በመዲናዋ በህገ ወጥ መንገድ ለገበያ ሊቀርቡ የነበሩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን የጫኑ 25 ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ለገበያ ሊቀርቡ የነበሩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን የጫኑ 25 ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስርመዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ድንገተኛ ቁጥጥር ነው በህገ ወጥ መንገድ ለገበያ ሊቀርቡ የነበሩ የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን እንዲሁም ልዩ ልዩ የምግብ ግብዓቶችን የጫኑ የጭነት ተሽከርካሪዎችን በቁጠጥር ስር ያዋለው።

ተሽከርካሪዎቹ በትናነትናው እለት በአራዳ ክፍለ ከተማ  ልዩ ቦታው ፒያሳ አትክልት ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው በቁጠጥር ስር የዋሉት።

በተሽከርካሪዎቹ ላይ ተጭነው የነበሩት የተለያዩ አትክልቶች፣ ፍራፍሬዎች እና ልዩ ልዩ የምግብ ግብዓቶች  ህጋዊ ስርዓቱን ጠብቆ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚሸጡ በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 7 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ አራጋው ገልፀዋል።

የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ከንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ ከደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽህፈት ቤት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን እንዲሁም ልዩ ልዩ የምግብ ግብዓቶችን ወደ ገበያ ይዞ በመግባት ያለ ደረሰኝ እና ያለ ንግድ ፈቃድ በመሸጥ ከህጋዊ የንግድ ስርዓት ውጪ የዋጋ ንረት እንዲከሰት ለማድረግ በሞከሩ አካላት ላይ ድንገተኛ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረጉንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።


በመዲናዋ በህገ ወጥ መንገድ ለገበያ ሊቀርቡ የነበሩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን የጫኑ 25 ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ