የከተማ አስተዳደሩ በስታዲየም ዙሪያ ላሉ በ46 ማህበራት ለታቀፉ 278 ስራ አጥ ወጣቶች የመስሪያ ሱቆችን አስረከበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስታዲየም ዙሪያ ላሉ በ46 ማህበራት ለታቀፉ 278 ስራ አጥ ወጣቶች የመስሪያ ሱቆችን አስረከበ።

የመስሪያ ሱቆቹን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለወጣቶቹ ማስረከባቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የከተማ አስተዳደሩ የንግድ ሱቆችን በልዩ ሁኔታ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶቹ በዛሬው ዕለት በዕጣ ያስተላለፈው።

የመስሪያ ሱቆቹ ስፋት ዝቅተኛው 82 ካሬ ሜትር ሲሆን፥ ከፍተኛው 392 ካሬ ሜትር ሆኖ በወጣው ዕጣ መሠረትም ለባለዕድለኞቹ ተላልፈዋል።

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በዕጣ ማውጣት መርሃ ግብሩ ላይ ለስታዲየም ዙሪያ ስራ አጥ ወጣቶች የተፈጠረው የስራ ዕድል የከተማ አስተዳደሩ የከተማውን ወጣት ህይወት ለመቀየር የያዘው ግዙፍ ፕሮጀክት አካል ነው ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ካለፈው አመት በተሻለና የወጣቶችን ህይወት በሚቀይር መልኩ አዳዲስ ዕቅዶችን በመንደፍ ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል እንደሚፈጠር ተናግረዋል።

የንግድ ሱቆቹን ከመስጠት በተጨማሪም ለወጣቶቹ ጠንካራ ሙያዊ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ተገልጿል።

በርክክቡ ላይም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ደጋፊዎች እና የከተማው ወጣቶች ተገኝተዋል።


የከተማ አስተዳደሩ በስታዲየም ዙሪያ ላሉ በ46 ማህበራት ለታቀፉ 278 ስራ አጥ ወጣቶች የመስሪያ ሱቆችን አስረከበ