ከዘንድሮ መኸር እርሻ ከዋና ዋና ሰብሎች ከ382 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል

የግብርና ሚኒስቴርም በክረምት ወር መጀመሪያ የዝናብ መብዛት እና እጥረት በተለያዩ ክልሎች መከሰቱን በማስታወስ አሁን ላይ ግን በሁሉም ክልሎች የተስተካከለ የአየር ሁኔታ በመኖሩ የተሻለ ምርት ይጠበቃል ብሏል።

ሚኒስትር ዴታው አቶ ሳኒ ረዲ የመኸር ምርቱን የተሻለ ለማድረግ በግብዓት አቅርቦት ረገድ መንግስት ከ15 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እና ከ1 ሚሊየም ኩንታል በላይ ዘር ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ይህም አሃዝ ከከዚህ ቀደሙ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአየር ሁኔታው ምቹነት ምክንያት ሊነሱ የሚችሉትንም ተባይ ለመከላከል የአዳሚ ቱሉ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ፣ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን እና ሌሎች ተቋማት የምንዛሬ እጥረት እንዳይገጥማቸው ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸው ገልፀዋል፡፡

በሌላ መልኩ በሶማሌ ፣ አፋር ፣ ምስራቅ ኦሮሚያ ፣ አማራእና ትግራይ ክልሎች ከፍተኛ አደጋ ሊፈጥር የነበረውን የበረሃ አንበጣ በዋናነት ከምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከያ ጋር በመቀናጀት ጉዳቱን መቀነስ መቻሉን እና አሁን ያለው የሰብል አዝማሚያ በአጠቃላይ ተስፋን የሚሰጥ መሆኑን አቶ ሳኒ ገልጸዋል።

በአፈወርቅ አለሙ


ከዘንድሮ መኸር እርሻ ከዋና ዋና ሰብሎች ከ382 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል