የእሬቻ የጎዳና ሩጫ የፊታችን እሁድ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሆራ ፊንፊኔ የእሬቻ ሩጫ ውድድር መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

በሩጫ ውድድሩ ላይ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎም ይጠበቃል።

ለሩጫው የሚያስፈልገው ቲሸርት በፌደራልና በክልሉ የቀረበ ሲሆን፥ በአዲስ አበባም በኦሮሚያ ባህል ማዕከልና በአስሩም ክፍለ ከተሞች ይገኛል ነው የተባለው።

የአንዱ ቲሸርት ዋጋም 250 ብር ሲሆን፥ ውድድሩን የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከዲ ሲ ኢንተርቴይመንት ጋር በጋራ የተዘጋጀ ነው።

በሩጫ ውድድሩ ላይ መደበኛ አትሌቶች በሁለቱ ጾታዎች የሚሳተፉ ሲሆን፥ ለአሸናፊዎቹም የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል ተብሏል።

ውድድሩ መስከረም 24 በአዲስ አበባ የሚከበረውን የእሬቻን በዓል አስመልክቶ የሚካሄድ ሲሆን፥ ከበዓሉ ቀደም ብሎ ከመስከረም 12 እስከ መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ባዛር፣ የንግድ አውደ ርዕይ እና ትልልቅ ፎረሞች እንደሚካሄዱ ተገልጿል።

 

 

በትእግስት አብርሃም

 


የእሬቻ የጎዳና ሩጫ የፊታችን እሁድ ይካሄዳል