ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሸገር ሬዲዮ (ጠገናው ጎሹ)

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

የሬዲዮውን ቃለ ምልልስ  እኔም እንደ አንድ የአገሩን ጉዳይ እንደሚከታተል ኢትዮጵያዊ አዳመጥኩት  ።  እውቋና የማደንቃት ፀሐፊ መስከረም አበራ  የፃፈችውን አጭር አስተያየትም በጥሞና አነበብኩት ።

የእኔን እነሆ !

በጥሩ አገላለፅ ተገልጿል የምንለው የአስተዳደግና የቤተሰባዊ ግንኙነት ትረካው  መጨመሩ ካልሆነ በስተቀር የቃለ ምልልሱ አጠቃላይ ይዘት ከሥልጣን እርክክቡ ጀምሮ ከአንድ ዓመት በላይ ስንሰማው ከነበረው ለስሜት ቅርብ ከሆነ የህዝበኝነት (ተግባራዊ ይሆናል ወይ ሳይሆን ህዝብን ደስ ያሰኝልኛል ወይ ? )   ዲስኩር ጨርሶ የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም ።  አዎ! የትህትና ቅላፄ ያለው መሆኑ እውነት ነው። የገሃዱ ዓለም ፖለቲካ ግን በትህትና ቅላፄና በሞራላዊ ዲስኩር ብቻ የሚቀመስ ፈተና አይደለም። መሥራት የሚችሉትን ተናግሮና አድርጎ በመገኘት ነው የገሃዱን ዓለም ፈተና መጋፈጥ የሚቻለው።

የቃለ መጠይቁ አቅራቢ የወ/ሮ መዓዛ ብሩ ጥያቄዎችም አንድ ዓመት ሙሉ አገርን ማረጋጋት የተሳነውን  መንግሥት መሪ ምን ያህል  የሚፈትኑ (challenging) እንደ ነበሩ በኩራት መመለስ የሚቻል አይመስለኝም ። ጥያቄዎችን በመሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው ምስቅልቅልና አስከፊ ሁኔታ አንፃር እያሰቡና እራስንም በነዚያ ሚሊዮን ንፁሃን ዜጎች መከራና ስቃይ ውስጥ እያስገቡ ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት የመጀመሪያው ረድፍ ላይ የሚገኘውን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተጠየቅ! ከማለት ይልቅ ገብስ ገብሱን (ቀና ቀናውን) እየጠየቁ በጥሩ ቃላትና አንደበት በሚመለሱ መልሶች “ተአምረኛው ፖለቲከኛ”  በሚል አይነት አድናቆት አይንን አፍጥጦ ማዳመጥ የተዋጣለት ጋዜጠኝነት ነው  ማለት የሙያውን ሃያልነት ዝቅ ማድረግ ነው የሚሆነው።

የመስከረም አበራ አስተያየትም በተለመደው የጠቅላይ ሚኒስትሩ  የአቀራረብ ትህትና እና የቃላት አደራደር ወይም አንደበተ ርእቱነት የተማረከ በመሆኑ ደካማ ነው የሚል አስተያየት አለኝ ።

ልቀጥል

ለመሆኑ የአንዲት ደሃ አገር ባለሥልጣን እንደማነኛውም ኢትዮጵያዊ ህፃንና ወጣት ሆኘ ነው ያደግሁ ማለቱን   እንዴት በተለየ ሁኔታ  ሰው ሰው ሸተተኝ ወይም አልሸተተኝም የሚያሰኝ አድናቆትን ይፈጥርብናል ?

በአገር መሪነት  ወይም በሌላ ከፍተኛ ሥልጣን እርከን ላይ የምናገኛቸውን ፖለቲከኞች ትርክት በእንዲህ አይነት ሁኔታ የምናይበት ሥነ ልቦና ትክክል አይመስለኝም። መደብ ላይ ተኝቶ ያደገ ሰው በታሪክ አጋጣሚም ይሁን በግሉ ጥረት ወይም እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ   ከኢህአዴግ ወጥቶ ኢህአዴግን በማደስ  የመሪነትን ቦታ ሊይዝ መቻሉ ተአምር ነው እንዴ? ነው ወይስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ ብቻ የተሰጠ ልዩ ስጦታ ነው? ምነው እያደር አስተሳሰባችን ይኮሰምናል ?

“ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሆንኩ የምሠራው ለሁሉም ነው።” ሲል አረጋገጠ አይነት አግራሞትን ወይም አድናቆትን ምን  ይሉታል ? አንድ ፖለቲከኛ  ከዚህ ሌላ ምን እንዲል ነበር (ነው) የተጠበቀው ወይም የምጠበቀው? አንገርምም?

 

“ሃገራቸውን እንደሚወዱ የገለፁበት ልቤን ነካኝ” የሚል  አይነት  ስሜታዊነትንስ ከገሃዱ ዓለም ወይም ከተግባር ሰውነታችን አንፃር ከምር ካላስተያየነው የት ያደርሰናል ?

” ነገ ጧት ሌላ ጥፋት ሊያጠፉ ይችላሉ  ፤ ኢትዮጵያን ከመውደድ ከፍታ እስከ አልወረዱ ድረስ ከነቃርሚያው ተስፋ እንዳደርግ ይረዳኛል ።” ምን ማለት ነው?  የተስፋ ቃርሚያስ ምን ማለት ነው? ያውም ለቃርሚያ ተስፋ ነው እንዴ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ ምልልስ ልብ ያላወሰ ?   ኢትዮጵያን የመውደድ ከፍታ መለኪያው ምንድንና የት ድረስ ነው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን ከፍ የሚያደርግ በቅጡ እንድትቆይ የሚያደርግ ሃላፊነት እየተወጡ ነው እንዴ ? መቸነው ከፍ ብለው አገርን ከፍ ያደርጋሉ የምንለው? እየዳከሩ ያሉት እኮ   ኢትዮጵያን ዝቅ   በሚያደርጋት የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጥራ ፖለቲካ አዙሪት ውሰጥ ነው ። ለውጥ አመጣለሁ የሚሉን እኮ የመከራው ሁሉ ምንጭ የሆነው ህገ መንግሥት እና ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓተ ኢህአዴግን እያስቀጠሉ  ነው። ለውጥ የሚሉን እኮ እርሳቸውና በወንጀል የተዘፈቀው ገዥ ቡድናቸው የሚሉትን (የሚፈልጉትን)  እንጅ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚለውን (የሚፈልገውን) መሠረታዊ ለውጥ አይደለም።

የመጣንበትና የምንገኝበት አስከፊ ፈተና እኮ  በሞራልና “ልቤን አላወሰው” በሚል የምንወጣው አይደለም።

ገና ከለውጥ ብልጭታው ጀምሮ  “ስንወለድም ኢትዮጵያውያን ፥ ስንሞትም ኢትዮጵያውያን ፥ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው”  የሚል እፁብ ድንቅ አባባል ሲያስተጋቡ ከነበሩ ፖለቲከኞች  “አገራችን ስንውድ እስከ ነፍሳችን ነው” ቢሉ ምን አዲስ ነገር ሆነና ነው ልቤን ነካኝ የሚያሰኘን  ?

የፖለቲከኛን ፖለቲከዊ ሰብእናስ እውን በእንዲህ   አይነት ግልብ  “እንስፍስፍነት” ነው እንዴ የምንለካው?

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርንና የእኒህን ክፋት ወይም ደግነት  በዋናነት የምናነፃፅረው በየነበሩበት ወይም በያሉበት ወቅትና ተጨባጭ ሁኔታ እና  በድርጊት ካደረጉት ወይም ከሚያደርጉት ጋር   እንጅ  ልብ የሚበላ አንደበት ነበራቸው ወይም የላቸውም ከሚል ነው   እንዴ

“ኢትዮጵያን በተወሰኑ ዓመታት ካደጉ አገሮች ተርታ እናደርሳታለን” የሚለው ዲስኩር በተጨባጩ ሁኔታችን ላይ ሳይሆን ፖለቲካና ሥልጣን ወለድ (political and authoritative) የሆነ አገላለፅ ነው። እውነት ቢሆን እንዴት ሸጋ ነበር!

ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ያለምንም ተጨባጭና ትንሽ እንኳ እንዲመስል የሚያስመስል ጥናታዊ ዋቢ ሳይኖር እንዲህ አይነት ከስሜት የማያልፍ ተስፋ “ማብሰር” ቢያንስ ባለሙያን መናቅ ነው። መሃይሙ ወገኔስ በለውጥ ስም ሥልጣን ላይ የወጣ ሁሉ የህልም እንጀራ እየጋገረ ሲያስጎመዠው መኖሩን ተለማምዶታል ።አንድ ቀን በቃኝ እስኪል ድረስ ተተኪዎችም በዚያው መቀጠላቸውን እየነገሩን ነው ።

የኢህአዴግ ፖለቲከኞችን ” ተአምረኞችና ሙሴዎች” እያልን የተቀበልንበት መንገድ ወደ የት እየወሰደን እንደሆነ እያየን መሆኑ ትምህርት አልሆነን ብሎ አሁንም በሚዲያ የሚሰጡትን ድንቅ ዲስኩር ለምን? እንዴት? ከየት ወደየት? መቸ? ወዘተ ሳንል ተቀብለን እፁብ ድንቅ እንላለን ።  ክፉ አባዜ ! ለዚህ ነውና ከተዘፈቅንበት መውጣት ያቃተን አሁንም ልብ እያልን ከመራመድ ሌላ የተሻለ አማራጭ ከቶ የለንም። ልብ ይስጠን አልልም ። አሳመሮ ሰጥቶናልና። ሳይመሽብን ልብ እንድንል ግን ይርዳን እያልኩ አበቃሁ ! 

 

 

The post  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሸገር ሬዲዮ (ጠገናው ጎሹ) appeared first on ሳተናው: Satenaw: Ethiopian News/Breaking News: Your right to know!.


 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሸገር ሬዲዮ (ጠገናው ጎሹ)