የኢትዮ ቱኒዚያ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ ቱኒዚያ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በፎረሙ ላይ ከሁለቱ ሃገራት የተውጣጡ የቢዝነስ እና የቱኒዚያ የባለሙያዎች ቡድን ተሳትፈዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ ኢትዮጵያና ቱኒዚያ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፥ ፎረሙ የሃገራቱን ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአውሮፓ እና አሜሪካ ገበያዎች እንደምትሳብ ያነሱት ሚኒስትር ዲኤታው፥ ይህንን ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ማድረግ ቢቻል ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ቱኒዚያ ካላት ጠንካራ ኢኮኖሚ አንጻር ይህን እድል መጠቀም ቢቻል አዋጭ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የቱኒዚያ ባለሃብቶችም በኢትዮጵያ ያለውን አመቺ የኢንቨስትመንት ዕድል እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል።

የቱዚያው አቻቸው ሃተም ፈርጃኒ በበኩላቸው፥ ሃገራቱ ብዙም ታሪክ የሌለውን አብሮ የመስራት ሂደት ጀምረዋል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ሁለቱ ሃገራት ከስራ እድል ፈጠራ አንጻር መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፥ አብሮ የመስራቱ ሂደትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው።

አያይዘውም የሃገራቸው የባለሙያዎች ቡድን ያገኘው ቀና ምላሽ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁለቱ ሃገራት የንግድ ትስስር መፍጠር እንዲችሉ ያግዛቸዋልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ እምቅ ሃብት አላት ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፥ ወደ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከመቀየር አንጻር ግን ከቱኒዚያ ልትማር እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

በዚህ ዘርፍም ሃገራቸው ያላትን ሰፊ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም አስታውቀዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ አመራሮች ተገኝተዋል።

የሁለቱ አመራሮች ሃገራቱ የጀመሩትን አዲስ የኢኮኖሚ ጥምረት አድንቀው፥ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

በፎረሙ ላይ ሃገራቱ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ፣ በቱሪዝም፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በሃይል እንዲሁም በሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ምክክር ተካሂዷል።

 

በፍሬህይዎት ሰፊው

 


የኢትዮ ቱኒዚያ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው