ምኑ ነው ስህተቴ” (ገጣሚ ህሊና ደሳለኝ)

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

ተሳሳትሽ አትበለኝ የቱ ነው ስህተቴ፤
ጥበብ ነው ማርከሻ የብዕር ጥይቴ።
አዎ መንጋማ አለ ከጥንት መሰረቱ፤
እየሱስን አስረው በርባንን ሲያስፈቱ።
ዛሬም በኔ ዘመን
የመንጋ ፍርድ ነው ሀገሬን የፈታት፤
አዋቂ ዝም ብሎ መንጋ እየፈተታት።
በድንጋይ በርሚል ውስጥ ሽ ድንጋይ ቢቀቀል፤
ሽ ዘመን ተጥዶ እልፍ አመት አይበስል።
አገር ተረክቦ በሰፈረ የኮራ፤
የመንጋ ፍርድ አይደል ያበቃን ለተራ።
የቱ ጋ ነው የሳትኩ አርመኝ መምህሩ፤
ምላስክን አጥፈኽው ሞክር በብዕሩ።
ዘመን የሰጠው ቅል ድንጋይ ቢሰብር ጣሪያ፤
ማዕዘን ተደርጎ አይሆን ለቤት መስሪያ።
ሰውነት ነው ልኩ የሰው ሚዛን ፍርዱ፣
አዋቂ እንዲበይን መንጋዎች ይውረዱ።
አሁንም እላለው
በመንጋ ተፈጭቶ በመንጋ ተጋግሮ፤
እልፍ ጾም አዳሪ ወና ነው ጉረሮ።
ቤት መምታት ቤት መድፋት ስንኝ መቋጠሩ
ጥበቡ ቢያቅተው፤
ቤት እያፈረሰ ህዝብ እያስደደ
አገሩን አመሰው።
እኔ ይሄንን ሰው፣
ሌላ ምን ልበለው፣
መንጋነትም ሲያንሰው።
በባዶነት ሙሌት በዘር እብሪት ታስሮ፣
ከጥበብ ጓዳ ውስጥ ከሰውነት አጥሮ።
አበውን ሲያሰደድ ሲያርድ ሲያጎሳቁል፣
አንተም መንጋ ካልሆንክ መቼም ሰው ነው አትል።
እና ምኑ ላይ ነው ብዕሬ የሳተች፣
ብሔር የነቀፈች ህዝብን ያዋረደች።
“ንገረኝ በሞቴ የመንጋው ጠበቃ
አንተም ሰው ሁንና መንጋነትህ ይብቃ”

ረጅም እድሜ እና ክብር ይስጥልን

The post ምኑ ነው ስህተቴ” (ገጣሚ ህሊና ደሳለኝ) appeared first on ሳተናው: Satenaw: Ethiopian News/Breaking News: Your right to know!.


ምኑ ነው ስህተቴ” (ገጣሚ ህሊና ደሳለኝ)