ኢትዮጵያ ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ላይ ያቀረበችውን ሃሳብ ውድቅ አደረገች

ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፥ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች መካከል በተደረገው ውይይት ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል ላይ የራሷን አዲስ ሃሳብ አቅርባላች።

ሃሳቡም የግድቡ የውሃ ሙሌት በሰባት አመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ በአመት 40 ቢሊየን ሜትር ኪዮብ ውሃ እንድትለቅ እና የአስዋን ግድብ የውሃ መጠኑ ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ ግድቡ ዋና ስራው ውሃ መልቀቅ ብቻ እንዲሆን የሚጠይቅ ነው።

ኢትዮጵያ ሃሳቡ እስካሁን ቀደም ሲል በሶስቱ ሀገራት መካከል የተፈረመውን የአባይ ውሃ አጠቃቀም የመርህ ስምምነት የጣሰ ነው ብላለች።

አዲሱ የግብፅ ሃሳብ ኢትዮጵያን አላስፈላጊ እና ጎጂ ግዴታ ላይ የሚጥል በመሆኑ ሃሳቡን እንዳልተቀበልችውም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለም፤ ግብፅ አመታዊ የውሃ ፍስቱ 40 ቢልዮን እንዲሆን ያቀረበችው ጥያቄ፤ ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን እንዳትጠቀም የሚከለክል በመሆኑ አልተቀበለችውም ብለዋል።

የተደራዳሪ ቡድኑ አባል እና የሚኒስትሩ አማካሪ ኢንጂነር ጌድዮን አስፋውም፤ ኢትዮጵያ በአመት ልትለቅ የምተችለው ውሃ መጠን ከ29 አስከ 35 ቢልዮን ሜትር ኪዩብ ብቻ ነው ብለዋል።

ኢንጅነር ጌድዮን አንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በአመት 40 ቢልዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመልቀቅ ግዴታ ወስጥ ብትገባ፤ የአየር መለዋወጥብን ተከትሎ በሚከሰት ደርቅ የገባችውን ውል መፈፀም ስለማትችል፤ ሃሳቡን ወድቅ ማድረጓ ተገቢ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ውይይት በባለሙያች ደረጃ ከመስከረም 22 ጀምሮ በሱዳን ይካሄዳል።

ውይይቱ የሶስቱ ሀገራት ገለልተኛ ቡድኖች በታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል፣ አለቃቀቅ እና በታችኛው የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ተፅእኖ ላይ ይወያያሉ።

ውይይቱ በውሃ አለቃቀቁ ላይ ሳይንሳዊ ሃሳብ የሚያቀርቡበት እና ካሁን ቀደም ከተካሄዱ ምክክሮች የቀጠለ እንደሚሆንም ተነግሯል።

ባለሙያዎቹ ተወያይተው በደረሱበት ነጥብ ላይም የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች ሌላ ምክክር እና ድርድር ያካሂዳሉ።

በዳዊት መስፍን


ኢትዮጵያ ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ላይ ያቀረበችውን ሃሳብ ውድቅ አደረገች