‘ፍላጎታችን ወደፊት ድርጊታችን ወደኃላ!’ (ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ)

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡2009 እና የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

የሀገራችን ነባራዊ ኹለንተናዊ ኹኔታን በተመለከተ ከተለያየ አቅጣጫ የተለያዩ ሀሳቦች ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ በመነሣትም ላይ ይገኛሉ፡፡ ለወደፊቱም ቢኾን መነሣታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ቆም ብሎ ማሰብ፣ መመራመርና ማሰተዋል እጅግ አስፈላጊ ኾነና የሚከተለውን ሀሳብ ለመወያየት እናንሣ፡፡

በአለም እጅግ ረዥም እድሜ ያስቆጠረ ታሪክ አላቸው ከሚባሉ ቀዳሚ ሀገራት ተርታ የምትመደበው ሀገራችን በ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አንሥቶ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ሳይኖራት በመሳፍንት በየአካባቢውና በየመንደሩ በባለ ኃይሎች ስትናጥ – “ዘመነ መሳፍንት” በተሰኘ ጊዜ ውስጥ እንደቆየች የታሪክ መዛግብት ያለ ልዩነት ያስቀምጣሉ፡፡

ያ ጊዜ በተለይም ከዛ ቀደም ባሉት ሁለት ክፍለ ዘመኖች ጀምሮ አለም (በተለይ ምዕራብ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ) እጅግ በከፍተኛ ደረጃ በ20ኛው ክፍለ ዘመንም ኾነ ዛሬ ላለንበት ኹለንተናዊ (ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ) ነባራዊ ኹኔታዎች ገዢ የኾኑ በርካታ ነገሮች በእጅጉ የተከሰቱበትና ክስተቱም የአለም ሕዝብን ኹለንተናዊ አኗኗር እንደቀየረ ይታወቃል፡፡

አለም በ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽና በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የአብዮት ጊዜ (Age of Revolution: 1774 – 1849 እ.አ.አ) ላይ ኾነው በዋናነት ከነገሥታትና ፍጹም ዘውዳዊ ከኾነ ሥርዓት ወደ በሕገ መንግሥት ወደ ሚተዳደር መንግሥትና ሪፐብሊክ የተቀየሩበት፤ ቅያሬው በውስጡ ግለሰብን (ነገሥታትን) ማዕከል ካደረገ የሥልጣን ፖለቲካ ኹለንተናዊ ትግሎች ወደ ቡድናዊና ተቋማዊ እንቅስቃሴ የተሻገሩበት ጊዜ ነበር፡፡

ከኢኮኖሚያዊ ዕሳቤ አንጻር ከ16ኛው እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን ያለውን የሚያካትተው በዋናነት ንግድና የንግድ መስመር ኹለንተናዊ እንቅስቃሴን የያዘው መርከንታሊዝም (Mercantilism) እንዲሁም ከእሱ ጋር ተሳስሮ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የዳበረው የግብርና ምርትንና ምርታማነትን በዋናነት ማዕከል ያደረገው የፊዝዮክራሲይ (Physiocracy) ሂደት ለረዥም ዘመናት የቆየውን ዕሳቤ በትምህርትና በሳይንስ በመገዳደርና የበላይ በመኾን ረገድ ትልቅ ሚና ከተጫወተው የአብርኾት ጊዜ (Age of Enlightenment) /ከ1650 እስከ 1780 እ.አ.አ/ ጋር የፈጠረው ኹለንተናዊ ትስስር በአለም ሕዝቦች የአኗኗር ዘይቤ ላይ ያስከተለው ለውጥ በኹለንተናዊ መንገድ ከፍተኛ እንደኾነ አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል በርካታ አብዮቶች – በአሜሪካ (1765 – 1783 እ.አ.አ)፣ ፈረንሳይ (1789 – 1799 እ.አ.አ)፣ የአይሪሽ አመጽ (1798 እ.አ.አ)፣ የሃይቲዎች በፈረንሳይ ቅኝ ግዛትና ባሪያ ንግድ (1791 – 1804 እ.አ.አ)፣ የባሪያዎች አመጽ በደቡብ አሜሪካ፣ የመጀመሪያው የጣልያን የነጻነት ጦርነት (1848 – 1849 እ.አ.አ)፣ የሲሊያኖች (1848 እ.አ.አ)፣ እና በጣልያን (1848 እ.አ.አ) አብዮቶች ከመካሄዳቸውም በላይ የአለምን ሕዝብ አኗኗር በመለወጥ ረገድ ወሳኝ ጉልህ ሚና በመጫወት ለከተማዊ ሕይወት በእጅጉ መስፋፋትና ለብዙ ለውጦች ትልቅ ግብዓት የኾነው የኢንዱስትሪ አብዮት (1760 – 1840 እ.አ.አ) በ18ኛው ክፍለ ዘመን የምክንያታዊነት (Age of Reason) አልያም የአብርሆት ጊዜን (Age of Enlightment) ተከትሎ እንደመጣብሎም ከሥልጣን ፖለቲካ ወደ ፖለቲካ ኹለንተናዊ ሽግግር ያደረጉበት፤ የሊበራሊዝም አስተሳሰብ ነጥሮ የወጣበትና የአብርኾት መርሆች የዳበሩበት፤ ከውስጥ ትግል ወደ ውጭ ትግል ያመሩበት፤ በጋራ ከመተጋገል ወደ ጋራ በጋራ ስለጋራ መጠቃቀም ያደጉበት ዋነኛ የምዕራፍ ጊዜ መኾኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

እነዚህ ለውጦች እንዲሁ በቀላሉ በአንድ ቦታ የቆሙና የሚቆሙ ሳይኾኑ እርስ በራሳቸው እየተጠላለፉ ኹለንተናዊ (Multidimensional) እና ኹለገብተጽዕኖ (Multidimensional Effect) በማሳረፍ በቀጣይና አኹን ድረስ ለዳበሩና በመዳበር ላይ ላሉ የትራንስፖርት፣ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ፣ የባሕል፣ የትምህርት፣ የቴክኖሎጂ፣ የፖለቲካ አስተዳደር፣ የሙያ መበራከት፣ – – – ወዘተ ለውጦችና ግኝቶች መዳበርና መስፋፋት ታላቅ ግብዓት በመኾን በሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ኹለንተናዊ የአኗኗር እንቅስቃሴ/ዎች ውስጥ የአኗኗር ዘይቤውን በመቀየር እጅግ የጎላ አስተዋጽዖ እንዳለው እንረዳለን፡፡

ከታሪክ መነሻነት እጅግ የሩቁን ትተን በዘመነ መሳፍንትና ከዘመነ መሳፍንት በኃላ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግሥት ታሪክ ባሉት አራት ነገሥታቶቻችንበአጼ ቴዎድሮስ (1855 – 1868 እ.አ.አ)፣ በአጼ ተክለ ጊዮርጊስ II (1868 – 1871 እ.አ.አ) ፣ በአጼ ዮሃንስ IV (1871 – 1889 እ.አ.አ) እና በአጼ ምኒሊክ II (1889 – 1913 እ.አ.አ) ምን ይመስል እንደነበር ታሪካችንና ከዛ ዛሬም ድረስ የወረስናቸው ቀላል የማይባሉ ማንነቶቻችንና የማንነቶቻችን አካሎች ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡

እኛ በዛን ጊዜ እጅጉን ተኝተንና አንቀላፍተን ነበር፡፡ ሌሎች – አለም ከዚያ ቀደም አይታ በማታውቃቸው ኹለንተናዊ አብዮቶች ስትናጥ እኛ በለመድነውና ለረዥም ዘመናት በኖርንበት የሥልጣን ፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ ነበርን፡፡ እነሱ ከራሳቸው ወደ ሌላው ሲያልፉ እኛ ወደ ታች፤ ከማዕከል ወደ ከባቢያዊነት ወርደን ቆየን፡፡ እነሱ ድንበር ሲሻገሩ እኛ ከባቢያዊ ድንበርን ማስፋት ላይ ተጠምደን፤ ዕሳቤና ኹለንተናዊ ኢንዱስትሪ ሲያበለጽጉና – አበልጽገውም አለምን ለማጥለቅለቅ ሲተጉ – እኛ ግን ከነበርንበት ወርደን ነበር፡፡ ያ ልዩነት! ያ ክፍተት! ያ መራራቅ! ያ መለያየት! ዛሬም ድረስ ኹለንተናዊ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል፡፡

እንደሀገር ዲሞክራሲ፣ ነጻነት፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ፍትሃዊነት፣ ፍትህ፣ መልካም አስተዳደር፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ የሰብዓዊና ዲሞከራሲያዊ መብት መከበር፣ ዕድገት፣ ልማት፣ – – – ወዘተ ያለ ኹለንተናዊ የጾታ፣ የሃይማኖት፣ የሀብት (የመደብ)፣ የትምህርት፣ የእድሜ ልዩነት እያንዳንዱ ዜጋ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ያለ ይፈልጋል፡፡ ትልቁ ጥያቄ መፈለጉ ሳይኾን የፈለጉትን የማግኘት ነው፡፡ አስፈላጊነቱ ፈጽሞ አያጠያይቅም፡፡ ፈጽሞ አያከራክርም፡፡ የሚያጠያይቀው፣ የሚያከራክረውና የሚያለያየው የሚፈለጉትን ኹለንተናዊ ፍላጎት/ቶች የማግኛና የማረጋገጫ – መንገዶች፣ አይነታቸው፣ መጠናቸው፣ ስርጭታቸውና ጥራታቸው ነው፡፡

እነዚህም እንደነበርንበትና እንዳለንበት ኹለንተናዊ የአስተሳሰብና አመለካከት ደረጃ የሚወሰን ብቻ ሳይኾን መኾን እንደምንፈልግበት የሀሳብና ዕሳቤ ደረጃ ኹለንተናዊ ሂደት የሚወሰን ኾኖ እናገኘዋለን፡፡

ከላይ ከመግቢያው ሶስተኛ አንቀጽ አንሥቶ እንደቀረበው በኛና በተቀረው አለም (በተለይ በምዕራብ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ) እጅግ ሰፊ ልዩነት አለን፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የነሱ አስተሳሰብና አመለካከት በአለም አቀፍ ኹለንተናዊ (ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ) እንቅስቃሴዎች ውስጥ ለነሱ ጥቅም ማስጠበቂያነት፣ ከኹለንተናዊ መስተሳስራዊ ግንኙነት (unavoidable relationship) ፣ ከሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን /globalaization/) በኹለንተናዊ መንገዶች መስፋፋት፣ ከሰው ልጅ አለም አቀፋዊ ጠባይ መወራረስ የተነሣ አልያም ከኹለንተናዊ የሂደት ውጤትና ተጽዕኖ የተነሣ በሰፊው የሚቀነቀን ነው፡፡

እነሱ ዘሩን ለዘመናት እየወደቁና እየተነሡ፣ እየጣሉና እያነሱ፣ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው ባዳበሩት ኹለንተናዊ መሣሪያዎች በመታገዝ በቅድሚያ የዘር መዝሪያውን ቦታ ሲያዘጋጁና ለማዘጋጀት ሲገደዱ፤ እርስ በራሱም እንዲቀናጅ ካደረጉ በኃላ በሂደት በተቋማዊነት የሚዘወርበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ተጠቃሚነታቸውን በማጉላት በውስጥ ብቻ ሳይኾን ወደ ውጭ በማውጣት የብዙ ታዳጊ ሀገራትን ምሁራን፣ ደራሲዎች፣ ጸሐፍቶች፣ ገዥዎች፣ መሪዎች፣ የፖለቲካ ኃይሎችና ባለሙያዎችን በተለያየ መንገድ በመሳብ አለፍ ሲልም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻቸው፣በአለም አቀፍ ድርጅቶቻቸውና ጥምረቶቻቸው፣ በሚድያዎቻቸው፣በመጻሕፍቶቻቸው፣ በአስተምህሮቶቻቸውና ዲስኩሮቻቸው፣ በአለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ብሎም ቀጠናዊ ስምምነቶቻቸው፣ በባሕል ኢንዱስትሪያቸውና በንግድ እንቅስቃሴዎቻቸው በግለሰብ፣ በቡድንና በተቋም ደረጃ ቧንቧ በማድረግ እየተጠቀሙብን እንደሚገኙ ማንም አስተዋይ በቀላሉ ሊረዳው የሚችል ነው፡፡

በቃላት ጣፍጠው፣ በጽንሰ ሀሳብ ተሰባጥረው፣ በአመክንዮ ተሸፋፍነው፣ በማዕቀፍ ተምታተው፣ በተለያዩ ስምምነቶችና ቅድመ ኹኔታዎች ታጥረው የሚመጡልንን እንዳለን ነባራዊ ኹኔታ/ዎች ሳንመረምርና ትርጉም ባለው መንገድ ሳናስተውል፣ ፈልገን መስሎን፣ ፈልገን፣ በእጅ አዙር በአስተሳሰብና አመለካከት ቅኝ ተገዝተን፣ ያወቅን መስሎን፣ አዋቂዎች ተብለን እውቅና ተሰጥቶን (ዲግሪ፣ማስተርስ፣ፒኤችዲ፣ ፕሮፌሰርሽፕ፣ የክብር ዶክትሬት – – – )፣ ሳናውቅ፣ በኹኔታዎች ተገደን አልያም አማራጭ አጥተን እንደምናቀነቅናቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

እነዚህን አንድ በአንድ እያነሱ መተንተኑ ካለን ኹለንተናዊ የአስተሳሰብና አመለካከት ደረጃ፣ የ“እናውቃለን” ትምክህት መንሰራፋት፣ የሀሳብና ዕሳቤ የውይይት ባሕል አለመዳበር አንጻር ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝንና በተሳሳተ መንገድ የመተርጎሙ (misunderstand) ና የመደረጉ እድል እጅግ ከፍተኛ በመኾኑ ገለጻችንን ከእምነትና ከእውቀት አንጻር ከማድረግ ይልቅ ድርጊታችንን መነሻ ለማድረግ እንገደዳለን፡፡

አንድን ነገር ትርጉም ባለው መንገድ ለመረዳት ከድርጊቱ ከመጀመር ይልቅ ድርጊቱ የተሸከመውን እውቀትና እውቀቱ የተመሰረተበትን እምነት በማዕቀፍ ደረጃ መመርመሩ እጅግ አስፈላጊ ቢኾንም አማራጭ ሲታጣ ግን ውስንነቱን በቅድሚያ በመቀበል ድርጊቱን ራሱ ማጠየቁ አንድ የመተንተኛ መንገድ በመኾኑ ከድርጊቱ እንነሣለን፡፡

ዛሬ ከባቢያዊነትን በእጅጉ የሚያወግዘውና ውግዘቱን በእጅጉ የሚተነትን ከባቢያዊ እንመለከታለን፡፡ ዘረኛነትን ተንትኖ እያወገዘ ራሱ ግን ከሚያወግዘው በላይ ዘረኛ የኾነ – እንዳለው መሣሪያ በኹለንተናዊ መንገድ የሚያወግዘው የሚያደርገውን የሚያደርግ፣ የሚያምነውን የሚያምን፣ የሚያውቀውን የሚያውቅ ከተጠቃሚነት ውጭ አንዳች ልዩነት የሌለው ኾነን ስለሀገራዊነት እናነሣለን፡፡ በከባቢያዊነት ኹለንተናዊ ማዕቀፍ ቀን ከለሊት እየኖርን በሀገራዊነት ማዕቀፍ የሚገኝ ውጤትን እንናፍቃለን፡፡

የሥልጣን ፖለቲካ ደም ስር የኾነውን ሴረኝነት ባሕል አድርገን፤ ቁጭት መፍጠሪያ መሣሪያውን ጠላትነትን (Enemity) በኹለንተናዊ መንገድ እየተጠቀምን፤ መመኪያውን ኃይል – ደሙን ደግሞ ማስመሰልና ሀሰተኝነትን አድርገን ሳለን የፖለቲካ ደም ስር የኾነውን ሀሳባዊነትን ባሕል ያደረገ፤ መሣሪያውን ዕሳቤና ምክንያታዊነት የሚጠቀም፤ ደም ስሩን ሀገራዊ ማዕቀፍ – ደሙን ደግሞ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያደረገ ውጤት እንደሰኩራለን፡፡ በጓዳ የሥልጣን ፖለቲካ ውስጥ ኾነን የአደባባይ ፖለቲካ (ሀሳባዊ) ውጤት እንሻለን፡፡

የሥልጣን ፖለቲካ ኹለንተናዊ ቅኝ ተገዥ ኾነን የፖለቲካ ፍሬ እንሻለን፤ መንግሥትና ፓርቲ ሳንለይ በመለየት የሚገኝ ውጤት እንጠብቃለን፡፡ ሥልጣንን በኹለንተናዊ መልኩ የኹሉ ነገር መለኪያ (a standard for everything) አድርገን የዕውነት (Truth) ኹሉ ነገር መለኪያ ፍሬ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ዲሞክራሲያዊ ሳንኾን ዲሞክራሲያዊ ዕሴትን በእምነት፣ በእውቀትና በድርጊት ደረጃ እንደግለሰብ፣ ቡድንና ተቋም ሳናዳብርና ለማዳበር ሳንተጋ ዲሞክራሲዊነትና የዲሞክራሲያዊ ዕሴት ባለቤትነትና ተጠቃሚነትን እንሻለን፡፡ በስሜታዊነትና በጭፍን ደጋፊነት ውስጥ እየዳከርን የምክንያታዊነትና ዕሳቢያዊነትን ትሩፋት እንሻለን፡፡

“ሃይማኖተኛ ነን!” – “የዕምነት ሰዎች ነን!” ብለን ስለሰው መሰደድና ዘረኝነትን እንሰብካለን፡፡ እናቀነቅናለን፡፡ በድንበር ተሻጋሪ ዓለም አቀፋዊ ዕምነት ውስጥ ኾነን ከባቢያዊነትን በሕይወታችን እናሠለጥናለን፡፡ ጓዳዊ የኾነ ኹለንተናዊ የአኗኗር ዘይቤን አዳብረን ይዘን አደባባያዊ ኹለንተናዊ የአኗኗር ውጤት እንጠይቃለን፡፡ ተማርን ብለን መማርን በአኗኗር ሳንገልጽ – በመማርና ባለመማር መሐከል መሠረታዊ የአኗኗር ልዩነት እንደግለሰብ፣ ቡድንና ተቋም ሳንፈጥር የመፍጠር ጸጋ ተጠቃሚ መኾን እንሻለን፡፡

በርዕይ ጉዞ የሚገኝ ውጤትን በርዕይ አልባነት ለማግኘት፤ ሌሎች ለዘመናት ገንብተው የደረሱበትን እኛ ትላንት ገና ሳይገባን ጀምረን – የሱን ውጤት እንጠብቃለን፤ በተቋማዊነት ሂደት የሚገኝ ውጤትን በተቋም መሣሪያ ሂደት በተቋማዊ ግንባታ መደነባበር ውስጥ ኾነን እንሻለን፡፡

ይህ በንዲህ እንዳለ እንደሀገር ያልመለስናቸው እጅግ ከፍ ያሉ ኹለንተናዊ ጉዳዮች አሉብን፡፡ በአንድ በኩል ዕምነት አለን በሌላ በኩል ለዘመናት የሥልጣን ፖለቲካ የሠለጠነብን – የሥልጣን ፖለቲካ አስተሳሰብና አመለካከት በእምነት፣ በእውቀትና በድርጊት ደረጃ ቅኝ ተገዥዎች የኾንን፤ በአንድ በኩል ሃይማኖት አለን በሌላ በኩል አስመሳይነት፣ ድብቅነትና ከባቢያዊነትን ባሕላችን አድርገናል፤ በአንድ በኩል ሀገራዊ ዕሴቶቻችን አብረው አኑረውናል በሌላ በኩል ትርጉም ያለው ኹለንተናዊ ልዩነቶቻችንን የሚሸከምና የተሸከመ ሀገራዊ ርዕይ የለንም፤ በአንድ በኩል ብዙ ምንፈልጋቸው ነገሮች እንተነትናለን ግን ሀገራዊ ዕሳቤ ለማዳበር አንተጋም፤ በቀጥተኛ ቅኝ ግዛት ባለመገዛታችን እንኮራለን በአንጻሩ በቀጥተኛ ባልኾነ መንገድ በእምነት፣ በእውቀትና በድርጊት ደረጃ ለመገዛት እንተጋለን፡፡ አልፎ ተርፎም በዚህ ከመቆጨት ይልቅ መገዛታችንን እንኮራበታን፡፡ እነዚህ መቼ ይታረቁ ይኾን? መታረቅስ ይችላሉ? የኛስ ትክክለኛ ማንነት የቱ ነው?

በአለም ታሪክ ስደተኞችን በመቀበል ታላቅ ታሪክ ያለን ሕዝብ ኾነን ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እርስ በራሳችን የምንሳደድ፣ የምንፈነቃቀል ስንኾን ሌሎች ግን ስደተኞች በሀገራቸው ባለመብት ኾነው ዛሬ በአሜሪካ፣ በምዕራብ አውሮፓም ኾነ በእስራኤል የውስጥ ፖለቲካ ትልቅ ተጽዕኖ ሲፈጥሩ – እኛ ግን ለሌላ ዜጋ ጓዳችን ኹሉ ሳይቀር የሚከፈት ኾኖ ለራስ ዜጋ ግን አዳጋች፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ስደተኛ ተቀባይ የመኾናችን እውነታ (Reality) እንዳለ ኹሉ በሚሊዮን የሚቆጠር የውስጥ ተፈናቃዮችና ተሰዳጆች ያሉባት ሀገር የመኾናችን እውነታ (Reality) እንዴት ይጣጣማል?

ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ነጻነት፣ ልማት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ መልካም አስተዳደር – – – ለማንኛውም ሕዝብ የወደፊት ብሩህ ጉዞ ዘሮች ናቸው፡፡ “ዘርን ማግኘት ፈታኝ ነው፡፡ ዘርን ከማግኘት በላይ ዘር የሚዘራበትን ቦታ ማግኘት ደግሞ እጅጉን ፈታኝ ነው፡፡ ስለኾነም ዘር በተገኘበት ቦታ አይዘራም፡፡ ዘር በማንኛውም ጊዜ አይዘራም፡፡ ዘር ትክክለኛ ቦታና ትክክለኛ ጊዜን – ከባለቤቱ ትጋትና ከአስገኚው ጠባቂነት ጋር መቆራኘቱን ለፍሬያማነቱ የግድ ይላል፡፡ አምስቱ ካልተጣጣሙና ካልተጣመሩ – አልያም አንዳቸው ቢጎሉ ፍሬያማ ሳይኾን ይቀራል፡፡ የሀገር ኹኔታም እንዲሁ ነው፡፡”

ስለኾነም የምንሻቸውን፣ የምንደሰኩራቸውን፣ የምንጮህላቸውን – – – ወዘተ ነገሮች ከመግለጽ በፊት ይህን ለማግኘት የሚያስችል ነባራዊ ኹለንተናዊ ኹኔታ/ዎች ነበረን ወይ? አለን ወይ? ሊኖረን ይችላል ወይ? ብሎ ትርጉም ባለው መንገድ መጠየቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

መኾን ባለብን አልያም እንድንኾን በምንመኘው ሳይኾን እንደሀገር እንዳለን ነባራዊ አቅም፣ ብቃት፣ ምቹ ኹኔታ፣ ችሎታ፣ ስሜት፣ ፍላጎትና የዕይታ አድማስ ማድረግ ስለምንችለው ብቻ ትኩረት በማድረግ ወደ መኾን ሚገባንና መኾን ወደ ምንፈልገው በኹለንተናዊ መንገድ መትጋት አማራጭ የሌለው የመፍትሔ አቅጣጫ ነው፡፡ አለበለዚያ ከንቱ ድካም፣ ከንቱ መስዋዕትነት፣ ከንቱ አኗኗር፣ ከንቱ ህልመኝነትና ከንቱ ተስፈኛነት አለፍ ሲልም ከፍ ያለ ቅዠታምነት ነው፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

 

 

The post ‘ፍላጎታችን ወደፊት ድርጊታችን ወደኃላ!’ (ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ) appeared first on ሳተናው: Satenaw: Ethiopian News/Breaking News: Your right to know!.


‘ፍላጎታችን ወደፊት ድርጊታችን ወደኃላ!’ (ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ)