ከህውሀት በብዙ እጥፍ የሚያስከነዳ የተረኝነት ስካር ውስጥ የተዘፈቁት ጽንፈኞች (በመሳይ መኮንን)

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

መሳይ መኮንን (የኢሳት ጋዜጠኛ)
መሳይ መኮንን (የኢሳት ጋዜጠኛ)

የሰሞኑ ግርግር ያስጨንቃል። የኦዲፒ ሰዎች ሰከን ማለት ቢችሉ ጥሩ ነው። በጽንፈኞች የተጠለፉት አንዳንድ አመራሮቹ ከማይክና ከፌስ ቡክ ለጊዜው እንዲርቁ ቢደርግ ዋናው ተጠቃሚ ራሱ ኦዲፒ ነው። ከህውሀት በብዙ እጥፍ የሚያስከነዳ የተረኝነት ስካር ውስጥ የተዘፈቁት ጽንፈኞቹ ለኦዲፒ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የሚያስገኙለት እንደማይሆኑ ይታወቃል። ኦዲፒ ውስጡን በሚገባ ካላጠራ በጽንፈኞቹ ድር ተተብትቦ ውድቀቱን ቅርብ እንደሚያደርገው ጥርጥር የለውም።

ሀገር ቤት እግራቸውን የተከሉትና በባህር ማዶ ያሉት ጽንፈኞቹ የዘረኝነት አዶ ከበሬያቸውን መደለቁን በእጥፍ ጨምረው መጥተዋል። በርቀት ከኮሚውተር ጀርባ በኪቦርድ ሲደቀድቁት የነበረውን የዘረኝነት ጥይት በቅርበት ከቤተመንግስት አፍንጫ ስር ሆነው እያስወነጨፉት ነው። ትንሽም ቢሆን ማዕበል የመፍጠር አቅም አዳብረዋል። ለጊዜው ሳያላምጥ የሚወጥ፡ ሳይረዳ የሚከተል፡ በዕውቀት ሳይሆን በስሜት የሚነዳ ትውልድ ከጎናቸው መሰለፉ አይቀርም። ቀውስ እየፈጠሩ፡ ግጭት እየጠመቁ፡ መቀጠላቸው ይጠበቃል። እኔ ግን በጭለማ ከተዋጠው ዋሻ ማዶ ጭል ጭል የምትል ብርሃን ከርቀት ትታየኛለች። ባዶ ምኞት አይደለም። የቀን ቅዥትም አይደለም። መሬት ላይ በሚራመድ፡ ተስፋ በሚሰጥ የታጀበ የነገ እውነት እንጂ።

ውህድ ፓርቲው ለጽንፈኞች የምጸአት ቀን ይዞባቸው መጥቷል። የዘር መዋቅርን ያልተከተለ፡ ኢትዮጵያዊ ቅርጽና ቁመና የሚኖረው ሀገራዊ ፓርቲው በተመሰረተ ማግስት በኢትዮጵያ የብሄር ፖለቲካ ወደ መቃብር መውረዱ የማይቀር ነው። እዚህ ላይ የብሄር ፖለቲካ ይቀራል ሲባል የብሄር ብሄረሰቦች መብት ይደፈጠጣል፡ አህዳዊ ስርዓት አፈር ልሶ ይነሳል የሚል መሰረት የሌለው ዲስኩር ይዘው የመጨረሻ እድላቸው በሃይልና በጉልበት የሚሞክሩ ጽንፈኞች ከወዲሁ ጡንቻቸውን እያፍታቱ እንደሆነ ይታያል። የማይቀረው ውህደት የእነሱን የፖለቲካ ፍጻሜ እውን ማድረጉን በመረዳትም ለማጨናገፍ እያንዳንዷን የጥፋትና የቀውስ እድሎች በመጠቀም ላይ ናችው። ሰሞኑን የምናየውና ብዙዎቻችንን ያሰጨነቀን እንቅስቃሴያቸው የዚሁ ቀቢጸ ተስፋ ሙከራቸው መገለጫ ነው። ውህዱ ፓርቲ እውን ከሆነ ከግጭት ቀለባቸውን የሚሰፍሩ፡ በህዝብ መተላለቅ ቢዝነሳቸው የደራላቸው ቀፋይ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች የገንዘብ ምንጫው መድረቁ የማይቀር ነውና ከወዲሁ ሰማይን ቧጠው፡ ምድርንም ሰንጥቀውም ቢሆን የእነአብይን እግር ቆርጠው መንገድ ላይ ለማስቀረት መፈራገጣቸው ይጠበቃል። የቀውስ ዜና በማራገብ፡ ክሽን ያለች ወሬ በመፍጠር የዩቲዩብ ገበያቸው የደራላቸው ነጋዴዎችም የሚበሉትና የሚጠጡት እንዳያጡ የውህድ ፓርቲውን መመስረትን በጎሪጥ ማየታቸውን መጥቀስ ያስፈልጋል።

ከፈረሱ አፍ እንደሰማሁት ሀገራዊው ፓርቲው ወደ ኋላ ላይቀለበስ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተጠግቷል። ከኢህአዴግ ውጪ የተሰለፉ አጋር ፓርቲዎች ተጠቃለው የውህድ ፓርቲው አካል ለመሆን ስምምነታቸውን ጨርሰዋል። ህወሀትም በአንድ እግሩ ኮንፌደራሊስቶች መንደር ረግጦ፡ በሌላኛው ደግሞ ውህድ ፓርቲውን ለመቀላቀል በር ዘግቶ እየመከረ እንደሆነ ተሰምቷል። ህወሀት ከተሳካላት የኮንፌደራሊስቶች ግንባር ፈጥሮ ወደ ቤተመንግስት ለመግባት እስከደም ጠብታ ሊሞክር ይችላል። ሆኖም ከወዲሁ በሁለተኛው እግሩ የውህድ ፓርቲው መንገድ ላይ ወጥቶ እየተራመደ ለመሆኑ ከሰሞኑ መቀሌ ላይ የተደረገው የመደመር ስብሰባ ላይ ተመስክሯል። ህወሀት ቤተመንግስት ባይገባ እንኳን በህይወት መቆየት የሚከለክለው ለጊዜው አይኖርም። የሰሞኑ ግርግር ተዋናይ የሆኖት የኦሮሞ ብሄርተኞች ግን ምርጫቸው አንድ ብቻ ነው። በጥርሳቸውም ነክሰው፡ በጥፍራቸው ቧጠው ተረባርበው ውህድ ፓርቲው እንዳይመሰረት ማድረግ ነው። ቀኑ የጨለመባቸው ቢመስልም ከመሞከር ወደኋላ የሚሉ አይደሉም።

ውህዱ ፓርቲ ከተመሰረተ በእነዶ/ር አብይ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ትልቁን ምዕራፍ ያጠናቅቃል ማለት ነው። ለውጡ መዋቅራዊ እንዲሆን፡ ስር ነቀል በሆነ መስመር ላይ እንዲወጣ ለሚጎተጉቱ ቅን አሳቢዎች ተስፋ የሚሰጥ ውጤት ሆኖ የሚመዘገብ ይሆናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የቀረውን የጎሳ ተኮር መስመር በማጥፋት የአፍሪካን ገጸ ምድር ከጎሳ ፖለቲካ ነጻ የመሆኑን ድል ያበስራል ማለት ነው። ከእንግዲህም ፖለቲካው ዕውቀት ላይ የተመሰረተ፡ በሃሳብ የበላይነት የሚመራ እንዲሆን ሰፊ እድል የሚሰጥ ታሪክ ይጀመራል ማለት ነው። ኢትዮጵያ ለዘመናት የተጣባትን፡ እንደውስጥ ደዌ ስጋዋን በልቶ የጨረሳትን ህመም የምትፈወስበትን መድሃኒት ታገኛለች ማለት ነው። በአጭሩ ለኢትዮጵያ ትንሳዔ እውን መሆን አይነተኛ ሚና የሚጫወት ይሆናል ማለት ነው።

በተቃራኒው በተአምር እንኳን የጽንፈኞቹ ሙከራ የሚሳካ ቢሆን የኢትዮጵያ ጉዳይ ስለማክተሙ ጥርጥር አይኖረውም። ኢትዮጵያን እንደካንሰር እየበላ የሚያጠፋትን የጎሳ ፖለቲካ እንዳይነቀል ሆኖ ይተከላል። የኢትዮጵያን ጥፋት በእድሜ ዘመናቸው በጸሎትና በትግል ሲናፍቁ የነበሩ ሃይሎች ኮንፌደራሊስት የሆኑ ግልገል መንግስታትን በመፍጠር የኢትዮጵያን ፍጻሜ እውን ያደርጋሉ። አከባቢው ወደግጭት ቀጠና ተቀይሮ ኢትዮጵያውያን ለጎጣቸው፡ ለመንደራቸው ይተላለቃሉ። የሩዋንዳ ዘግናኝ ታሪክን በእጥፍ የሚደግም ክስተት ይፈጠራል። አሸናፊ የሌለው፡ ለዓመታት የሚዘልቅ የማያባራ እልቂት የሚያስከትል ጦርነት ምስራቅ አፍሪካ ላይ ይታወጃል። ከዚህም የከፋ መፈጠሩ ይጠበቃል። እያሟረትኩ አይደለም። መዳረሻቸው የኢትዮጵያ መጥፋት የሆኑ ሃይሎች ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ፈጥረው የለውጥ ሃይሉን ከደቆሱት የማይቀር ግን የሚያስፈራ እውነት ለመሆኑ አልጠራጠርም።

በእርግጥ ኮንፌደራሊስቶችም ይሁኑ የኩሽ መንግስት አቀንቃኞች፡ ዓላማቸው ከዳር የመድረስ እድሉ በጣም ጠባብ ነው። የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ የሚያረጋግጠው ሰራዊቱንና የደህንነት መዋቅሩን የተቆጣጠረ ሃይል በመጨረሻም አሸናፊ መሆኑን ነው። በእኔ እምነት የዶ/ር አብይ የለውጥ ሃይል ከህዝብ ድጋፍ በተጨማሪ የሰራዊትና የደህንነቱን የበላይነትን ይዟል። ከጥቂት ጽንፈኛ ቡድኖች በቀር አብዙዎቹን የፖለቲካ ሃይሎች በመሰብሰባቸው ፖለቲካዊ የበላይነትንም ጨብጠዋል። ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነትና የእነአሜሪካን ድጋፍ ሲጨመርበት በሁሉ መስክ የለውጡ ሃይል ጽንፈኞቹን ደቁሶ ኢትዮጵያን ከተደቀነባት የጥፋት ግርዶሽ እንደሚታደጋት አምናለሁ።

ኢትዮጵያ መሃሉን ትሻገራለች። ወጀቡን ታልፋለች። እየናጣት ያለው ተርቡላንስ ጊዜያዊ ነው። በ1926 የተጻፈና የነጮችን ብሽቀት በሚያሳየው the powder barrel በተሰኘው መጽሀፍ ውስጥ ኢትዮጵያን ለመስበር የኢትዮጵያን ምሶሶዎች መነቅነቅና ማጥፋት የሚል ሀሳብ ሰፍሯል። ነጮቹ በፊት ለፊት ሲያቅታቸው በእጅ አዙር ይህን ህልማቸውን ለማሳካት ብዙ ሙከራ አድርገዋል። የነጮችን ቀመር ተከትለው ህወሀቶች ብዙ ሞከሩ። አልተስካላቸው። ኢትዮጵያ ኖረች። የህወሀት አቻና የባህሪ ወዳጅ ኦነግ 40 ዓመታት አረጀበት። አልተስካለትም። ዘንድሮ ጽንፈኞች ተራቸውን የእጅ አዙሩን የነጮች እቅድ ለማሳካት ከየአቅጣጫው ተነስተዋል። አይሳካላቸውም። ኢትዮጵያ ነገም ወደፊትም ትኖራለች።

The post ከህውሀት በብዙ እጥፍ የሚያስከነዳ የተረኝነት ስካር ውስጥ የተዘፈቁት ጽንፈኞች (በመሳይ መኮንን) appeared first on ሳተናው ዕለታዊ ዜናዎች:ጥናታዊ ጽሁፎችና ዝማኔዎች: መረጃ ማግኘት መብተዎ ነው!.


ከህውሀት በብዙ እጥፍ የሚያስከነዳ የተረኝነት ስካር ውስጥ የተዘፈቁት ጽንፈኞች (በመሳይ መኮንን)