ለማጠናቀቅ ስራዎች እየተከወኑ ነው ብሏል።

የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ አሁን ላይ 67 ከመቶ የደረሰ ሲሆን፥ እንደ ዝዋይ እና መገጭ የመሳሰሉ የህብረተሰቡ ጥያቄዎች ያሉባቸው የመስኖ ግድቦችንም በዚህ አመት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራም አስታውቋል።

አዳዲሶቹን ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማስጀመር እንዲሁም የተጓተቱትን ፕሮጀክቶች ለመጨረስ በአጠቃላይ ለአመቱ የመስኖ ልማት ስራም 14 ቢሊየን ብር በጀት ተመድቧል።

 

 

 

በዙፋን ካሳሁን

 


በበጀት አመቱ 6 አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ይጀመራል